[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ነገ ወሳኝ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ረፋድ ላይ ከውኗል።
በኮስታሪካ ለሚደረገው የ2022 የሴቶች የ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በሚደረገው ማጣሪያ አንድ የደርሶ መልስ ጨዋታ የቀረው የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ቡድን ነገ ከጋና አቻው ጋር ቀዳሚውን ጨዋታ ያደርጋል።
ከታንዛኒያው ድል በኋላ ለቀረው የ180 ደቂቃዎች ፍልሚያ ልምምዱን ማካሄድ የጀመረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ዛሬም ቦሌ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመለማመጃ ሜዳ ላይ ከጋናው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ የሆነውን የልምምድ መርሐ ግብር ከረፋድ 04:30 ጀምሮ አድርጓል።
ለጨዋታው አንድ ቀን ብቻ እንደመቅረቱ ቀለል ያለ ልምምድ የከወነው ቡድኑ በተጫዋቾች መጫወቻ ቦታ የተከፋፈለ እንዲሁም ወደ ግብ ኳሶችን መምታት ላይ የታኮሩ ልምምዶችን ከውኗል።
ከትናንት በስትያ የብሔራዊ በድኑ ዋና አሰልጣኝ በመግለጫቸው ላይ በጉዳት ላይ እንደሆኑ ከገለጿቸው ተጫዋቾች መከከል የማጣሪያው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነችው አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ በጉዳት በልምምዱ ላይ ካለመኖሯ በቀር ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የሰነበቱት ቀሪ ተጫዋቾችን ጨምሮ ቀሪው ስብስብ በልምምዱ ላይ ተካፍሏል።
ከልምምድ መርሐ ግቡር መጠናቀቅ በኋላ በ1990ዎቹ በሙገር ሲሚንቶ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቶ ያሳለፈው እንዲሁም በአርጀንቲናው ዓለም ወጣቶች ዋንጫ ላይ በተሳተፈው ዝነኛው ወጣት ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የነበረው ደያስ አዱኛ የቡድኑን ተጨዋቾች ልምዱን በመካፈል አበረታቷል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዉ ቡድን ከጋና አቻው ጋር የሚያደርገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ነገ 10:00 ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚያደርግ ይጠበቃል።