የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ የምሽቱ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ለእኛ ጥሩ ነበር። በተለይ በመጀመርያው አርባ አምስት ሞውሊ እና ዓሊ ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ቢቀይሩ ኖሮ ጨዋታውን መቀየር እንችል ነበር። ከዚህ ውጪ እነርሱ በመጀመርያው አጋማሽ አንድ የጎል ሙከራ ነው ያደረጉት። እርሱንም ወደ ጎልነት ቀይረዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የነበረንን አጨዋወት ወደ 3-5-2 በመቀየር የአጥቂውን ሚዛን በመጨመር አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። ነገር ግን ብዙ እንደታየው ተጭነን እነርሱ አንድም ሙከራ ሳያደርጉ። ወደ ጎላችን አይደርሱም ማለት እችላለው። ከጉጉት የተነሳ ከአጨራረር ድክመት ተሸንፈን ወጥተናል። በቀጣይ ደግሞ አርመን እንመጣለን።
ስለቡድኑ የአጨራረስ ችግር
“ትክክል ነው። አንደኛ ማውሊ የረጅም ጊዜ በጉዳት ከጨዋታ መራቁ የተፈጠረበት ችግር አለ። ሁለተኛ ደግሞ አደም እና ዓሊ ገና ልጆች ናቸው። ከልምድ ማነስ ብዙ የሚስቷቸው ኳሶች አሉ። እርሱ ላይ በቀጣይ የተለዩ ልምምዶችን እየሰጠን ችግራችንን ለመቅረፍ እንሞክራለን።
በሁለቱም ዙር በአርባምንጭ ስለመሸነፋቸው
“ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። ሁለተኛው አርባ አምስት በጣም ነው በዝተው የሚከላከሉት በጣም ጥቅጥቅ ያሉ ናቸው። ያም ሆኖ በመስመር በሚመጡ ኳሶች ብዙ የጎል ሙከራዎችን አድርገናል ፤ ዕድሎችንም አግኝተናል። እነርሱን ወደ ውጤት አለመቀየራችን እንጂ ትክክል ነው የመከላከል ታክቲካቸውን ለመስበር ሞክረናል።”
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
ጨዋታውን በሚፈለገው መጠን ስለማስኬዳቸው
“ባለፈው በአስር ደቂቃ ሦስት ጎል የተቆጠረብን ስለዚህ ውጤት ለማስጠበቅ የምንችልበትን ዕድል ለመፍጠር ሞክረናል። ከዚህ በተሻለ ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር የእኛ መርህ ብልጫ በወሰድንበት ጊዜ ተደጋጋሚ ጎል ለማስቆጠር ነበር ያሰብነው። ግን ካሳለፍነው ነገር አንፃር ማሸነፋችን ለልጆቼ ትልቅ በራስ መተማመን የሚፈጥር በመሆኑ የዛሬው ውጤት የሚያመጣው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ዛሬ በጊዜ ነው አንድ ጎል ያስቆጠርነው። ይሄንን አስጠብቀን መውጣት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።
የአጥቂዎች ጉዳት መብዛት በቡድኑን የማጥቃት አቅም ስለመቀነሱ
“አዎ ጉዳቶች አጋጥመውናል። ሆኖም ግን ወጣት አጥቂዎች አሉ ሀቢብ ፣ ፍቃዱ እና ፀጋዬ ጠንካራ ናቸው የሚችሉትን አድርገዋል። በቀጣይም ጥረት ያደርጋሉ ብዬ አስባለው። ጎሎችም እያስቆጠሩ ነው። ስለዚህ በተወሰነ መልኩ ዛሬ ይዘነው የቀረብነው አቀራረብ ባላጋራን ወደ እኛ ሜዳ የሚያመጣ ባህሪ አለው። በቀጣይ ግን እንደየቡድኑ እንደኛ አቅም አንፃር እየቀያየርን የምንጫወትበት ነገሮች ይኖራሉ።
በሁለቱም ዙር ባህር ዳርን ስላሸነፉበት መንገድ
“እንግዲህ የቡድኖቹ የተለያየ አቀራረብ ነው የሚኖራቸው። ከእነርሱ ስድስት ነጥብ ነው የወሰድነው ሌሎችም አሉ ደግመን ያሸነፍናቸው። ባለፈው አንደኛው ዙር አሸንፈውን አሁን ደግሞ አስተካክለን ያሸነፍናቸው ቡድኖች አሉ ፤ ከባህርዳር ብቻ አይደለም። የትኛውንም ቡድን ስናገኝ ሦስት ነጥብ ፈልገን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው። በቀጣይ ይህን በሌሎች ላይ ለማሳካት ጥረት እናደርጋለን።”