“ጣፎ እና እኔ እጅ እና ጓንት ነን ማለት ይቻላል” ልደቱ ለማ
“ራሴን አዘጋጅቼ የተሻለ ነገር አሳያለሁ ብዬ ገምታለሁ” ፋሲል አስማማው
ለገጣፎ ለገዳዲን ከአንደኛ ሊጉ እስከ ከከፍተኛ ሊጉ በወጥነት ማገልገል ችሏል፡፡ በተደጋጋሚ የከፍተኛ ሊግ ቀዳሚው ግብ አስቆጣሪ እየሆነ ስሙ በጉልህ ይጠራል፡፡ በስሑል ሽረ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ቆይታም ነበረው። ዘንድሮ ለገጣፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲገባ ግብ አምራች በመሆን ለክለቡ ስኬት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ፤ አጥቂው ልደቱ ለማ።
ሌላኛው አጥቂ ደግሞ ከመተሀራ ተገኝቶ ለመከላከያ ፣ ጅማ አባ ቡና ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ውስጥ በመጫወት አሳልፏል፡፡ በለገጣፎ በነበረው የተሳካ ጊዜ መነሻነት ወደ ፋሲል ከነማ ተጉዞ የመጫወት ዕድሉም ገጥሞታል። ጉዳት ከሚበረታባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ቢሆንም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በድጋሚ ወደ ለገጣፎ ተመልሶ በወጥ አቋሙ ክለቡን ለፕሪምየር ሊግ አብቅቷል ፤ አጥቂው ፋሲል አስማማው፡፡
ለገጣፎ ለገዳዲ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ተከትሎ ሁለቱ አጥቂዎች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
ልደቱ ለማ…
የውድድር ዓመት ጉዟችሁ ምን ይመስላል ?
“እግዚአብሔር ይመስገን የዘንድሮው የውድድር ዘመን በጣም አሪፍ ነበር ፤ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም በክለቡ በኩል። የሱፐር ሊግ ነገር ቢሆንም በእግዚአብሔር ፍቃድ አንድ ሆነን በፍቅር ተሳስረን ከኮቺንግ ስታፍ ጋር በመሆን በሰራነው ሥራ ቡድኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማሳደግ በቅተናል፡፡
በጎል አስቆጣሪነት ከክለቡ ጋር በተደጋጋሚ ዓመታት ስምህ ሲነሳ አሳልፈሀል። ይሄ ድል ከዚህ አንፃር ለአንተ ምን ትርጉም አለው ?
“አዎ በገጣፎ ለገዳዲ ቤት ከብሔራዊ ሊግ ጀምሬ ነው የተጫወትኩት። እስከ አሁን በተጫወትኩበት ወቅት ሁሉ የክለቡ ኮከብ ጎል አግቢ ነኝ። በአጠቃላይ የክለቡ ግብ አግቢ ነኝ። በ2012 ኮከብ ጎል አግቢነትን እየመራው ነው በኮቪድ ምክንያት የተቋረጠው። አሁንም ዘንድሮም ኮከብ ጎል አግቢ ሆኜ ነው የቡድኑም በውድድሩ ላይ አጠቃላይ አግቢ በመሆን ነው የጨረስኩት፡፡ ብሔራዊ ሊግ ለለገጣፎ የመጀመሪያ ጨዋታ ሳደርግ ጎል አግብቼ ነበር ፤ ዋንጫ በልተን ስናድግም የመጨረሻውን ጎል 1-0 ስናሸንፍ አግብቼ ጨረስኩ። በዘንደሮውም ዓመት ያ ታሪክ ተደግሞ ስልጤ ወራቤ ላይ የመጀመሪያውን የሱፐር ሊግ ጎል እኔ ነበርኩ ያገባሁት። እግዚአብሔር ፈቅዶ አሁን የመጨረሻ ጨዋታን ከሰንዳፋ በኬ ጋር ስናደርግ 4-0 ስናሸንፍ አራተኛውን ጎል ማሳረጊያዋን እኔ ነበርኩ ያገባሁት። ነገሮች ለእኔ ያማሩ ናቸው ጣፎ እና እኔ እጅ እና ጓንት ነን ማለት ይቻላል፡፡በጣም የተሳሰረ ነገር ነው ያለኝ ደስ የሚል ነገር ነው ይሄ፡፡
በከፍተኛ ሊግ በለገጣፎ ቆይተሀል። በፕሪምየር ሊጉ ግን ባህር ዳር ገብተህ ጎልተህ መውጣት አልቻልክም ነበር። አሁን ደግሞ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመጫወት ዕድሉን አግኝተሀል ፤ የያኔው ድክመትህን አሁን በሊጉ ላይ አሻሽዬ እገኛለሁ ብለህ ታስባለህ ?
“በመጀመሪያ ባህር ዳር ከመግባቴ በፊት 2010 በሱፐር ሊጉ ሽረ እንዳስላሌ ነበር የሄድኩት። ሽሬን የቡድኑ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኜ በአጠቃላይ በ15 ጎል የከፍተኛ ሊጉም አግቢ ሆኜ ጨረስኩ። ከዛም በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለክለቡ አምስት ጎል ነበር ያገባሁት። በሽሬ ታሪክ የመጀመሪያ ጎል አስቆጣሪም እኔ ነኝ። የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀት በአምስት ጎል እኔ ነበርኩ የምመራው። እንዳልከው ከክለቡ ጋር ተለያይቼ ወደ ባህር ዳር ሄድኩ። ግማሽ ዓመትን ትንሽ ባህር ዳር የነበሩ ልጆች ስለነበሩ እኔ አዲስ በመሆኔ ዕድል በበቂ ሁኔታ አልተሰጠኝም ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ደግሞ ቁጭ ብዬ ደመወዝ ብቻ መብላት ስላልፈለኩ ራሴን ማሳየትም ስለነበረብኝ ባህር ዳርን በስምምነት ለቅቄ ድጋሚ 2012 ላይ ወደ ለገጣፎ ተመልሻለሁ። አንድ ተጫዋች ሲጫወት ነው ራሱን የሚያሳየው ፤ ቁጭ ስትል አቅምህን ማሳየት አትችልም። በመሆኑም ወደ ጣፎ ተመልሼ ራሴን በትልቅ ደረጃ ለማሳየት ወርጄ ለመጫወት መርጬ በወቅቱ ክለቡን ተቀላቀልኩ፡፡
ይህ ስኬት ሊመጣ የቻለው ቡድኑ ውስጥ ምን የተለየ ነገር ቢኖር ነው ?
“የመሳካቱ ምስጥር ብዬ የማስበው ከዚህ በፊት ብዙ ጫናዎች ነበሩ። በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ስትጫወት ትንሽ ጫናዎች አሉ። አሁን ላይ ግን እንደ ቶርናመንት ስለሆነ የሚታይም ነገር ስለሆነ ማንም የሚያሳቅቅ ነገር የለም። አሁን ለምሳሌ በሰው ሜዳ ስትጫወት የዳኛም ጭምር ተፅእኖ ይኖርበታል፡፡ አሁን ግን ከምንም ነፃ ሆኖ የትኛውም ቡድን በነፃነት ነው የሚጫወተው። ያ ሲሆን ደግሞ ታሸንፋለህ ፤ ያ ነው አንዱም ስኬት፡፡ በዚህ አጋጣሚ የለገጣፎ እና የባህር ዳር ደጋፊዎች ማህበርን ማመስገን እፈልጋለሁ።”
ፋሲል አስማማው…
ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጋችሁበት የውድድር ዓመቱ ጉዞ በአንተ ዕይታ እንዴት ትገልፀዋለህ ?
“እስከ ዛሬም ጣፎ እንደሚታወቀው ለዋንጫ ሲፎካከር ነበር። እኔ አራት ዓመት ነው የቆየሁት። በአጠቃላይ እስከ ዛሬ ብዙ ታግለን ነበር። ግን ዘንድሮ በጣም ፍቅር እና አላማ ነበረን ፤ የመጡትም ልጆች ወጣቶች ነበሩ። በአብዛኛው ያ ይመስለኛል የነበረን ፍቅር ነው ለዚህ ያበቃን እና የተለያዩ ችግሮች ነበሩ እነሱን ተቋቁመን እዚህ ደርሰናል፡፡ ለእኔ ደስ የሚል ዓመት ነው፡፡
መከላከያ እያለህ ጉዳት ገጥሞህ ነበር ፤ ከጉዳት መልስ በለገጣፎ በተለየ ሁኔታ በተከታታይ ዓመታት በወጥነት ተጫውተሀል ፤ ከጉዳቱ በኋላ ያለህን ነገር እንዴት ትገልፀዋለህ ?
“እግር ኳስን ከመተሀራ ሲ ቡድን ነበር የጀመርኩት በመቀጠል ለዋናው ቡድን ሁለት ዓመት ካገለገልኩኝ በኋላ ነበር ወደ መከላከያ የሄድኩት። በቆይታዬም ጥሩ ተስፋ ነበር። ነገር ግን ሳይታሰብ ጉዳት መጣና ትንሽ ቸግሮኝ ነበር። ከዛ በኋላ ከገጠመኝ ጉዳት አገግሜ የተሻለ ነገር በመስራት ጅማም ተጫወትኩትኝ። ከጉዳቱ በኋላ ከዛ ኮምቦልቻ ነው የሄድኩት በመቀጠል ለገጣፎ ከመጣሁ በኋላ ጥሩ ነገርን በመስራት ወደ ፋሲል ከነማ ሄድኩኝ። በፋሲል ቆይታዬም ግማሽ ያህሉን ተጎድቼ ነበር ፤ ግማሹን የተሻለ መጫወት ችዬ ነበር፡፡ ወደ ውጪ ታንዛኒያም ሄደን ተጫውተናል የተሻለ ጊዜ ነበረኝ። ከተሻለኝ በኋላ አጋጣሚ ሆኖ ውበቱ ነበር አሰልጣኝ ተቀየረ። ውበቱ ሲወጣ ስዩም ያዘ እና እሱ ደግሞ የራሱ አማራጭ ስለነበረው በእኔ ቦታ ተጫዋች በማምጣቱ መቀጠል አልቻልኩም። ከዛ 2012 ላይ ወደ ለገጣፎ ተመለስኩኝ። ከአሁኑ ጋር ሦስተኛ ዓመቴ ነው፡፡ በዛው ጥረት ስናደርግ ዘንድሮ ተሳካልን ብዙ ለፍተናል እና ብቻ ከጉዳት በኋላ የተሻለ ነገር መስራት ችያለሁ ዘንድሮ ፍሬ አፈራና የተሻለውን መስራት ቻልን፡፡
ተደጋጋሚ ጉዳቶች በፈለኩት ልክ እንዳላድግ አድርጎኛል ብለህ ታስባለህ ?
“አዎ በጣም ! በፊት ካለህ አቅም እና ችሎታ አንፃር ከጉዳት ጋር ይከብዳል። ጭንቅላት ነው ኳስ የሚጫወተው እና ጉዳት የተወሰነ ተፅእኖ ያደርግብሀል። እነዛን ነገሮች ደግሞ ተቋቁመህ መስራት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዛ ውስጥ ሆኖ ብቻ እግዚአብሔር ይመስገን ዘንድሮ የተሻለውን ነገር ሰርቻለሁ ብዬ አስባለሁ።
ክለባችሁ ያለፉትን ተከታታይ ዓመታት ለማደግ ከጫፍ እየደረሰ ይመለሳል፡፡ዘንድሮ ግን የሳክቶላችኋል። የስኬታችሁ ቁልፉ ምንድነው ?
“በአንድ የዕድሜ ጣርያ ላይ በመሆናችን እና መደማመጥ እና መሰማማት አለ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ደግሞ ቢያንስ አንድ አራት አምስት ልጅ የሚሆን አምስት ዓመት ፣ አራት ዓመት የቆየን አለን። ይህ ከዛ በፊት ያለውን ነገር እንዲቀጥል አድርጎታል። እነሱም በእኛ ስር ሆነው የቡድኑን ስታንዳርድ ሳይለቅ የተሻለ ፍቅር ኖሮት አላማ እንዲኖረው አድርጎ ጥሩ ነገር እንድናመጣ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ ያው ተሳክቷል፡፡
በከፍተኛ ሊጉ በደንብ ትታወቃለህ ከአሁን በኋላ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ራስህን ይበልጥ ለማሳየት ዕቅድህ እስከ ምን ድረስ ነው ?
“አዎ በጣም ! ፕሪምየር ሊግ ገብቼ ወጥቻለሁ እስከ ዛሬም ስሰራ የነበረው ለመመለስ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ዕድል አግኝቻለሁ እና ራሴን አዘጋጅቼ የተሻለ ነገር አሳያለሁ ብዬ ገምታለሁ። እስከ ዛሬም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። አንዳንዴ በደንብ ያላየኸውን ነገር ድጋሚ የተሻለ ነገር ለማሳየት ታስባለህ። እኔ አይቼው ስለተመለስኩኝ ያንን ነገሬን ደግሞ አሻሽዬ መገኘትን ነው የምፈልገው እና ከፈጣሪ ጋር የተሻለ ነገር ሰራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡”