በቶማስ ቦጋለ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ በባህር ዳር ዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል። ንግድ ባንክ አንደኛውን ዙር በመሪነት ማጠናቀቁን ሲያረጋግጥ አርባምንጭ አሸንፏል። ሀዋሳ እና ኤሌክትሪክ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ረፋድ 3፡00 ላይ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ 1-1 ተጠናቋል
ሀዋሳዎች በአሥራ አንደኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን በምሕረት መለሰ ብቸኛ ግብ ከረቱበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ብዙኃን እንዳለ በቅድስት ዘለቀ ተተክታ ጀምራለች። ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በአሥራ አንደኛ ሳምንት አዳማ ከተማን 2-0 ከረቱበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።
ጨዋታው ብርቱ ፉክክር የሚኖርበት ፣ ብዙ የግብ ዕድሎች የሚፈጠሩበትና ለተመልካች አዝናኝ ይሆናል ተብሎ ቅድሚያ ግምት ቢሰጠውም በተቃራኒው የተቆራረጡ ቅብብሎች የበዙበት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብዙም ያልነበሩበት እና ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት ሆኖ አልፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ጨዋታው በጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዓይናለም አሳምነው ባስቆጠረችው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በቀኝ መስመር ከማዕዘን ተሻምቶ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች የተመለሰውና ፀሐይነሽ ጁላ ወደ ግብ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰው ነጻ ሆና ያገኘቸው ቱሪስት ለማ ባልተረጋጋ ሁኔታ ለማስቆጠር ብትሞክርም ኢላማውን ባለመጠበቋ ኳሱ የላይኛውን አግዳሚ ተጠግቶ ወጥቷል። ይሄም ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚፈልጉትን ሀዋሳዎችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።
ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ኤሌክትሪኮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተጋጋሚ መድረስ እና የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ ትኩረት ባጡበት ቅፅበት ያልታሰበ ግብ ያስተናገዱት ሀዋሳዎች ተረጋግተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ተቸግረዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው እና ምንትዋብ ዮሐንስ በቀኝ መስመር ይዘውት የገቡትን ኳስ ዓይናለም አሳምነው ነጻ ሆና ለነበረችው ሰላማዊት ጎሣዬ የማቀበል አማራጭ ቢኖራትም በራሷ ያደረገችውን ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ የላይኛው አግዳሚ መልሶባታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር የቻለችው ዓይናለም አሳምነው በጥሩ ሁኔታ የያዘችውን ኳስ ገፍታ ብታመቻችም ኃይል ባልነበረው ሙከራ ውጤታማ ሳትሆን ቀርታለች። 19ኛው ደቂቃ ላይ ምንትዋብ ዮሐንስ በግራ መስመር ያገኘችውን የቅጣት ምት ድንቅ አድርጋ ብትሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶባታል ይሄም በኤሌክትሪኮች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ቱሪስት ለማ ከቀኝ መስመር ያሻማችውና ትልቅ የግብ ዕድል ሊፈጥር የሚችል ኳስ ዘለቃ አሰፋ በፍጥነት በግንባሯ ገጭታ አስወጥታዋለች። ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል ቢደርሱም የተሳካ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት በ ሲሣይ ገ/ዋህድ ፣ ቱሪስት ለማ እና ከቆሙ ኳሶች ደግሞ በዙፋን ደፈርሻ የሞከሩት ሀዋሳዎች አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
የተለየ መልክ በነበረው በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳዎች ቅድስት ዘለቀን ቀይረው በማስገባት የኋላ ክፍላቸውን አጠናክረው በተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት ተጠግተው በመጫወት በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሆነው ሲቀርቡ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ አጋጣሚዎችን ያባከኑት ኤሌክትሪኮች ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዘዋል። ኢላማውን የጠበቀ የግብ ማግባት ሙከራ ብዙም ባልነበረበት ሁኔታ 68ኛው ደቂቃ ላይ ዘለቃ አሰፋ በነጻነት መና ላይ ጥፋት በመሥራቷ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ዙፋን ደፈርሻ በአግባቡ ተጠቅማ በማስቆጠር ሀዋሳን አቻ ማድረግ ችላለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል የጋለ የጨዋታ ስሜት የታየ ሲሆን በተሳኩ የግብ ሙከራዎች ላይ ግን ሁለቱም ደካማ ነበሩ። 79ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም አስረሳኸኝ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውና ኳስ አየር ላይ እንዳለ ኝቦኝ የን ወደግብ የሞከረችው ኃይል ያልነበረው ሙከራ የተሻለው የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
8፡00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘው ጨዋታ በአምናው ቻምፒዮን የበላይነት 6-1 ተቋጭቷል
በአሥራ አንደኛ ሳምንት አራፊ የነበሩት እንስት ፈረሰኞቹ በአሥረኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን በቤተልሔም መንተሎ ብቸኛ ግብ ከረቱበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በአሥራ አንደኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን 2-0 በሆነ ውጤት ከረቱበት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ትዕግሥት ያደታ ፣ አለምነሽ ገረመው እና ሎዛ አበራ በብዙዓየሁ ታደሠ ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ፀጋነሽ ወራና ተተክተው ጀምረዋል።
በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ንግድ ባንኮች ፍጹም የበላይነቱን የወሰዱ ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በ 6ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ባስቆጠረችው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ተረጋግተው ኳስ መሥርተው ለመውጣት የሚፈልጉት ፤ ነገር ግን ኳሱን በተጋጣሚ የግብ ክልል ይዞ መቆየት የከበዳቸው ፈረሰኞቹ የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራቸውን ያደረጉት 20ኛው ደቂቃ ላይ መስከረም መኮንን ከሳጥን ውጪ ወደግብ በሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ በያዘችው ኳስ ነበር። በተደጋጋሚ እንደፈለጉት በተጋጣሚ የግብ ክልል ኳስ ይዞ መግባት እና የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት ንግድ ባንኮች 32ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የሞከረች ኳስ በእቴነሽ ደስታ ተጨርፎ ተቆጥሮ መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።
በአንድ ደቂቃ ልዩነት የንግድ ባንኳ ሀሳቤ ሙሶ ዓይናለም ዓለማየሁ ላይ የሠራችውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፍቅራዲስ ገዛኸኝ በአግባቡ ተጠቅማ በማስቆጠር ፈረሰኞቹን አነቃቅታ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክራለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመግባት የቻሉት ፈረሰኞቹ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም።
42ኛው ደቂቃ ላይ ከትዕግሥት ያደታ የተቀበለችውን ኳስ መዲና ዐወል የግብ ጠባቂዋን መውጣት ተከትሎ ያደረገችው ቺፕ የላይኛውን አግዳሚ ተጠግቶ ወጥቶባታል ። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሰናይት ቦጋለ አረጋሽ ካልሳን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘ ጥሩ ኳስ አመቻችታ ብታቀበልም የአረጋሽን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ አስወጥታ የማዕዘን ምት አድርጋዋለች። የተሰጠውን የማዕዘን ምት እመቤት አዲሱ ከግራ መስመር ስታሻማ ትዕግሥት ያደታ በግንባሯ በመግጨት ማስቆጠር ችላለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ አረጋሽ ካልሳ ለማሻገር የሞከረችውን እህቴነሽ ደስታ ለማቋረጥ ብትጥርም የተመለሰውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ የነበረችው ሎዛ አበራ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት አጠናክራ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽም የንግድ ባንክ የበላይነት ተጠናክሮ ሲቀጥል 50ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። 55ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በግራ መስመር ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ስታሻማ ኳሱን ለማግኘት ትክክለኛ ቦታ ላይ የነበረችው መዲና ዐወል ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችላለች።
66ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ለመዲና ዐወል ጥሩ ኳስ አመቻችታ ብታቀብልም ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘችው መዲና ዐወል ሳትጠቀምበት ቀርታ አጋጣሚውን አባክናለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሰናይት ቦጋለ በድጋሚ ከሳጥን ውጪ ከቀኝ መስመር ይዛው የገባችውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም የላይኛው አግዳሚ መልሶባታል። ደቂቃው በሄደ ቁጥር በራስ መተማመናቸው እየቀነሰ የመጡት ፈረሰኞቹ በሶፋኒት ተፈራ ፣ ገብርኤላ አበበ እና ቤተልሔም መንተሎ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም አደገኛ ሙከራ ለማድረግ ግን እጅግ ሲቸገሩ ታይተዋል።
73ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ በድንቅ ሁኔታ ያሻገረችላትን ኳስ ሎዛ አበራ የግል ክህሎቷን ተጠቅማ ግብ ጠባቂዋን በማለፍ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ሐት ትሪክ መስራት ችላለች። ከጎሏ መቆጠር በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም የበላይ የነበሩት ንግድ ባንኮች ተረጋግተው ኳሱን ይዘው በመጫወት ጨዋታውን 6-1 በሆነ ውጤት መጨረስ ችለዋል።
10፡00 ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በአርባምንጭ 3-2 አሸናፊነት ፍፀሜውን አግኝቷል
አዲስ አበባ ከተማዎች በአሥራ አንደኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ከተረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ በቤተልሔም ዮሐንስ እና ንግስት ኃይሉ በመስታወት አመሎ ተተክተው ገብተዋል። አዞዎቹ በበኩላቸው በአሥራአንደኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ በምሕረት መለሰ ብቸኛ ግብ ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብጠባቂዋ ምሕረት ተሰማ በከንባቴ ካታሌ ፣ ወርቅነሽ መሠሎ በድንቅነሽ በቀለ ፣ መሠረት ወርቅነህ በርብቃ ጣሰው ተተክተው ጀምረዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ እና የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ አዞዎቹ 2ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ከሳጥን ውጪ በሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በአዲስ አበባ በኩል አርያት ሁዶንግ በአርባምንጭ በኩል ወርቅነሽ ሚልሜላ እና ትውፊት ካዲዮ የግብ እድል መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም።
16ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ከተማዋ ትርሲት መገርሣ በግራ መስመር ከቅጣት ምት የተገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም ደራ ጎሣ በግንባሯ ገጭታ ወደ ማዕዘን አስወጥታዋለች። ወዲያው በቀኝ መስመር የተሰጠውን የማዕዘን ምት በሻዱ ረጋሳ ስታሻማ ንግሥት ኃይሉ በግንባሯ በመግጨት ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ ተጭነው ለመጫወት የቻሉት አዞዎቹ ሲሆኑ በትዝታ ኃይለማርያም እና ወርቅነሽ መሠለ የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ በተለይም 30ኛው ደቂቃ ላይ ደራ ጎሣ ከወርቅነሽ ሚልሜላ የተቀበለችውን ኳስ ከረጅም ርቀት ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የያዘችባት የተሻለው ሙከራ ነበር።
40ኛው ደቂቃ ላይ ሠላማዊት ኃይሌ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ንግሥት ኃይሉ ኳሱን በትክክል መቆጣጠር ባለመቻሏ የግብ ዕድሏን አባክናለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት የአዞዎቹ ወርቅነሽ መሠለ እና ትውፊት ካዲዮ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ወርቅነሽ ወደግብ ብትሞክርም ኢላማውን መጠበቅ አልቻለችም። ይሄም የመጨረሻው የተሻለ ሙከራ ሆኖ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጠበቀው በላይ ፉክክር የታየበት እና ለተመልካች አዝናኝ የነበረ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሲሆን አዞዎቹ በተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዛ ብለው ኳሱን ተቆጣጥረው አጥቅተው መጫወት እና ብዙ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ አዲስ አበባዎች በበኩላቸው ወደራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመጫወት ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ጥረት ለማድረግ ሞክረው ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ቺፕ አድርጋው የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ በወጣው ኳስ የግብ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት አዞዎቹ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲያገኙ ወርቅነሽ መሠለ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ የተቀበለችው ድንቅነሽ በቀለ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ብትገናኝም ያገኘችውን ወርቃማ እድል ሳትጠቀምበት ቀርታ ኳሱን ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት ወደ ውጪ ማስወጣት ችላለች።
በተደጋጋሚ ወደተጋጣሚ የሜዳ ክፍል መግባት የቻሉት አዞዎቹ በወርቅነሽ መሠለ፣ ወርቅነሽ ሚልሜላ ፣ መቅደስ ከበደ እና ርብቃ ጣሠው ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። 62ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው የአዲስ አበባዋ ግብ ጠባቂ ቤተልሔም ዮሐንስ ከተፈቀደው የጊዜ ገደብ በላይ እጇ ላይ ኳስ በማቆየቷ ሁለተኛ ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥ ወርቅነሽ መሠለ ለ ወርቅነሽ ሚልሜላ አመቻችታላት ወርቅነሽ ሚልሜላ በተረጋጋ ሁኔታ ምርጥ ግብ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ ማድረግ ችላለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመውጣት የተቸገሩት አዲስ አበባዎች በትርሲት መገርሣ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ኳስ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ግብ ጠባቂ ይዛዋለች። 74ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው የገቡት አዞዎቹ ድንቅነሽ በቀለ የግብ ጠባቂዋ ስህተት ተጨምሮበት ያገኘችውን ኳስ ለመሠረት ወርቅነህ አመቻችታ ስታቀብል ግብ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው መሠረት ወርቅነህ ባስቆጠረችው ግብ ከኋላ ተነስተው መሪ ሊሆኑ ችለዋል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ጺዮን ሳህሌ በድንቅ ብቃት ያሻገረችውን ኳስ ተቀይራ የገባችው መሠረት ማቴዎስ ከሳጥን ውጪ በአስገራሚ አጨራረስ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ስታጠናክር ሁለቱ የጫዋቾች ጎሉ ላይ ባሳዩት ጥምረትም የአሰልጣኙን ውጤታማ የተጫዋች ቅያሪ ማረጋገጥ ችለዋል።
በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት የአዲስ አበባዋ ትርሲት መገርሣ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ የተገኘውን የቅጣት ምት በድንቅ ብቃት አስቆጥራ ቡድኗን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ችላለች። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማዎች የተለያዩ የግብ እድሎች ቢፈጥሩም አዞዎቹ ከራሳቸው የግብ ክልል ጥቅጥቅ ብለው በመጫወት እና የሚያገኙትን ኳስ አርቀው በማውጣት ውጤታቸውን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ሰዓት በማባከን ምክንያት የአዞዎቹ አምበል ወርቅነሽ ሚልሜላ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብታ ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።