[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″] በኢትዮጵያ እግር ኳስ ገናና ስም ያለው መከላከያ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ስያሜውን ለመቀየር ውሳኔ ላይ ደርሷል።
በ1934 ጦር ሠራዊት በሚል ስያሜ የተመሰረተውና በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክለቦች ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ሁለተኛው አንጋፋ ቡድን የሆነው መከላከያ በ1947 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ”የወታደራዊ እና ፖሊስ ቡድኖች መጠርያ ስማቸው የጦር ክፍሉን ስያሜ ሲይዝ የሚፈጥረው ስሜት ለእግር ኳሱ ህግ አተገባበር አይመችም” በሚል ስያሜያቸውን እንዲቀይሩ ባወጣው ህግ መሰረት በወቅቱ ጦር ሠራዊት ወደ መቻል ተቀይሮ እንደነበር ይታወሳል። ክለቡም በዚህ የስያሜ ለዓመታት እጅግ የታወቀበትን እና ውጤታማ ዘመኖቹ የሚታወሱበት ጊዜያትን አሳልፏል።
ክለቡ ከመቻል በኋላ ወደ ምድር ጦር፣ ፀሐይ ግባት እና ሌሎች መጠርያ ስሞች ሲቀየር ቆይቶ በ1990ዎቹ አጋማሽ በአዲስ መልክ ሲደራጅ መከላከያ ስፖርት ክለብ የሚለው ስያሜን በመያዝ እስከ ዘንድሮው የውድድር ዓመት ድረስ ሲጠቀምበት ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት የሚገኙት የስፖርት ክለቡ አመራሮችም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ስያሜ ዳግም ለመመለስ ሥራዎችን ሲሰሩ የከረሙ ሲሆን በመጨረሻም መቻል የሚለው የቀደመ ስያሜ እንዲመለስ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቀዋል።
ከእግር ኳስ ውጪ በርካታ የስፖርት ቡድኖች በሁለቱም ፆታዎች ያሉት መከላከያ ስሙን ለመቀየር ቢወስንም መቻል የሚለውን ሥያሜ ከቀጣዩ የ2015 የውድድር ዓመት ጀምሮ እንደሚጠቀምበት አውቀናል። ይህ የሆነው ደግሞ ዘንድሮ በስፖርት ክለቡ ሥር የሚገኙ ቡድኖቹ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና አወዳዳሪ አካላት መከላከያ በሚል ስያሜ በመመዝገባቸው እንደሆነ ተነግሮናል።
በሁለቱም ፆታዎች በፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ ቡድኖቹ በተጨማሪ የወታደር ፣ ከ20 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የስፖርት ለሁሉም (በመስሪያ ቤቱ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚሳተፉበት) እንዲሁም በአትሌቲክሱ ከአጭር እስከ ማራቶን ድረስ ቡድኖች በስሩ ያሉት መከላከያ በቀጣዩ ዓመት ስያሜውን ሲቀይር የሚሳተፍባቸውን የስፖርት አይነቶች እንዲያሰፋ አቅጣጫ እንደተቀመጠም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።