[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት የቀረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ባቱ ከተማ ድል ሲቀናው ሀላባ እና ሻሸመኔ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
በአፄ ቴድሮዎስ ስታዲየም በተካሄደው የስምንት ሰዓት ጨዋታ ሀላባ ከተማን ከሻሸመኔ ከተማ አገናኝቶ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በክብር እንግድነት ተገኝተው ከተጫዋቾቹ ጋር በመተዋወቅ በህብረት ፎቶ በመነሳት ያስጀመሩት ጨዋታ በመጀመርያው አስር ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ እያስመለከተን ቆይቶ በ14ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቱ ሻሸመኔዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የተገኘውን አጋጣሚም አጥቂው ቦና ቢመታውም የሀላባው ግብ ጠባቂ ንጉሴ ሙልጌታ አድኖት ቡድኑን ከመመራት ታድጓል።
መከላከልን መሠረት አድርገው በሚገኙ ኳሶች ፈጣን የሆኑትን የመስመር አጥቂዎችን መዓከል በማድረግ ወደ ማጥቃት ሽግግር የሚገቡት ሀላባዎች በዚህ ሂደት በ20ኛው ደቂቃ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። የመስመር አጥቂው አቡሽ ደርቤ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ እየገፋ አጥብቦ በመግባ በጥሩ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ማናዬ ፋንቱ አቀብሎት ተጫዋቹ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። የአጨራረስ አቅማቸው ከፍ ያሉ የፊት አጥቂዎቻቸው የተቀዛቀዙባቸው ሻሸመኔዎች ከቆሙ ኳሶች በተደጋጋሚ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ በተደጋጋሚ የሀላባ የሜዳ ክፍል በመድረስ ተጭነው ጎል ፍለጋ የተያያዙት ሻሸመኔዎች ከሳጥን ውጭ አንበሉ ጌታለም ማሙዬ በጥሩ ሁኔታ መቶት ግብ ጠባቂው ያዳነው ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ የቀጠሉት ሻሸመኔዎች በ66ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ በዕለቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደር የነበረው አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥን ውጭ ግብ ጠባቂውን አቁሞ ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው መሪ ለመሆን ማጥቃታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሻሸመኔዎች ተስፈኛው አጥቂ ቦና ዓሊ እና ወጋየሁ ቡርቃ ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ጨዋታውም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን አንድ አቻ ተጠናቋል።
የአስር ሰዓት መርሐ-ግብር የነበረው የባቱ ከተማ እና አምቦ ከተማ ጨዋታ በባቱ ከታማ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
እንደ መጀመርያው ጨዋታ ሁሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ይህንንም ጨዋታ ከተጫዋቾቹ ጋር በመተዋወቅ አስጀምረውታል። ተመጣጣኝ ፉክክር ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ የጎል ማግባት ሙከራ መመልከት የጀመርነው ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። በ5ኛው ደቂቃ የአምቦ ከተማ ተከላካዮች ኳሱን መስርተው ለመጀመር አስበው በቅብብሎሽ መሐል የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎ የባቱው አጥቂ ሂኒካ ሄይ አግኝቶ ወደ ጎል ቢመታውም ግብ ጠባቂው አድኖበታል።
ብዙም ሳይቆይ ከሳጥን ውጭ ለባቱ ከተማ የተሰጠውን ቅጣት ምት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን አልፎም ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የምናቀው ጌታሰጠኝ ሸዋ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በተመሳሳይ መንገድ በ22ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ጠርዝ ሌላ ቅጣት ምት ያገኙት ባቱዎች ኳሱን በቀጥታ ዳዊት ቹቹ መቶት የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ ወደፊት በመሄድ ክንዳዓለም ፍቃዱ ያሻገረለትን ያሬድ ወንድማገኝ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ አምቦዎች በተሻለ ወደ ጎል በመድረስ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻለ ቢሆኑም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ውጤቱን ለማስጠበቅ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ባቱዎች ቢጥሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። አምቦዎች ምንም እንኳን በቀጣዩ ዓመት በከፍተኛ ሊግ የመቆየት ዕድላቸው የከተመ ቢሆንም ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን መሆኑን ተከትሎ በስታዲየም የተገኘው ተመልካች አድናቆቱን ቸሮታል። ጨዋታውም ከዕረፍት በፊት ባቱዎች ባስቆጠሩት ሁለት ጎሎች ተጠናቋል።