ያለግብ ከተጠናቀቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ
ስለጨዋታው
“ተጋጣሚያችን ጠንክሮ እንደሚገባ እናውቃለን። ብዙ የአዳማ ተጫዋቾች ሊጉን ጠንቅቃው የሚያውቁ እና ልምድ ያላቸው ናቸው ፤ ከጀማል ጀምሮ እስከ ዳዋ ልምድ ያላቸው ናቸው። ፋክክሩ አሁንም እየለየ ስላልሆነ እኛ ደግሞ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የሌሎችን ውጤት አይተን ነው የገባነው እና ያለንን የሁለተኝነት ደረጃ ጠብቀን ነጥቦችን ለማስጣል አስበን ነበር የገባነው። በዚህ የፀሀይ ጨዋታ እንደዚህ ዓይነት ፉክክር መታየቱ ቀላል የሚባል አይደለም። በምንፈልገው መልኩ ሄዷል ማለት እንችላለን ፤ ካለማሸነፋችን ውጪ ጠንካራ ፉክክር ነበር።
ስለዋንጫ ፉክክሩ
“ዛሬ ብናሻነፍ እና ውጤታማ ብንሆን ከተከታዮቻችን ጋር ያለን ልዩነት አራት ይሆንና ወደ ጊዮርጊስ ደግሞ እንጠጋለን የሚል ግምት ነበረን። እግርኳስ ነው ፤ ያጋጥማል። ሁለተኛው ዙር ላይ ሁሉም ቡድኖች ተመሳሳይ ናቸው ፤ ተመጣጣኝ ብቃት ውስጥ ናቸው ያሉት ፤ እና ቀላል አይደለም። ተጋጣሚያችንን አክብረን ነው የገባነው ፤ እኛም የተለየ ቡድን አይደለም ያለንን ታታሪነት ፍላጎት ጥሩ ነው። አሁን በተቻለ መጠን ሁለቱን ነገር አካተን ወደ ጎል እየደረስን ነው ያለነው ፣ ጠንካራ የሆነ የመከላከል ባህሪም አለን። እንደቡድን እንከላከላለን ፤ በተገኘው አጋጣሚ ለማግባት እንሞክራለን። እንደቡድን ግን ሦስተኛ የዘጠኝ ሰዓት ጨዋታ ነው ያደረግነው። ድካሞች ሊኖሩ ይችላሉ እንደዛም ሆኖ ግን ፍሬሽ የሆነ ቡድን ነው ይዘን የቀረብነው።
ስለደጋፊው
“ስለደጋፊያችን መናገር አትችልም ፤ የወላይታ ድቻ ደጋፊ ደሙ ነው ቡድኑ። የትም ቦታ የሚከተለን ደጋፊ ነው። በደጋፊው በሜዳ ላይ ብልጫ ነበረን ማለት እችላለሁ። እኛም ከፍተኛ ኃላፊነት እየተሰማን ነው። ደጋፊዎቻችን እንደድካማቸው በየጨዋታዎች ጨፍረው ተደስተው እንዲሄዱ ነው የምንፈልገው። ለደጋፊያችን አሁንም ቢሆን በትዕግስት ከሄድን የተሻለ ደረጃ ይዘን ማጠናቀቅ እንችላለን። አሁንም እንደተለመደው ከጎናችን አይለየን ነው የምለው።”
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ
ስለጨዋታው
“ከኋላ ኳሱ ሲነሳ መጥፎ አልነበረም። መሀል ሜዳ ላይ ከአጥቂዎች ጋር የነበረን ግንኙነት ደካማ ስለነበር ብዙ ኳሶች መሀል ላይ ይቆራረጡ ነበር። በዚህ ላይ ስድስት እና ሰባት ሆነው ተጠቅጥቀው ይከላከሉ ስለነበር ማስከፈት አልቻልንም። እነሱ ከቆመ ኳስ እና ከመስመር እንደሚያጠቁ ገምተን ነበር። ግን ይበልጥ እነሱ ሜዳ ላይ ምቾት ነበራቸው ፤ ካላቸው ደረጃ አንፃር። እኛ ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንፈልግ ስለነበር በችኮላ እና ጫና ውስጥ ሆነው ስለነበር ልጆቹ ውሳኔዎች ይወስኑ የነበረው ያ ነው አስቸጋሪ ያደረገብን።
የአጥቂዎች ከግብ መራቅ በራስ መተማመናቸውን ዝቅ ስለማድረጉ
“ትክክል ነው ፤ ሁሉም ጎል ማግባት ይፈልጋሉ። በዚህ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ አንድ ነጥብ ማግኘታችን በተለይ በሜዳችን ተጫዋቾች የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍ እንዲል ያደርግ እና ግን ሜዳ ላይ አስተውለው እንዳይሰሩ ያደርጋቸዋል። አንዳንዴ በቀላል ኳስ የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ሁሉ ደካማ ነበር። ውጤቱ ባያስደስተንም ያው አቻ ወጥተናል።
ወደ አሸናፊነት ስለመምጣት
“ጥረት እናደርጋለን። የመጀመሪያው ተጫዋቾቻችንን ሥነልቦና ከፍ ማድረግ ነው ፤ ሁለተኛ የምናጠቃበትን መንገድ ማስተካከል። በተለይ ከሂደቶች ጋር ተያይዞ ችኮላዎች አሉ ፤ አላስፈላጊ ረጅም ኳሶች ይጣላሉ። ከተሰጡም ደግሞ አላማ ያላቸው እንዲሆኑ እዛ ላይ ጠንክረን እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።”