በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ለሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ከተጫዋቾች የደመወዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ልምምድ እስካሁን አልጀመሩም፡፡
በ2014 ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የአስራ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎችን ደካማ በሆነ የውጤት ጉዞ ያገባደዱት እና በደረጃ ሰንጠረዡ በወራጅ ቀጠናው 15ኛ እና 16ኛ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት ጅማ አባጅፋር እና ሰበታ ከተማ ለሁለተኛው ዙር የሊጉ መርሀ ግብር ቅድመ ዝግጅት እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አልጀመሩም፡፡ በመጀመሪያው ዙር የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ባስመዘገበው ውጤት የተነሳ ግርጌው ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ሰበታ ከተማ የካቲት 29 ዝግጅት ለመጀመር ለተጫዋቾቹ ጥሪን አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በጥሪው መሠረት በተባለው ዕለት ልምምድ ሳይጀምሩ ዛሬ አስራ አንደኛ ቀናቸው ላይ ይገኛሉ፡፡
ዓለምገና በሚገኘው መገርሳ ባቱ ሆቴል የክለቡ ተጫዋቾች እስከ አሁን ተቀምጠው የሚገኙ ሲሆን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ “የ2013 ደመወዝ የሰባት ወር የዘንድሮው ደግሞ የሁለት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበን መጥቶ መልስ የሚሰጠን የለም አሁንም በሆቴል ውስጥ ተቀምጠን እንገኛለን ክለቡ ካልሆነ እንዲለቀን ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም”ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
የተጫዋቾቹን ጥያቄ ተንተርሰን ምላሽ ለማግኘት ብለን የክለቡን ስራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳን ጠይቀን በምላሻቸው “አሰልጣኙ ዕቅድ አውጥቶ ልምምድ ጀምሩ የሚል አቅጣጫን አስቀምጦ ነበር። ተጫዋቹ ግን ደመወዝ ካልተከፈለን አንሰራም በማለታቸው ዝግጅት አልጀመሩም፡፡ እኛ ደግሞ ውድድር እየቀረበ ስለሆነ እየሰራችሁ ጠይቁ ብለናቸዋል፡፡ በክለቡ ላይ የበጀት እጥረት ችግር ገጥሞናል እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የክለቡ ሰራተኞችም ጭምር በዚህ እየተቸገሩ ነው፡፡ ተጨማሪ በጀት እስኪመጣ እየጠበቅን ነው ያለነው፤ እኛ ጀምሩ ብለናል ውድድር ስለቀረበ ተጫዋቾቹ ግን አንሰራም ካልተከፈለን ብለውናል። ነገሩን ለማስተካከል እኛም እየሰራን እንገኛለን።” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾችም ወደ ዝግጅት አልገቡም፡፡ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ላይ ለተጫዋቾቹ ክለቡ ጥሪ ቢያቀርብም የክለቡ ተጫዋቾች ግን እስከ አሁን ጅማ ገብተው አልተሰባሰቡም፡፡ ጥሪ ከቀረበላቸው አምስተኛ ቀናቸው ላይ የሚገኙት ጅማዎች የአራት ወራት ደመወዝ ለክለቡ ተጫዋቾች ተፈፃሚ ስላልሆነላቸው ልምምድ ላለመግባት ከውሳኔ ላይ ደርሰው ይሄን ዜና እስካጠናከርንበት የዛሬዋ ዕለት ድረስ ዝግጅት አልጀመሩም፡፡
በያዝነው ወር መጋቢት 21 ለሚጀምረው የሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ወደ ልምምድ ያልገቡት ሁለቱ ክለቦች የየተጫዋቾቹ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ መቼ ወደ ዝግጅት ይገባሉ ? የሚለውን ጉዳይ ተከታትለን ወደ እናንተ የምናደርስላችሁ ይሆናል፡፡