[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በሦስት ጨዋታዎች ሲጀምር ንግድ ባንከ እና ሻሸመኔ ድል ሲቀናቸው ጋሞ ጨንቻ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል።
የረፋዱ የመጀመርያ የነበረው የንግድ ባንክ እና የባቱ ከተማ ጨዋታ በንግድ ባንክ 2–1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሁለቱም ጥንቃቄ ላይ መሠረት ያደረገ አጨዋወት በመከተላቸው እንቅስቃሴያቸው መሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ የቀረ ቢሆንም በንግድ ባንኮች በኩል አደም አባስ በተደጋጋሚ በግል ጥረቱ ከመስመር እየተነሳ ወደ አደጋ ክልል ላይ የሚያሻግራቸው ኳሶች ሲታዩ የሚጠቀምባቸው ተጫዋች በማጣት ግን ይባክኑ ነበር። በአንፃሩ ባቱዎች በአማካይ ተጫዋቹ ዳዊት አማካኝነት በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ወደፊት ቢሄዱም አጥቂዎቹ መረጋጋት ተስኗቸው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ታይተዋል። በዚህ ሂደት የቀጠለው ጨዋታ 30ኛው ደቂቃ ከመሐል የተጣለለትን ኳስ ፈጣኑ ተስፋኛ አጥቂ አደም አባስ ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ፊት በሚሄድበት ወቅት የባቱ ከተማው ግብ ጠባቂ መስፍን ሙዜ ግማሽ ጨረቃው ላይ ጥፋት በመስራቱ በቀጥታ በቀይ ካርድ ወጥቷል። ውሳኔውን በመቃወም የባቱ ተጫዋቾች ከፈጠሩት ክርክር በኋላ ጨዋታው ወደ ከውሀ ዕረፍት መልስ ሲቀጥል የተሰጠውን ቅጣት ምት ሚካኤል ዳኛቸው በቀጥታ ወደ ጎልነት ቀይሮት ንግድ ባንክን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ከቆመ ኳስ የተሻገረውን ኳስ የባቱዎች ተከላካይ ስንታየሁ ኡታ ከሜዳ ክፍሉ ለማራቅ አስቦ በግንባሩ ጨርርፎ በራሱ ጎል ላይ አስቆጥሮ የንግድ ባንክን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
ከዕረፍት መልስ በቁጥር አንሰው ይጫወቱ የነበሩት ባቱዎች ምንም እንኳን ግልፅ የማግባት የጎል አጋጣሚ አይፍጠሩ እንጂ በተሻለ ጫና ፈጥረው ተንቀሳቅሰዋል። ይህ የባቱ እንቅስቃሴ ያሰጋቸው የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ውጤቱን ለማስጠበቅ የተከላካይ ቁጥር ጨምረው ቢጫወቱም በ66ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ያሬድ ወንድማገኝ ጎል አስቆጥሮ ንግድ ባንኮችን ውጥረት ውስጥ ሲከት ባቱዎችን አነቃቅቷቸዋል። ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል ያልተደራጀ ኳስ ቢሆንም ባቱዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት በመሄድ አቻ የሚሆኑበትን ጎል ፍለጋ ሲታትሩ ቢቆዩም ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ሳያገኙ ቀርተዋል። ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ጎል ለማግኘት በሚረዳ መልኩ በአንድ አጋጣሚ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ደሳለኝ ወርቁ ነፃ ኳስ ከቀኝ ቢጥልላቸውም ኢሳያስ ታደለ እና ሰለሞን ጌታቸው ሲገባበዙ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውም በቀሩት ደቂቃዎች የተለየ ነገር ሳያስመለክት በንግድ ባንክ 2–1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ከመሪዎቹ ያለውን ነጥብ ሲያጠብ ባቱዎች ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ አድርጓቸዋል።
በስምንት ሰዓት በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ አምቦ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ ተገናኝተው ሻሸመኔዎች በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል 2–1 አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ ጎል መቆጠር የጀመረው በጊዜ ነበር። ሻሸመኔዎች ከሳጥን ውጪ ለቀኝ መስመር ያጋደለ ቅጣት ምትን አግኝተው ቦና ዓሊ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት አምቦዎች ጎል ከተቆጠረባቸው ከሁለት ደቂቃ በኋላ ግሩም ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጪ አስቆጥሮ አምቦዎችን አቻ አድርጓል። ከውሀ ዕረፍት በኋላ የሻሸመኔው አጥቂ ቦና ዓሊ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ሮብሰን በዳኔ በግንባር ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ብዙም ሳይቆይ በመስመር አጥቂው ተጠቃሽ ሲሆን አሸናፊ ጥሩነህ አማካኝነት ሌላ የማግባት ዕድል ሻሸመኔዎች ቢፈጥሩም የአምቦው ግብ ጠባቂው ነጋ ከበደ አድኖባቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽም የሻሸመኔዎች የማጥቃት ሂደት ቀጥሎ በ50ኛው ደቂቃ የመስመር አጥቂ አሸናፊ በጥሩ መንገድ ወደ ፊት ሄዶ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጎል አገባ ሲባል ግብጠባቂው በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት ሻሸመኔን መሪ የምታደርግ አጋጣሚ ነበረች። ከዚህች ሙከራ በኋላ ጨዋታው እምብዛም ሳቢ ሳይሆን እየተቆራረጠ ቀጥሎ ባሳለፍነው 13ኛው ሳምንት ሻሸመኔዎች ገላን ከተማን በመጨረሻው ደቂቃ ባሸነፉበት አኳኋን ዛሬም የዳኛው የጨዋታ ማሳረጊያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት 90+3 ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ወደ ፊት ጥሩ አጥቂ እንደሚሆን እየተመለከትነው የምንገኛው ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ሲተፋው በኳሱ የቅርብ ርቀት የነበረው ተቀይሮ የገባው ምስጋና ሚልኪያስ ወደ ጎልነት በመቀየር ሻሸመኔዎች ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል። በገላንም በዛሬውም ጨዋታ ሻሸመኔዎች ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ ዋናው አሰልጣኝ ኤፍሬም አለምነህ ቅያሪ ጉልህ ድርሻ ነበረው። ውጤቱን ተከትሎ ሻሸመኔ ደረጃውን ሲያሻሸል አምቦዎች ባሉበት ደረጃ ለመቆየት ተገደዋል።
በርከት ያለ ቁጥር ያለው ተመልካች በታደመበት የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በጋሞ ጨንቻ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተካሂዶ አንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በታክቲክ በታጠረው ጨዋታ በጋሞ ጨንቻ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኤሌክትሪኮች ጎል የሚያስቆጥሩበት የማጥያ መንገድ አጥተው ተቸግረው ውለዋል። በዚህም መነሻነት በሁለቱም በኩል ግልፅ የጎል አጋጣሚዎችን ለመመለክት ከዕረፍት መልስን መጠበቅ ግድ ሆኗል። ጋሞዎች ቁጥራቸውን በራሳቸው የሜዳ ክፍል አብዝተው ሲከላከሉ የነበረ በመሆኑ በመልሶ ማጥቃት 59ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከማል አቶም አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ያዳነበት የጨዋታው የመጀመርያ ግልፅ የጎል ዕድላቸው ነበር። ኤሌክትሪኮች የጋሞን የመከላከል ጥንካሬን አልፈው ጎል ለማስቆጠር በተቸገሩበት በዚህ ሁኔታ ከቆመ ኳስ የተጣለውን ኪሩበሌ ፍቅረማርቆስ ጨርፎ በመምታት ጋሞዎችን ቀዳሚ አድርጓል።
ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት ኃይላቸውን ለማብዛት ጥረት አድርገዋል። በ75ኛው ደቂቃ አዳርጋቸው ይላቅ በግንባሩ ከመሬት ጋር አንጥሮ የገጨው ኳስ ለጥቂት ቋሚውን ታኮ ሲወጣ ሌላው 85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው በአስደናቂ ሁኔታ የመታውን የቅጣት ምት ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ጨዋታው በጋሞ ጨንቻ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ሲባል አራት ደቂቃ ጭማሪ ታይቶ በ93ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት በተላከ ኳስ በቁመቱ ዘለግ ያለው አብነት ደምሴ ጎል አስቆጥሮ የምድቡን መሪ ከሽንፈት ታድጎ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።