ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በሊጉ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ታይተዋል ያላቸው የዲሲፕሊን ጥሰቶች ተከትሎ የቅጣት እርምጃ መውሰዱን አረጋግጠናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ክለቡ ከመከላከያ ጋር በነበረው የ19ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን የውድድር አመራሮችን በተደጋጋሚ አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው ፣ ወደ ጨወታ አመራሮች የውሃ ላስቲክ ስለመወርወራቸው እና የስቴዲየሙ ንብረት የሆኑ 20 ወንበሮችን ስለመሰባበራቸው ሪፖርት ቀርቦበታል ። ከዚህ በፊት የክለቡ ደጋፊዎች ቁሳቁስ ወደ ሜዳ በመወርወራቸው ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ
66 በተቁ 3(ሀ) መሰረት 50,000 ብር /ሃምሳ ሺ/ ቅጣት እንዲሁም የእለቱን የውድድር አመራሮች አፀያፊ ስድብ
በመሳደባቸው ኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተቁ 4(ሀ) መሰረት ብር 50,000 /ሃምሳ ሺህ/ በድምሩ ብር 100000 /አንድ መቶ ሺህ/ እንዲከፍልና በሪፖርት ላይ የቀረቡትን የተሰበሩ ንብረቶችን እንዲያሰራ ወይም ባለንብረቱ አስልቶ በሚያቀርበውን ዋጋ መሰረት ክፍያ እንዲፈፅም ወስኗል ።

በተጨማሪም መከላከያ ስፖርት ክለብ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው የ19ኛ ሳምንት እግር ኳስ መርሐ-ግብር ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለፀብ የሚያነሳሳ ድርጊድ ስለመፈፀማቸውና እና ከተፈቀደላቸው ስፍራ ውጪ በመንቀሳቀስ የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎችን በምልክት ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቦበታል። በዚህም ደጋፊዎች በፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተቁ 4(ሀ) ብር 50000 /ሃምሳ ሺህ/ ቅጣት እንዲከፍል ወስኗል ።