የአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር መጠናቀቁን ተከትሎ በተከፈተው የዝውውር መስኮት አንድ አጥቂ ያስፈረሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሦስት ተጫዋቾችን የግላቸው ለማድረግ ተቃርበዋል።
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የውድድር አጋማሹ መጠናቀቁን ተከትሎ የተወሰ እረፍት ካደረጉ በኋላ በባህር ዳር ከተማ እና በባቱ ከተማ በመዟዟር ተጫዋቾችን የመልመል ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በተመለከቷቸው ጨዋታዎች ቀልባቸውን የሳቡ ሦስት ተጫዋቾችን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በውሰት ለመውሰድም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል።
ተጫዋቾቹም የተከላካይ አማካዩ አብነት ደምሴ፣ የመስመር አጥቂው ኢብራሂም ከድር እና አጥቂው ፊሊሞን ገ/ፃድቅ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ቡና ለኤሌክትሪክ የውሰት ጥያቄ ደብዳቤ አቅርቧል። ኤሌክትሪክ ጥያቄውን የተቀበለ ቢሆንም የከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ እና የመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የተጫዋቾቹን አገልግሎት ካገኘ በኋላ በቀጣይ ቅዳሜ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንደሚያቀኑ አመላክቷል።
አጥቂው ፊሊሞን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን ተጫውቶ ያለፈ ሲሆን በማስከተል በገላን ከተማ ከተጫወተ በኋላ ዘንድሮ አጋማሽ ላይ ለኢትዮ ኤሌክትሪክን ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ሰበታ ከተማን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደጉ ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበረው የመስመር አጥቂው ኢብራሂም ከድር አከራካሪ በሆነ መንገድ ዘንድሮ ከሰበታ ከተማ ጋር ከተለያየ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር መልካም የሚባል ጊዜን አሳልፏል።
አብነት ደምሴ ደግሞ በፌደራል ፓሊስ እና በወላይታ ድቻ ቆይታ ያደረገ ሲሆን ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማምራት ቡድኑን ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት እና በማጥቃትም እንዲሁም ጎል በማስቆጠርም ጥሩ ሚና ነበረው።