“በጣም ኳስ የሚችል ቀልደኛ ሳቂታ መልካም ሰው ነበር።” ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ)
“ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ታሪክ አዋቂ ብዙዎች የሚሳሱለት ባለሙያ ነው” ካሳሁን ደርበው (ካስትሮ)
በስልሳዎቹ መጀመርያ አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ የስፖርት ባለሙያዎች በፈለቁበት ቂርቆስ አካባቢ ተወልዶ አድጓል። የተወለደበት አካባቢ ለእግርኳስ ቅርብ መሆኑን ተከትሎ አዲስ አበባ ስታዲየም ዙርያ እየዋለ የአፍላነት ዕድሜውን አሳልፏል። ስቴዲየም ዙርያ መወለዱም እግርኳስን እንዲወድ እንዲጫወት እንዲመለከት ትልቁን አስተዋፆ አድርጎለታል። በምድር ጦር ኦርኬስትራ ተቀጥሮ በሙዚቃ መሳርያ ተጫዋችነት ከቀድሞ አንጋፋ ድምፃውያን ጋር አብሮ የመሥራት ዕድል አግኝቷል። ብዙም ሳይቆይ ነፍሱ ወደ ምትወደው እግርኳስ በማምራት ከታችኛው ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለረጅም ዓመታት ያህል ታላቁ ክለብ መቻልን አገልጎሎ በህክምና ምክንያት ከጦሩ ቤት ሊወጣ ችሏል።
ከታዳጊ ቡድን እስከ ከዋናው ቡድን ድረስ አብሮት የተጫወተው የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) ስለታሪኬ ምስክርነቱን እንዲህ ሰጥቶናል። ” ታሪኬን ያወቅኩት ምድር ጦር ሙዚቃ ቤት ስገባ ነው። በምድር ጦር በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚሰጠው አገልግሎቶች በጣም የሚታወቅ ሰው ነበር። በኃላም በእግርኳሱ ጦሩ ቤት የነበሩ ትላልቅ ተጫዋቾች በተለያዩ ምክንያቶች ቡድኑን ሲለቁ ከታችኛው ቡድን ወደ ዋናው ቡድን አብረን አድገን መጫወት ችለናል። በጣም ኳስ የሚችል ፣ ቀልደኛ ሳቂታ ተጫዋች መልካም ሰው ነበር። በጣም ታሪክ የሚያቅ የብዙዎቹ የማይታወቁ የቀድሞ ተጫዋቾችን ታሪካቸውን ፈልፍሎ የሚያወጣ ትልቅ ባለሙያ ነው። ረጅም ጊዜ እርሱም በስራ እኔም በስራ ምክንያት ሳንገናኝ ቆይተናል። መሞቱን አሁን ደውለው ሲነግሩኝ በጣም ነው ያዘንኩት እውነት በጣም ደንግጫለው። ፈጣሪ ነፍሱን ይማር” በማለት ተናግሯል።
የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ታሪኬ ከምድር ጦር በኋላ ለሜታ አምቦ ፣ ለራስ ሆቴል፣ ለምድር ባቡር ተጫውቶ አሳልፏል። ከእግርኳሱ ህይወት ከተገለለ በኃላ ሙሉ ለሙሉ በልጅነት ዕድሜው ይሰማቸው ያያቸው የነበሩትን በተለይ የስልሳዎቹ እና የሰባዎቹ የእግርኳስ ታሪኮችን በጊዜው ለነበሩት አሁን ላሉት እና ለሚመጣው ትውልድ ለማሻገር ታሪኮችን የመፃፍ የማስተላለፍ ስራዎችን ህይወቱ እስኪያልፍ ድረስ ሳይሰስት ሲሰራ ቆይቷል።
ጋዜጠኝነት በደሙ ውስጥ እንዳለ የሚናገረው ታሪኬ በህትመቱ ሚዲያ ካምቦሎጆ ጋዜጣን ከተመሰረተበት እስከቆመበት ጊዜ በአዘጋጅነት እንዲሁም ወደ አምስት የሚጠጉ የተለያዩ ኢትዮጵያ የተካፈለችባቸውን ሆነ ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫዎችን የሚዳስሱ መፅሔቶችን ሰድሮ በማዘጋጀት ለህትመት አብቅቷል። በማስከተል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ በመሆን የተለያዩ መፅሄቶችን ከማዘጋጀቱ ባሻገር ልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ፣ የምንጊዜም ጊዮርጊስ የሬዲዮ ፕሮግራም አገልግሏል።
የስራ ባልደረባው በመሆን ታሪኬን በቅርብ ዕርቀት ከሚያውቁት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ የህዝብ ግኑኝነት አባል ካሳሁን ደርበው (ካስትሮ) ስለ ታሪኬ ይሄን ብሎናል። ” ታሪኬ ወደ ጊዮርጊስ ቤት በተለይ በአገልግሎቱ እንድመጣ ትልቁን አስተዋፆኦ ያደረገልኝ ሰው ነው። የፅናት ፣ የትዕግስት የትህትና ምሳሌ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስን ታሪክ ከፍ አድርጎ ለትውልዱ ተማስተላለፍ መፅሄቶችን ጋዜጦችን የተለያዮ ክብረ በዓላቶችን በጫንቃው ተሸክሞ ይሰራ የነበረ ደከመኝ የማያቅ እስከ መጨረሻው ታሞ እስኪቀመጥ ድረስ በፍፁም ጥንካሬ ይሰራ የነበረ ባለሙያ ነበር። እጅግ በጣም ለሙያው ታማኝ በመረጃ ሙሉ የሆነ በመረጃ የሚያምን ሰው ነው። ከዕራሱ አልፎ ለብዙ ሰዎች፣ ባለሙያዎች ታሪክ አዋቂ ሆኖ የግብአት ምንጭ ነበር። ለእኔ ተምሳሌቴ የነበረ ብዙ ነገሮችን ያካፈለኝ በተለይ በመረጃ ሙሉ ሆኖ መገኘት እና መረጃን አለመናቅ እንደሚገባ ያስተማረኝ ሁልጊዜም የሚመክረኝ የሚያበረታኝ ወንድም ጓደኛ አባት የሆነ ሰው ነበር። በተለይ እኔ ነገ ባልኖር ብሎ ያለፉ ታሪኮች እንዳይረሱ ታሪክ እንዳይጎድል መቅረፀ ድምፅ ይዘህ ና በማለት ይነግረኝ የነበረ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ብዙዎች የሚሳሱለት ታሪክ አዋቂ ባለሙያ ነው።” በማለት ይናገራል።
አንድን ታሪክ ካየ ከሰማ እንደማይረሳው ይገልፅ የነበረው ታሪኬ በዚህ ዘመን ለተፈጠሩ የስፖርት ሰዎች ታሪክን ወደኋላ አሻግሩ መረጃ ይሰጥ የነበረ እንደ ስሙ ታሪክ አዋቂ ነበር። ሁሉን ነገሩን ለስፖርት እንደሰጠ የሚታመንለት ታሪኬ ያለፉትን አምስት ዓመታት የስኳር ህመም አጋጥሞት እንደቆየና ሙሉ ለሙሉ ሥራው ላይ ነው ባይባልም በሁሉም ረገድ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አስፈላጊውን የህክምና ወጪ በመሸፈን ሌሎች ነገሮችን በማገዝ ከጎኑ እንደነበረ ይታወቃል። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ዓይኑ ስኳር ህመም ምክንያተረ ማየት ተስኖት እንደነበረ ህመሙ እየጠናበት ሄዶ ስተመጨረሻም በትናትናው ዕለት መንፈቀ ሌሌት ሞት አሸንፎታል።
ታሪኬ በትዳር ህይወት ይኖር የነበረ ቢሆንም ልጅ እንደሌለው ታውቋል። የቀብር ሥነ-ስርዓቱ ነገ 6 ሰዓት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ በአንጋፋው ጋዜጠኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ትመኛለች።