[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በተመሳሳይ ሰዓት የተካሄዱት ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን ሲያበስሩ ነገሌ አርሲ ደግሞ ድል ቀንቶታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ገላን ከተማ
በፔዳ ካምፓስ የተካሄደው ይህ ጨዋታ ውጥረት በተሞላበት እንቅስቃሴ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመርያውን አስራ አምስት ደቂቃዎች እንደነበራቸው ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ንግድ ባንኮች ገና በ8ኛው ደቂቃ ነበር ቀዳሚ መሆን የቻሉት። የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው አዳም አባስ ከግራ መስመር ጠርዝ ሰብሮ በመግባት መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ሌላኛው የመስመር አጥቂ ወሰኑ ዓሊ በፍጥነት በመድረስ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። በተወሰነ መልኩ የማጥቃት ፍላጎታቸው ከጎሉ መቆጠር በኋላ የጨመረ ይመስል የነበረው ንግድ ባንኮች የኃላ የኃላ እንቅስቃሴያቸው ተቆርጦ ኳሶቻቸው እየባከኑ ወደ ግብ ክልላቸው አፈግፍገው መጫወትን መርጠዋል። ይህን ተከትሎ ጨዋታው ወደ ገላን የበላይነት አድልቶ እስከ ዕረፍት መዳረሻ ዘልቋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ኢዮኤል ሳሙኤል እና አፍቅሮት ሰለሞን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ የቀሩበት አስቆጪ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ መንገድ የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ገላኖች በ60ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በሱፍቃድ ነጋሽ አግኝቶ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። የጨዋታው መጠናቀቂያ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ገላኖች መሪ የሚያደርጋቸውን አጋጠሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም ኢዮኤል ሳሙኤል አምክኗል። በተቃራኒው ባንኮች በረጃጅም ኳሶች የገላን ግብ ሲፈትሹ ቢቆዮም ብዙም ስኬታማ አላደረጋቸውም። ሆኖም በተጨማሪ ደቂቃ የተገኘውን የማዕዘን ምት ዮሐንስ ኪሮስ በግንባር በመግጨት ወደ ጎል የመታው ኳስ ገባ ሲባል የገላኑ ግብ ጠባቂ ውብሸት ጭላሎ እንደምንም የያዘበት ለንግድ ባንኮች አስቆጪ ዕድል ነበር። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ጌዲኦ ዲላ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተ ቢሆንም ኤሌክትሪክ ወደ ጎል በመድረስ የተሻለ ነበር። አጥቂው አቤል ሀብታሞ በጥሩ መንገድ አቀብሎት አንበሉ እንዳለ ዘውገ ያልተጠቀመበት ኤሌክትሪኮች ቀዳሚ የሚሆኑበት ዕድል ነበር። ግልፅ የማግባት ዕድሎችን መፍጠር አይቻሉ እንጂ ጌዲዮዎች ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርገው ቆይተዋል። የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመግባት አጋጣሚያቸውን ላለማጣት ጫና ውስጥ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በ35ኛው ደቂቃ ጎል በማስቆጠራቸው ተረጋግተዋል። በዚህም ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ እንዳርጋቸው ይልቃል በግንባር በመግጨት ግሩም ጎል አስቆጥሩ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ፍላጎት ተሳክቶላቸው በ61ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። በሁለተኛው ዙር ከጅማ አባ ጅፋር ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው ወጣቱ አጥቂ አቤል ሀብታሙ ከማዕዘን ምት የተላከው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
በቀሩት ደቂቃዎች የምንያህል ተሾመ ቡድን የመምራት አቅም የታየበት ሲሆን ከእርሱ መነሻነት የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል አድርሰው ከመጣደፍ ጋር ተያይዞ ይባክኑ የነበሩ ኳሶች የበለጠ ጨዋታውን ለመግደል የነበራቸውን አጋጣሚ አሳጥቷቸዋል። በስተመጨረሻም ጨዋታውም በኤሌክትሪክ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ ጨዋታ እየቀረው ማደጉን አረጋግጧል።
ነገሌ አርሲ ከ ጋሞ ጨንቻ
በሁለቱም ቡድኖች በኩል የነበረው የመጫወት ፍላጎት ጥሩ የነበረ ቢሆንም የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የአቅም ውስንነት በጨዋታው ታይቷል። ይህን ተከትሎ የመጀመርያው አጋማሽ የጠራ የጎል ሙከራ ሳንመለከትበት ተገባዷል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተሻለ ሙከራዎችን ሲደረጉ ቆቆይተዋል።
ጋሞ ጨንቻዎች ያገኙትን ከሳጥን ውጭ ቅጣት ምት አሸናፊ ኃ/ማርያም በጥሩ ሁኔታ መቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ እና በድጋሚ የተመለሰውን ኳስ አጥቂው ማቲዮስ ኤልያብ አግኝቶ በመቀስ ምት መቶት በተመሳሳይ ሁኔታ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው ሁነት በጣም የምታስቆጭ ሆና አልፋለች። በአንፃሩ ነገሌዎች ተቀይሮ በገባው ወሳኝ አጥቂያቸው ብሩክ ብፁአምላክ አማካኝነት የፈጠሩት ዕድል ጥሩ ነበር። ዕድለኛ ያልነበሩት ጋሞዎች ከሳጥን ውጭ ሌላ ቅጣት ምት አግኝተው አስቻለው ኡታ ቢመታውም አግዳሚ መልሶባቸዋል። ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቀቀ ሲባል በተጨማሪ ደቂቃ ነገሌ አርሲ በፍቅሩ ጴጥሮስ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።