ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 18ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተሻለ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾች እና አሰላጣኝን መርጠናል።

አሰላለፍ 4-4-2 ዳይመንድ

ግብ ጠባቂ

በረከት አማረ – ኢትዮጵያ ቡና

ከቆይታ በኋላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ብቅ ያለው በረከት ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ መሩቡን ሳያስደፍር እንዲወጣ ከፍተኛውን ኃላፊነት ተወጥቷል። በጥሩ ንቃት እና የጊዜ አጠባበቅ ኳሶች አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት ሲያመክን የነበረው በረከት ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ከባባድ ሙከራዎች ቢደረገበትም አልተበገረም ፤ በዚህም አራት ኢላማቸው የጠባቁ ከባድ ሙከራዎችን ማዳን ችሏል።

ተከላካዮች

ብርሀኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

በሳምንቱ አስደናቂ የውጤት ለውጥ በታየበት የአርባምንጭ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ነብሮቹ ከ4-1 መመራት ወደ 4-4 ውጤት ሲመጡ ወሳኟን አራተኛ ግብ በጭማሪ ደቂቃ ያስቆጠረው የቀኝ ተመላላሹ ብርሀኑ በቀለ ነበር። ተጫዋቹ ቡድኑ ወደ መጨረሻ ላይ በፈጠረው ጫና ውስጥ ከነበረው አስተዋፅዖ ባለፈ ነብሮቹ ተዳክመው በቆዩባቸው አመዛኝ ደቂቃዎችም የተሻለው የማጥቃት ጥረቶቻቸው መነሻ በመሆን የበኩሉን አድርጓል።

ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና

ቁመተ መለሎው የሲዳማ የኋላ ደጀን ወጥ የሆነ አቋም በማሳየቱ ገፍቶበታል። ተጫዋቹ ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ምርጥ 11 ስብስባችን ውስጥ መካተቱ በራሱ ለዚህ ምስክር ነው። በሀዋሳው ጨዋታ ጊት በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበረው ድንቅ ትኩረት እና የደርቢውን ጨዋታ የሚመጥን ጀብደኝነት ብቻ ሳይሆን በማጥቃቱም ረገድ ከቆሙ ኳሶች በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክሯል።

ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ዋነኛ መመዘኛ የቡድናቸው ግብ እንዳይደፈር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቢሆንም ፊሪፖንግ ግን በ18ኛው ሳምንት ከዚህም እጅግ የራቀ አገልግሎት ሰጥቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ሲረታ የፊት አጥቂ ድርሻ በሚመስል መልኩ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ግቦቹ ጨዋታውን ከ0-0 ወደ 2-0 እንዲመጣ ያደረጉ መሆናቸው ደግሞ ዋጋቸውን ከፍ ያደርገዋል።

ሱራፌል ዐወል – ጅማ አባ ጅፋር

የዓመቱን ሦስተኛ ጨዋታውን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የጀመረው ሱራፌል ከአማካይነት ሚናው ወደ ግራ መስመር ተመላላሽነት ተቀይሮ ለ 85 ደቂቃዎች ተጫውቷል። በእንቅስቃሴውም ኮሪደሩ ላይ በመመላስ የፋሲልን የቀኝ ጥቃት በመከላከል እንዲሁም እስከ ተጋጣሚው የሜዳ አጋማሽ በጥልቀት በመግባት ለቡድኑ የማጥቃት አማራጭ በመስጠት በቀጣይ የተሻለ የመጫወቻ ደቂቃ የሚያሰጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የጅማን ብቸኛ ጎል በተመጣጠነ ተሻጋሪ ኳስ ማመቻቸትም ችሏል።

አማካዮች

ይሁን እንዳሻው – ፋሲል ከነማ

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰው ይሁን ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ በብቸኝነት ተሰልፏል። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በልዩ ንቃት ኳሶችን ሲያስጥል የነበረው ይሁን መካከለኛ ርቀት ባላቸው ኳሶች ማጥቃትን በማስጀመር እንዲሁም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመቅረብ ለቡድኑ ጥቃት ተጨማሪ ኃይል በመሆን አሳልፏል። በዚህም ፋሲል ከመመራት ተነስቶ ሲያሸንፍ አቻ የሆነባትን ወሳኝ ግብ ከሰጥን ውጪ በጠንካራ ምት አስቆጥሯል።

ሮቤል ተክለሚካኤል – ኢትዮጵያ ቡና

ቡና ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመለስ ኤርትራዊው አማካይም የደመቀበትን ምሽት አሳልፏል። በቡድኑ አማካይ ክፍል ውስጥ ከሳጥን እስከ ሳጥን በትጋት በመንቀሳቀስ ቡና በተጋጣሚው ላይ የመሀል ሜዳ ብልጫን እንዲወስድ የግሉን ጥረት አድርጓል። ሮቤል የመጀመሪያውን የአቡበከርን ጎል አመቻችቶ ማቀበል ሲችል ሁለተኛውን ደግሞ በልዩ ሁኔታ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ በመምታት አስቆጥሯል።

ያብስራ ተስፋዬ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በዚህ ሳምንት ምርጥ 11 ውስጥ ለመካተት ከቡድን አጋሩ አቤል ያለው ጋር የተፎካከረው ያብስራ ተመራጭ ሆኖ 4-4-2 ዳይመንድን እንድንጠቀም ምክንያት ሆኗል። በጥሩ ወቅታዊ አማካይ ላይ የሚገኘው አማካዩ መሀል ላይ በቁጥር ብልጫ ከነበረው እና በተጫዋቾች ምርጫም የቦታውን ፍልሚያ ያከበደው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ጊዮርጊስ ብልጫ እንዳይወሰድበት በታታሪነት ተንቀሳቅሷል። ከኳስ ጋርም በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ሦስተኛውን የአቤልን ጎል አመቻችቷል።

ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና

በሮድዋ ደርቢ ሲዳማ ሀዋሳ ከተማን 3-1 ሲረታ መሀል ሜዳ ላይ ዳዊት ልዩነት ፈጣሪው ተጫዋች ሆኗል። በቡድኑ የኳስ ቅብብሎች ውስጥ ዋናው አቀናባሪ የነበረው ግራኙ አማካይ ጥሩ የማጥቃት ተሳትፎ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ራሱ የጀመረውን የማጥቃት ሂደት ሳጥን ውስጥ ደርሶ ዋደ ግብነት ሲቀይር ይገዙ ቦጋለ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ ሲያገናኝ ከሲዳማ ሜዳ በቀጥታ የላካት ኳስ የዕይታውን ጥልቀት ያሳየች ነበረች። በዚህም የአማካይ ክፍላችን ዳይመንድ ጫፍ ላይ ሰይመነዋል።

አጥቂዎች

አህመድ ሁሴን – አርባምንጭ ከተማ

ረጅሙ አጥቂ ከባድ ጉዳት ባስተናገደበት ጨዋታ 72 ደቂቃዎችን ብቻ ሜዳ ላይ ቢቆይም በአዲሱ ክለቡ የዓመቱን የመጀመሪያ ሐት-ትርኩን ሰርቷል። አህመድ የቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መቋጫ ከመሆን ባለፈ ረጃጅም ኳሶችን በማውረድ አርባምንጭ በተደጋጋሚ ከሁለተኛ ኳሶች አደጋ እንዲፈጥር አስችሏል። ቀሪዋ የፀጋዬ አበራ ጎል የተገኘችውም በአህመድ አመቻችነት ነበር።

ሪችሞንድ ኦዶንጎ – አዲስ አበባ ከተማ

ጋናዊው የመዲናዋ የፊት መስመር ተጫዋች በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ በስምንት ግቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻለውን የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል። ቡድኑ በእጅጉ ሲፈልገው የነበረውን ሦስት ነጥብ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ሪችሞንድ በእንቅስቃሴም የፊት መስመሩን አስፈሪነት ማላበስ ሲችል አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ በትዕግስት ለምን ዕድል እየሰጡት እንደቆዩ አሳይቷል።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ

ሲዳማ ቡና ከሁለት ነጥብ የተጋራባቸው ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ ያስቻሉት አሰልጣኝ ገብመድኅን የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል። ከደርቢነት ባለፈ ከሀዋሳ ከተማ ወቅታዊ አቋም አንፃር ከፍ ያለ ግምት በተሰጠው ጨዋታ የተጋጣሚያቸውን ጠንካራ ጎኖች በማክሸፍ የእንቅስቃሴ የበላይነት በመውሰድ 3-1 መርታታቸው የማያሻማ ተመራጭ አድርጓቸዋል።

ተጠባባቂዎች

አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር
ውሀብ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ
አስጨናቂ ፀጋዬ – ጅማ አባ ጅፋር
መሀሪ መና – ሲዳማ ቡና
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ፀጋዬ አበራ – አርባምንጭ ከተማ
አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና