ነገ ምሽት በሚደረገው ጨዋታ ላይ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስር ነጥብ ልዩነት ሊጉን መምራት በቀጠለበት በዚህ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በዚህ ሳምንት ተጠበቂ ከሆኑ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው። ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት የገጠመው ሀዋሳ ከተማ ከነገ ተጋጣሚው ያለውን ርቀት ቀንሶ አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ከሁለት እስከ አምስት ባለው ደረጃ ላይ ከሚታየው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ሌላ ሽንፈት ማስተናገድ ወደ ኋላ ሊያስቀረው ሰለሚችል ለጨዋታው ከፍ ያለ ትርጉም ይሰጠዋል። ያለሽንፈት የሊጉን ሁለት ሦስተኛ የጨረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በዚሁ መንፈስ ለመቀጠል አሁንም ሙሉ ነጥብ ሰብስቦ ልዩነቱን ማስፋት ዋና ዓላማው ይመስላል።
ይህ ጨዋታ ያለው ትርጉም ይበልጥ ለሀዋሳ ከተማ ከፍ ያለ መሆኑ ሜዳ ላይ የሚኖሩ ፍልሚያዎችንም ከኃይቆቹ አንፃር መመልከት የተሻለ ይሆናል። ሌላኛውን የቅርብ ተፎካካሪያቸው ሲዳማ ቡናን በመርታት መሪነታቸው ማስቀጠል የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚህም ሳምንት ጨዋታ ተመሳሳይ እርምጃ ለመራመድ የሚያቅዱ ሲሆን በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ከሚፈጠር ጫና አንፃር ግን ከተጋጣሚያቸው ቀለል ባለ ጫና ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል። በመሆኑም ምንም እንኳን ሀዋሳ ከተማ ጠንከር ባሉ ጨዋታዎች ላይ ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ የጨዋታ መንገድን ሲከተል ቢታይም በነገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከተጋጣሚያቸው ውጤት መሻት መነሻነት ለሚኖረው የማጥቃት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ ለፈጣን ጥቃት የተመቹ ቅፅበቶችን የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል።
ለሀዋሳ ከተማ በነገው ጨዋታ ጥንቃቄ አዘል የሆነ በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ መንገድን መከተል ቀላል ላይሆንለት ይችላል። ይህም በቅርብ ጨዋታዎች ከኋላም ከፊትም የታየበት ድክመት እንደ ከዚህ ቀደሙ ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድን በውጤታማነት ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆኑን ከማሳየቱ ባለፈ ከተጋጣሚው ጠንካራ ጎን አሳልፎ ሊሰጠው እንደሚችልም ይነግረናል። ከፊት የተባረክ ሄፋሞ ድንቅ ጥረት እንዳለ ሆኖ ሀዋሳ ከሦስቱ አጥቂዎች ጥምረት ውጪ ሲሆን አስፈሪነቱ ቀንሶ መታየቱ ነገም የኤፍሬም አሻሞን አለመኖር እና የመስፍን ታፈሰ ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሊያደርግ ከመቻሉ አንፃር ስናየው ክፍተቱ በቀላሉ ስለመሸፈኑ ለመናገር አስቸጋሪ ይሆናል። ከኋላ ደግሞ ከመሀል በቂ ሽፋን እያገኘ ያልሆነው የተከላካይ መስመር በአመዛኙ ጥንቃቄን በመረጠበት የሆሳዕናው ጨዋታ እንኳን የታየበት የአቋቋም እና የግለሰባዊ ስህተቶች ለነገው ጨዋታ ጥሩ ምልክት የሚሰጡ አልነበሩም።
ከእነዚህ ነጥቦች አንፃር ለቅድመ ጨዋታ ዝግጅት የሀዋሳ የአሰልጣኞች ቡድን ብርቱ ዝግጅት እንደሚጠብቀው መረዳት እንችላለን። በቅዱስ ጊዮርጊስ ካምፕ በኩል በእርግጥ ቡድኑ ጥሩ የመከላከል መዋቅር ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በቀላሉ አሸንፎ መውጣት እንደሚከብደው በመከላከያው እና በሲዳማው ጨዋታ መመልከታችንን እንደ ድክመት መውሰድ እንችላለን። ሆኖም ይህ ለጊዮርጊስ ነገ ችግር እንዲሆን ኃይቆቹ በቅርብ ጨዋታዎች በዚህ ረገድ የታየባቸውን ክፍተት አርመው የፈረሰኞቹን አደገኛ መልሶ ማጥቃት ለመቋቋም በሚያስችል የጨዋታ ዕቅድ መግባት እና በተጨዋቾች የግለሰብ ብቃትም ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። ያም ቢሆን ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታ በተጨማሪ በተለያዩ ተጫዋቾች አስቆጣሪነት የቆሙ ኳሶችን ጥቅም ላይ እያዋለ ያለበት ጥንካሬው በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድበት እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ አስክቶ መውጣት እንደሚያስችለው መረሳት የለበትም።
በጨዋታው ሀዋሳ ከተማው ከአዲስዓለም ተስፋዬ በተጨማሪ ኤፍሬም አሻሞን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የማያሰለፍ ሲሆን የግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ ከጉዳት መመለስም አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ መስፍን ታፈሰ እና ዳንኤል ደርቤ ግን አገግመው ለነገው ጨዋታ እንደሚደርሱ ታውቋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሀይደር ሸረፋ እና ሱለይማን ሀሚድ ቅጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን ልምምድ የጀመረው አቤል ያለው መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።
ጨዋታውን አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ይበቃል ደሳለኝ እና እሱባለው ሙሉጌታ በረዳትነትን ተካልኝ ለማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ43 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በግንኙነቱ 74 ጎሎችን በማስቆጠር 26 ድል ሲያስመዘግብ ሀዋሳ ከተማም 34 ጎሎችን በማስቆጠር 7 ድል አለው። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን ያገኙ ናቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)
ዳግም ተፈራ
ካሎንጂ ሞንዲያ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ
ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – አብዱልባስጥ ከማል – መድሃኔ ብርሃኔ
ተባረክ ሄፋሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሄኖክ አዱኛ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ያሬድ ሀሰን
ጋቶች ፓኖም – የአብስራ ተስፋዬ
አቤል ያለው – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ
አማኑኤል ገብረሚካኤል