በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በስምምነት ከሦስት ተጫዋቾች ጋር መለያየቱ ታውቋል።
በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ጅማ አባጅፋር በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 18 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ቡድኑ ቀድሞ ከሦስት ተጫዋቾች ጋር ከተለያየ በኋላ በቀሪ ጨዋታዎች በሊጉ ለመትረፍ በውሰት አራት ተጫዋቾችን ያመጣ ሲሆን በቋሚነት ደግሞ የግብ ዘቡ ሀሪሰን ሄሱን ለማስፈረም ቢስማማም እስካሁን የወረቀት ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው የተጫዋቹን ውል ማፀደቅ አልቻለም።
አሁን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾች በስምምነት ከቡድኑ መለየታቸውን ይጠቁማል። የመጀመሪያው ተጫዋች ስብስቡን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በውሰት ተቀላቅሎ የነበረው ትንሳኤ ያብጌታ ነው። ከ45 ደቂቃዎች በላይ በአባ ጅፋሩ ቤት ግልጋሎት ካልሰጠው ትንሳኤ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ከሀዋሳ ከተማ በውሰት የመጣው እና አንድ ጨዋታ የተጫወተው ብሩክ ሙሉጌታም እንደ ትንሳኤ ቡድኑን ተለያይቷል። ከሁለቱ በተጨማሪ ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀላባ ከተማ በአንድ ዓመት ውል ፈርሞ አንድም ደቂቃ በሜዳ ያልተመለከትነው አብዱልሰመድ መሐመድም በስምምነት ክለቡን መልቀቁ ተመላክቷል።