የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 መከላከያ

እስከመጨረሻው በፍልሚያ የደመቀው ጨዋታ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ይህንን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለተጋጣሚያቸው

“በመከላከሉ ይሄ እንደሚገጥመኝ መጀመሪያም ተናግሬያለሁ። የተሻለ ተከላክለዋል በዚህ ውስጥ ግን የተሻሉ ኳሶች አግኝተናል ፤ ስተናል። ይሄ በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው። ጠንካራ ቡድን ነበር ዛሬ።

መከላከያ በጨዋታው መጀመሪያ ከፊት ስለፈጠረው ጫና

“መጀመሪያ ራስህን አረጋግተህ የጨዋታውን ሪትም አይተህ ትገባለህ። እኛ እንዳንጫወት በእኛ ሜዳ በጥልቀት ገብተው የመከላከል ሥራ እየሰሩ ነበር። ያንን በሁለተኛው አጋማሽ እንደማይቀጥሉት እናውቅ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ አንዴም ወደኛ አልመጡም። ያንን ሰብረን የተሻለ ነገር ለመስራት ብዙ ዕድሎች ሞክረናል አግኝተናልም ፤ አልተጠቀምንም።

ስለተሳቱ ኳሶች

” አንዳንዱ ስሜታዊ መሆን ቸኩሎ ለማግባት የመሄድ ነገሮች ናቸው ፤ ግብ ጠባቂውም ጥሩ ነገሮች አድርጓል። በእንቅስቃሴ ኳሶች አግኝተናል ብንጠቀምባቸው ኖሮ ይበልጥ ተሻሽለን ሌሎች ጎሎችንም እናገባ ነበር። ግን በጭንቀት ውስጥ ሆነህ የምታደርገው ነገር ራስ ላይ ጫና ይፈጥራል እና ልጆቼን በዚህ አጋጣሚ ዘጠናውን ደቂቃ ሳይደክሙ ምንም ስሜታዊ ሳይሆኑ የተሻለ ነገር ለማድረግ ወደ ጎል ብዙ ኳስ ደርሰዋል አልተጠቅምንበትም። ይሄን ስላደረጉ በጣም ነው የማመሰግናቸው።”

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ

ስለቅዱስ ጊዮርጊስ ጥንካሬ

“በትክክል ፤ ጠንካራም ቡድን ስለሆነ ለራሳችን ብለን ጠንክረን መግባት ነበረብን። የማይሆን መሸነፍም ልትሸነፍ ትችላለህ። ስለዚህ የጊዮርጊስ ጠንካራነት አንተም ጠንክረህ እንድትገባ ያደርግሀል። ምክንያቱም ራስህን ከአደጋ ለማዳን። ስለዚህ በዛ ምክንያት ጠንከር ያለ ጨዋታ መጫወት ነበረብን። የሊጉ መሪ ነው ፤ ዝም ብለህ የምትጫወተው ቡድን አይደለም። 19ኛ ጨዋታው ነው ሳይሸነፍ ፤ ስለዚህ ሜዳ ላይ ቆመህ ስራ ሳትስራ እና ሳትታገል ነጥብ ማግኘት አትችልም።

ስለክሌመንት ቦዬ ብቃት

“አቅሙ ይሄ ነው። አንዳንዴ መዘናጋት አለበት እንጂ ካዛ ውጪ ስታየው ልጁ በጣም ጥሩ አቅም ያለው። on and off..አንድ ቀን አለ አንድ ቀን ይጠፋል እንጂ በጣም አቅም አለው።”