[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ በነበረው ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን አገናኝቶ 1-1 ተጠናቋል።
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ከወልቂጤ ጋር አቻ ከተለያየው የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ደስታ ዮሐንስ እና አቡበከር ወንድሙ በማስወጣት በምትካቸው እዮብ ማቲያስ እና ሚሊዮን ሰለሞን ሲተኩ በተቃራኒው በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ከተረታው ስብስብ በተመሳሳይ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል ፤ ተስፋዬ መላኩ እና ሙሴ ካበላ ወጥተው በምትካቸው ቦና ዓሊ እና አስጨናቂ ፀጋዬን በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።
ባለ ሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት ዳዋ ሆቴሳ እና አሜ መሀመድን በፍጥነት ከተከላካይ ጀርባ በማስገባት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ግን አልቻሉም።
በአንፃሩ ቀዝቃዛ አጀማመርን በማድረግ ቀስ በቀስ ራሳቸውን ወደ ጨዋታው ማስገባት የቻሉት ጅማ አባ ጅፋሮች ዝግ ባለ ፍጥነት ኳሶችን በመቀባበል ወደ ፊት ለመሄድ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም የጨዋታውን የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል ፤ በ14ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ እና መስዑድ መሀመድ በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ያደረሱትን ኳስ መሀመድ ኑር ናስር በግሩም ሁኔታ ተንሸራቶ ቢሞክርም ጀማል ጣሰው ሊያድንበት ችሏል።
ቀስ በቀስ በጨዋታው ተፅዕኖ መፍጠር የጀመሩት ጅማዎች በ17ኛ ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል ፤ አድናን ረሻድ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ሳይጠበቅ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት የቅጣት ምት ኳስ ጀማል ጣሰውን አልፋ ከአዳማ መረብ መዋሀዷን ተከትሎ ጅማዎች መምራት ጀምረዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩት የጨዋታ ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች ጅማ አባ ጅፋሮችን ወደ ራሳቸው ሜዳ በመግፋት ይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረው ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም በ16ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የሞከራት እንዲሁም በ34ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አሜ መሀመድ በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም በሁለቱም አጋጣሚዎች አላዛር ማርቆስ የሚቀመስ አልሆንም።
ጫና የበረታባቸው ጅማዎች ይበልጥ በመከላከሉ ቢጠመዱም አዳማ ከተማ የአቻነቷን ግብ ከማግኘት የከለከላቸው አልነበረም ፤ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን ሰለሞን ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የጅማ አባ ጅፋር ተከላካዮች ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ በተፈጠረ መደራረብ ያገኘውን ኳስ አሜ መሐመድ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።
ከግቧ በኋላም የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ44ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የጣሉትን ኳስ በመከላከል ወቅት ግቡን ለቆ የወጣው አላዛር ማርቆስ ስህተት ታግዞ አሜ መሀመድ ያገኘውን ግሩም አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ አዳማዎች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት በቻሉ ነበር።
ሁለተኛውን አጋማሽ ካቆሙበት የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ47ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ዳዋ ሆቴሳ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም አላዛር ማርቆስ ሊያድንበት ችሏል።
በጨዋታ ሂደት አዳማ ከተማዎች አደገኛ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ሂደት ዘርዘር ማለትን ሲጠባበቁ ተመልክተናል። በዚህም የጅማ አባ ጅፋሮች ከግብ ክልሉ በራቁባቸው ውስን ቅፅበቶች አዳማ ከተማዎች ይህን ክፍተት ለመጠቀም በረጃጅም ኳሶች ሆነ በቅብብሎች ይህን ቦታ ለማግኘት ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን ይህም ሂደት እምብዛም ውጤታማ ሲሆን ግን አልተመለከትንም።
የጨዋታ ደቂቃ እየገፋ ሲመጣም ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች ይበልጥ ጫና ይፈጥራሉ ተብሎ ቢጠበቅም አዳማ ከተማዎች ግን ቀስ በቀስ ተቀዛቅዘው ተመልክተናል። በዚህም በ72ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከቆመ ኳስ የሞከራት እና አላዛር ማርቆስ ካዳነበት እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም አይተን አማካኝነት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎችን ለማስመልከት ተቸግረዋል።
አዳማ ከተማዎች በተለይ በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች በቁጥር በርከት ብለው በቀጥተኛ ኳሶች ለማጥቃት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም በጭማሪ ደቂቃ ላይ ጂብሪል አህመድ ያመከናት ኳስ እጅግ አስቆጭ ነበረች።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በውድድር ዘመኑ 11ኛ የአቻ ውጤታቸውን ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በ23 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ በ12 ነጥብ ሰበታ ከተማን በጎል በልጠው ወደ 15ኛ ደረጃ ተመልሰዋል።