የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

17ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 በጨዋታ ሳምንቱ ያተረፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሊጉ ሰንጠረዥ ለዋንጫ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት እና እስከ አምስተኛ ደረጃ ከሚገኙ ቡድኖች በጨዋታ ሳምንቱ ብቸኛ ድል ማስመዝገብ የቻለው መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ቡናን 4-0 መርታት የቻሉት ፈረሰኞቹ በሰንጠረዡ አናት መሪነታቸውን በ37 ነጥብ ሲያስቀጥሉ በማስከተል 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ በመሆን ቅዱስ ጊዮርጊስን እየተከተሉ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ በጨዋታ ሳምንቱ ሌላኛው ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸው ልዩነት ወደ አምስት እና ስድስት ነጥቦች ከፍ እንዲል ተገደዋል።

በተመሳሳይ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፋሲል ከተማዎች በወልቂጤ ከተማ መሸነፋቸውን ተከትሎ ከመሪው ያላቸው ልዩነት ወደ 10 ነጥብ ከፍ ሲል 5ኛ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡናም እንዲሁ ከድሬዳዋ ጋር ነጥብ በመጋራቱ መነሻነት ከጊዮርጊስ በ10 ነጥብ ርቆ ተቀምጧል።

በጥቅሉ በጨዋታ ሳምንቱ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፉን ተከትሎ ከተከታዮቹ ያለው ልዩነትን በማስፋት እጅግ ውጤታማ የጨዋታ ሳምንት ማሳለፍ ችሏል።

👉 ቆም ብሎ ማሰብ የሚገባው ኢትዮጵያ ቡና

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተጠባቂ ከነበሩት ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚው በነበረው እና ኢትዮጵያ ቡናን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው የሸገር ደርቢ ፈረሰኞቹ ፍፁም የሆነ የበላይነት የተጠናቀቀ ነበር። 4-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናዎች እንቅስቃሴ ግን ለክለቡ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር።

በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡና ኳስ ምስረታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ጫና አንፃር እንዴት ይሆናል የሚለው ጉዳይ ይጠበቅ ነበር። ታድያ በጨዋታውም ከዚህ በፊት በነበሩት በመጨረሻዎቹ ሦስት የደርቢ ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያውን የምስረታ ሂደት በጠራ መልኩ ለመውጣት ተቸግረው ያስተዋልን ሲሆን በዚህ ሂደት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሚያቋርጧቸው ኳሶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተመልክተናል።

ከዚህ ከተለመደው አዝማሚያ ባለፈ በጨዋታው ሌላው መነጋገርያ የነበረው ጉዳይ ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ፍፁም ተቸግሮ የመመልከታችን ጉዳይ ነበር። እርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ላለ ኳሶችን መስርቶ በሂደት በማሳደግ በኳስ ቁጥጥር ለመጫወት ለሚሻ ቡድን የምስረታው ሂደት የጠራ ካልሆነ ብዙ ነገሮች ሊበላሹ እንደሚችሉ ቢገመትም በጨዋታው ቡድኑ የነበረው የማጥቃት አፈፃፀም ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥቅሉ ሦስት ብቻ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ጋር የደረሰ አንዳች ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።

ይህ ሂደት በደርቢው ጨዋታ ብቻ የተሰተዋለ ሳይሆን በአጠቃላይ የውድድር ዘመን የቡድኑ ጉዞ ውስጥ እያስተዋልነው የመገኘታችን ነገር ገዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። እስካሁን በሊጉ 12 ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ቡና ከድሬዳዋ ጋር በጣምራ በሊጉ ሦስተኛው ደካማ የማጥቃት ቁጥር ያለው ቡድን ሲሆን በዚህም ረገድ የሚበልጡት በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር (10) እና አርባምንጭ ከተማ (11) መሆኑ ስለቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ በደንብ ገላጭ ቁጥር ነው።

ለንፅፅር እንዲረዳን በ2013 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡናዎች ከ17 ጨዋታዎች በኋላ 36 ግቦችን ማስቆጠር ችለው የነበረ ሲሆን ይህም በወቅቱ የሊጉ ምርጥ ማጥቃት እንደነበረ የምናስታውሰው ነው። አሁን ላይ የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ቁጥሮች በዚህ ደረጃ የመውረዳቸው ነገር የሚያነጋግር ነው።

ለዚህ ሂደት በርካታ ምክንያት መጥቀስ ቢቻልም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከምንም ለቡድኑ ግቦችን ሲፈጥር የነበረው አቡበከር ናስር ቁጥሮች መቀነስ ግን ቀዳሚው መንስኤ ነው። በዘንድሮ የውድድር ዘመን በ14 ጨዋታዎች ተሳትፎን ያደረገው አቡበከር ናስር 1198 ደቂቃዎችን ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን በዚህም ስድስት ግቦችን እንዲሁም ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶችን ብቻ ማስመዝገብ ችሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ29 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው አጥቂው አምና በጨዋታ በአማካይ 1.26 ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ይህ ቁጥር በጨዋታ ወደ 0.43 ግብ ወርዷል። ለግብ የሆነ ኳሶች አመቻችቶ የማቀበል ቁጥሩም በተመሳሳይ በጨዋታ በአማካይ 0.17 የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ወደ 0.16 ወርዷል። ለአብነት እነዚህን ቁጥሮች አነሳን እንጂ ሌሎችም ቁጥሮች የሚያሳዩት የአቡበከር ጨዋታን በሚወስኑ ሂደቶች ላይ ያለው ተፅዕኖ ስለመቀነሱ ነው።

ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በክረምቱ ያጣቸው ቁልፍ ተጫዋቾች ተፅዕኖም ሆነ ተጋጣሚ ቡድኖች ለኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ መንገድ ይበልጥ እየተለማመዱት የማክሸፊያ መንገዶችን እያዘጋጁ የመቅረባቸው ጉዳይ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ የቡድኑን ጉዞ ፈታኝ አድርገውበታል።

ደካማ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘው ቡና በአሁኑ ወቅት በ21 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁናዊ ደረጃው ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 ነጥብ እንዲሁም በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በ10 ነጥቦች ርቀት ላይ ሆኗል። በመሆኑም በሰንጠረዡ ወደ ላይ ገፍተው ለማጠናቀቅ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ በተለይም የማጥቃቱ ነገር መላ ሊባል ይገባል።

በተቃራኒው በመከላከሉ ረገድ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በአጠቃላይ የቡድኑ የአደረጃጀት ክፍተቶች እንደነበሩበት በስፋት የተስተዋለ ሲሆን ከዚህ ጋርም በተያያዘ የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና በስፋት ከኳስ ጋር ስላሉ ጉዳዮች እንጂ ከኳስ ውጭ ስለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እምብዛም ትኩረት የሚያደርግ ቡድን አለመሆኑን በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን። ቡድኑ ከኳስ ጋር በቁጥር በርክቶ ለማጥቃት ይሞክራል ነገር ግን ቡድኑ ከኳስ ውጭ በሚሆንበት ጊዜ በሜዳው የላይኛው ክፍል ካውንተር ፕሬስ በማድረግ አልያም በፍጥነት ወደ መከላከል ቅርፅ በመምጣት ሂደት ላይ ግን ጥርት ያለ ሀሳብ የሌለው ቡድን መሆኑ በመከላከሉ ተጋላጭ ሲያደርገው አስተውለናል።

ሌላው በመከላከሉ ቡድኑ ካለበት ችግሮች አንዱ የተረጋጋ የተከላካይ መስመር ያለመያዙ ጉዳይ ነው። ቡና በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በአራት ተከላካይ እንደመጫወቱ አራት የተለያዩ የመሀል ተከላካይ ተጫዋቾች ጥምረት ተጠቅሟል። በዚህ ሂደት የአበበ ጥላሁን እና ቴዎድሮስ በቀለ ጥምረት 50% በሚሆኑ ጨዋታዎች ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን የወንድሜነህ ደረጀ እና አበበ ጥላሁን ጥምረት ደግሞ 31.25% በሚሆኑት ጨዋታዎች ጥቅም ላይ መዋል ሲችል የተቀሩት የአበበ እና ገዛኸኝ እንዲሁም ቴዎድሮስ እና ገዛኸኝ ጥምረቶች ደግሞ 12.5% እና 6.25% በሚሆኑት ጨዋታዎች ላይ በሜዳ ውስጥ ነበሩ።

በዚህ ሂደት ከአበበ ጥላሁን ውጪ ከእሱ ጎን የሚጫወተው አጣማሪ እስካሁን ያለመለየቱ ነገር ቡድኑ ጠንካራ እና የተዋሀደ የመከላከል መስመር እንዳይኖረው አስገድዷል።ይህ አለመረጋጋት በተወሰነ መልኩ በመስመር ተከላካይነት ስፍራም ይስተዋላል ሀይሌ ገ/ተንሳይ እና ስዩም ተስፋዬ የተሻለ የጨዋታ ቁጥር ቢኖራቸውም በቡድኑ ማጥቃት ላይ ባለፈው ዓመት ድንቅ አበርክቶ የነበረው የመስመር ተከላካያቸው አስራት ቱንጆ በስድስት ጨዋታዎች ብቻ በመስመር ተከላካይነት ጨዋታውን ጀምሯል። ይህም ምናልባት በማጥቃት ረገድ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ድርሻ እንዲያንስ አድርጓል።

እንደ አጠቃላይ ግን እጅግ አስከፊ ሽንፈትን በደርቢው ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት ቆም ብለው በማሰብ አምና ተስፋ ሰጥቶ የነበረውን ቡድን ከፍ ብሎ እንዲመለስ በማስቻል የደጋፊውን መሻት ለመሙላት መጣር ይኖርባቸዋል።

👉 ከ108 ቀናት በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ሰበታ ከተማ

በስምንተኛ የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን በክሪዚስቶም ናታምቢ ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ከቻሉ በኋላ ድል ማስመዝገብ ተቸግረው የቆዩት ሰበታ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት መከላከያን በመርታት ዳግም ከድል ታርቀዋል።

ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲታመስ የቆየው ቡድኑ ከጅማ አባጅፋሩ ድል በኋላ እንኳን ተጫዋቾች ልምምድ ያቆሙባቸው አጋጣሚዎች ፣ ዋና አሰልጣኙን ያገዱበት እንዲሁም አሰቃቂ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ሽንፈት ክለቡን ስናስብ ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡ ዓበይት ክስተቶች ነበሩ።

አሁንም ከእነዚህ አስተዳደራዊ ችግሮች ጋር እየታገለ ቆይቶ ሌሎች ቡድኖች ለሁለተኛው ዙር ከአስራ አምስት ቀናት ያላነሰን የዝግጅት ጊዜያትን አሳልፈው ወደ ውድድሩ ሲገቡ ሰበታ ከተማዎች ግን በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች መነሻነት ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ ለአራት ያህል ቀናት ብቻ ልምምድ ሰርተው ወደ ውድድር መግባታቸው አይዘነጋም። በዚህም በዙሩ የመክፈቻ ጨዋታ በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 በተሸነፉበት ጊዜ ከነበሩበት ሁኔታዎች በተቃራኒው ሜዳ ላይ የነበራቸው እንቅስቃሴ ተስፋ የሚያስቆርጥ አልነበረም።

በቀናት ልዩነት መከላከያን የገጠመው ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ያሳዩትን የተነሳሽነት ስሜት ይበልጥ አሳድገው ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል በዚህም ተጋጣሚያቸው መከላከያ በጥንቃቄ መጫወት መምረጡን ተከትሎ በሁለቱም አጋማሾች የተሻለ ኳስን በመቆጣጠር እንዲሁም ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ጥቃቶች ጦሩ ላይ ብልጫ በመውሰድ በመጨረሻም በዴሪክ ንሲምባቢ አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ከድሉ በኋላ ቡድኑን በአሰልጣኝነት በመሩት ብርሃኑ ደበሌ ሆነ በተጫዋቾች እንዲሁም ጨዋታውን በሜዳ ተገኝተው በታደሙ ጥቂት የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ይታይ የነበረው ከጭንቀት የመገላገል ስሜት ቡድኑ ለስምንት የጨዋታ ሳምንታት በዘለቀው እና በድምሩ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ባሳኩበት ውጤት አልባ ጉዞ መነሻነት ተፈጥሮ የነበረውን የውጥረት ስሜት ፍንተው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድሉን ማሳካት የቻለው ሰበታ ነጥቡን ሁለት አሀዝ ማድረስ የቻለ ሲሆን በሊጉ ቆይታውን ለማስቀጠል ይህን የመነሳሳት ስሜት ማስቀጠል ይኖርበታል።

👉 ለተጋጣሚው ከልክ ያለፈ አክብሮት ያለው መከላከያ

ጥንቃቄ እና መከላከያን ነጣጥሎ መመልከት እስኪከብድ ድረስ በሊጉ እየተመለከትነው የሚገኘው መከላከያ ስላለመሸነፍ አብዝቶ የሚጨነቅ ቡድን መሆኑን እየተመለከትን እንገኛለን።

አራት ጨዋታዎችን 0-0 በሆነ ውጤት ያጠናቀቀው ቡድኑ ፤ በስምንት ጨዋታዎች ደግሞ 1-0 በሆነ ውጤት አጠናቋል (አራት አሸንፈው ፣ አራት ተሸንፈዋል) ፤ ቡድኑ እስካሁን በሊጉ በሦስት አጋጣሚዎች ብቻ በጨዋታ ሁለት እና ከዚያ በላይ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ከላይ የጠቀስናቸው አሀዞች ስለቡድኑ ጥንቃቄ መር አጨዋወትም ሆነ ጨዋታዎችን ለተጋጣሚ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚያደርጉ ማሳያ ናቸው። ዘንድሮ ከታችኛው ሊግ እንደመጣ ቡድን በጥንቃቄ በመጫወት በሊጉ በተረጋጋ መልኩ ቆይታቸውን ለማስቀጠል ከመፈለግ ሊመነጭ ቢችልም የመከላከያ ግን ትንሽ ከልክ ያለፈ ይመስላል።

ለአብነትም በሊጉ በሁለተኛ ዙር ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች በደረጃ ከመከላከያ ጋር “ተመጣጣኝ” ከሆኑት እና ሁለቱም ቡድኖች ዕኩል የማሸነፍ ዕድልን ይዘው በጀመሩበት የአርባምንጭ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ የቡድኑ ጥቅል የጨዋታ አቀራረብ በሰንጠረዡ አናት ካለ ተጋጣሚ ጋር የሚጫወቱ እስኪመስል ድረስ ተሰብስበው ወደ ኃላ ሲከላከሉ ብሎም የአቻ ውጤቶቹን ለማስጠበቅ ሲታትሩ ተስተውሏል።

ታድያ ይህም “ተመጣጣኝ” ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች በዚህ መልኩ ከተጠነቀቀ በስብስብ ጥራት ከላቁ እና በሰንጠረዡ የተሻለ ቦታ ላይ ከሚገኙ ተጋጣሚዎች ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በምን መልኩ ሊቀርብ ነው የሚለው ነገር ተጠባቂ አድርጎታል።

👉 በመሻሻሎች ውስጥ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ

ከመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች አንስቶ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እየተመሩ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በሚታይ መልኩ እየተሻሻሉ ይገኛል።

ከሰሞኑ ስለመሻሻላቸው ምልክት እየሰጡ የነበሩት ወልቂጤ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የአምናው የሊጉ አሸናፊ የነበረውን ፋሲል ከነማን እንደመግጠማቸው ብዙዎች ሊቸገሩ እንደሚችሉ ቢጠብቁም በጨዋታው የገጠማቸውን ፈተና በሚገባ በመወጣት ጠንካራውን ፋሲል 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አከታትለው ባስቆጠሩት ግብ መምራት የጀመሩት ወልቂጤ ከማዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው ድንቅ እንቅስቃሴ የፋሲል ከነማ ጠንካራ ጎኖችን በሙሉ በማዳከም ቡድኑ ተገዶ ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን እንዲጥሉ ያስገደደ ነበር።

ትልቅ ትርጉም ያለው ድል ያስመዘገበው ወልቂጤ በአዲሱ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እየተመራ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ከውጤት አንፃር ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈው ፤ በሁለት አቻ ወጥተው እንዲሁ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈትን ቢያስተናግዱም እንደ አጠቃላይ ግን ቡድን በሚታይ መልኩ ሜዳ ላይ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የሚገኝ ሲሆን በእነዚሁ ጨዋታዎች ወቅት የራሱ የሆነ የአጨዋወት መገለጫ ያለው ቡድን ለመሆን ጥረት ላይ መገኘቱ ትኩረትን ይስባል።