[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከጋናው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሲሰጥ ከብዙሃን መገናኛ ጠንከር ባለ መልኩ የተነሳው የመልበሻ ቤት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ምላሽ ተሰጥቶበታል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከነገ በስትያ ከጋና ጋር ለሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ከሌላው የመግለጫው ክፍል በተለየ የቡድናቸውን መልበሻ ክፍል በተመለከተ ‘ጣልቃ ገብነት አለ’ ስለሚባለው ጉዳይ የቀረበላቸው ጥያቄ እና የሰጡት ምላሽ ደግሞ አነጋጋሪ ነበር። አሠልጣኙ በቅድሚያ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታዩን ዝርዝር ሀሳብ ሰጥተዋል።
“እኔ ልምድ አለኝ ብዬ መናገር የምችል አሰልጣኝ ነኝ። ከዚህ ቀደም ትልልቅ ቡድኖች ላይም ሰርቻለሁ። ቻምፒዮን የሆነ ቡድን ውስጥም ሰርቻለሁ ፤ ደደቢት እና ሲዳማ ቡናም ሰርቻለሁ። ሙያዬም ሆነ መልበሻ ቤቴ ተደፍሮ አያውቅም ፤ ሊደፈርም አይችልም። እንደዚህ ዓይነትም ሰው አላውቅም። ‘ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው’ እንደሚባለው ብዙ ነገሮች ሉባሉ ይችላሉ። የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ኮሚውኒኬሽን ስም ይጠራል ፤ ምክትል ፣ ዋና ፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እያለ ከሚጠራቸው ሰዎች ውጪ እኔ ጋር መልበሻ ቤት የሚገባ ሰው የለም። እኔ ሁለት ዓይን ነው ያለኝ በወቅቱ ትኩረቴ ተጫዋቾቼ ላይ ነው። ከጀርባ ሰዎች መግባት አለመግባታቸውን ላላይ እችላለሁ። በቀጣይ ማየት ያለብኝ ነገር ካለ ግን ለማየት ዝግጁ ነኝ። ነገር ግን ማንም ሰው እዛ ጋር ገብቶ ተሳትፎ ሊያደርግ አይችልም። እስከዛሬ ቡድን ስሰራ የምታወቅበት የራሴ መንገድ አለ። በጣም ሙያዬን የማከብር ፣ ሙያው እንዲከበር የምፈልግ ከዛም አልፎ በዚህ ዓይነት መልኩ ሰዎችን ካየሁ የምኮንን መሆኔ ይታወቃል።”
አሠልጣኙ ከላይ ያስቀመጥነውን ጠቅለል ያለ ሀሳብ ከተናገሩ በኋላ ‘የቡድኑ አባል የሆነ ጋዜጠኛ አለ’ በሚለው ተከታይ ጥያቄ ዙሪያ ደግሞ ይህንን ብለዋል።
“እኔ የቡድን አባል ይዤ የምሄደው ተጫዋቾች እና ምክትል አሰልጣኞቼን ነው ፤ መምረጥ የምችለው። አሁን በተባለው ሁኔታ ግን ያንን ሰው የማምጣት ፣ የመቀነስም ሆነ የመጨመር መብቱ የለኝም። ይሄ ነው ሊታወቅ የሚገባው። ማስረጃዎች ካሉ በማስረጃው መሄድ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ማንም ሰው በፎቶ እንደዚህ ነው እንደዚህ ነው የሚለውን እኔ አላውቅም። ቡድኑን ብዙ ቦታ ይዤ ሄጃለሁ ሞግዚት የምፈልግ ሰው አይደለሁም። ራሴን ጠንቅቄ የማውቅ ሰው ነኝ። ቅድም እንዳልኩት የፌዴሬሽኑ ኮሚውኒኬሽን በጨዋታ ዕለት ከሚጠራቸው ሰዎች ውጪ መልበሻ ቤት ማንም ሰው አይገባም። ምክትል አሰልጣኝ ፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ፣ የሥነ ምግብ ባለመያ በወቅቱ ፣ ቡድን መሪ በወቅቱ ይጠራሉ። ከዚህ ውጪ እስከዛሬ ስሰራ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዳሬሽን ውስጥ ሁለት ዓመቴ ነው። ጣልቃ ገብነት እኔ ጋር የለም።”
በማስከተል ጥያቄው ይበልጥ ወደ ዝርዝር ውስጥ ገብቶ እና ጋዜጠኛውም በስም ተጠቅሶ (አሸናፊ ዘለሌ) ከፊት አሰልጣኙ ከኋላ ሆነው በመልበሻ ክፍል ውስጥ የሚያሳዩ ምስሎች ስለመኖራቸው ተያያዥ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኙ የሚከተለውን ብለው ኃሳባቸውን ቋጭተዋል።
“እኔ ከኋላ እሱ ከፊት ? የቱ ጋር ? እኔ ይህንን አላውቅም። ካለ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ። እዚህ ጋር የመጣው ሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ፤ የሚመለከተው ሰው ነው። የሙያ ጉዳይ ነው። ሙያን አርክሶ መሄድ አይቻልም። የሚነሱት ጥይቄዎች እውነትም ይሁኑ ውሸትም ይሁኑ ግልፅ መውጣት አለባቸው። ግን ይሄንን ቡድን እስካሁን ስመራ በዚህ ጉዳይ አንድም ነገር ተብሎ አይታወቅም። ይህ ጥያቄ ከነበረ መጀመሪያ ማንሳቱ ይቀል ነበር። መልበሻ ቤት ከተገባ ‘መቼ ?’ የሚለውን ነገር ማንሳት ተገቢ ነው። እንደሀገር ነው መስራት ያለብን። እኛ የግለሰቦችን ፍላጎት አናረካም። ሙያ ክቡር ነው። ይሄን የሚያደርግ ሰው ካለ ደግሞ ሙያውን ሽሯል ማለት ነው። በዚህ መታሰብ አለበት። እኔ በማውቀው ጋዜጠኝነት ክብር ነው። ከዛ በተለየ ግን በምትሉት ሁኔታ ነው ለማለት አያስኬድም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የምደራደር ሰው አይደለሁም። መልበሻ ቤት ውስጥ ፍሬው ያወራል ፍሬው ይጨርሳል። ከተጫዋቾቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት እኔ እና ተጫዋቾቼ ናቸው። ከዛ ውጪ ለህክምና ባለሙያዎች አምስት ስድስት ደቂቃ ይሰጣቸዋል ፤ ይሰራሉ። የምጀምረውም እኔ ነኝ የምጨርስወም እኔ ነኝ ሲጀመር ፣ ዕረፍት ላይም ሲያልቅም ፤ ይሄ ሊታወቅ ይገባል። እንደዚህ ዓይነት ነገር ካለ ግን በግልፅ መውጣት አለበት። አሰልጣኝነትም መያ ነው መከበር አለበት ጋዜጠኝነትም ሙያ ነው መከበር አለበት።”