በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ተጠባቂው የአዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በፋሲል ተካልኝ የሚመራው አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ 11 ተመራጮች ላይ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አምበላቸው ዳዋ ሆቴሳ በአቡበከር ወንድሙ ተተክቷል። በሲዳማ ቡና በኩል በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ስብስብ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እንዲሁ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም አማኑኤል እንዳለ እና ብርሃኑ አሻሞ ወጥተው በምትካቸው ደግፌ ዓለሙ እና ይገዙ ቦጋለ በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ተመራጭ ሆነው ጀምረዋል።
ቀዝቀዝ ያለ አጀማመርን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ነበር። በ2ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ይገዙ በማይታመን መልኩ ባመከናት አጋጣሚ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ ይገዙ ቦጋለ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል በንፅፅር የተሻለ የማጥቃት ጥረቶችን ሲያደርጉ አስተውለናል።
በጠሩ የግብ ዕድሎች ረገድ ውስንነት በነበረበት የጨዋታ አጋማሽ ሲዳማዎች በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው ወደ ውሃ ዕረፍት ከማምራቱ አስቀድሞ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ጀማል ጣሰው በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ የተገኘውን ዕድል ሳላዲን ሰዒድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በአንፃሩ ወደ ጎል በመድረስ እና ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ በተጋጣሚያቸው ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማ ከተማዎች በ29ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ከተሻማ ኳስ አዲስ ተስፋዬ ያሸነፈውን የመጀመሪያ ኳስ ተጠቅሞ ሚሊዮን ሰለሞን ወደ ግብ ገጭቶ የሞከረው እንዲሁም በ42ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አቡበከር ወንድሙ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ በአዳማ በኩል በአጋማሹ የነበሩ አስቆጭ እድሎች ነበሩ።
በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በ37ኛው ደቂቃ ሳልሀዲን ሰዒድ ከግቡ ትይዩ የተገኘን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግቡ የላካት እና ጀማል ጣሰው ያዳነበት ኳስ ሌላኛው የአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ቀስ በቀስ መነቃቃቱን የቀጠለው አጋማሹ አስገራሚ አጨራረስን ያስመለከተን ነበር።
አዳማ ከተማዎች በአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ዒላማውን በጠበቀው የመጀመሪያ ሙከራቸው መሪ መሆን ችለዋል። በ44ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከተነጠቀው ኳስ መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ ያደረሰውን ኳስ ነፃ ሆኖ የደረሰችው አቡበከር ወንድሙ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም ሁኔታ በመምታት አስቆጥሯል።
ነገር ግን የአዳማ ደስታ መዝለቅ የቻለው ለሰከንዶች ነበር ፥ ምክንያቱም በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች አቻ መሆን ችለዋል። ፍሬው ሰለሞን ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቆመ ኳስ ሳላዲን ሰዒድ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመራ አስችሏል።
በፍላጎት ደረጃ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አውንታዊ መሻሻሎችን በተመለከተንበት የሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ጥረት ቢያደርጉም በመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ የነበራቸው የውሳኔ ችግር አንገት የሚያስደፋ ነበር። በተመሳሳይ በአጋማሹ በርከት ያሉ አደገኛ ጥፋቶችንም እንዲሁ የታዘብንበት ነበር።
በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻለ ድርሻ የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ በአስገዳጅ ሁኔታ የተጫዋቾች ለውጥ እንዲሁም የአደራደር ለውጥ በማድረግ ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ 70ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትኩት የሰራውን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን አጋጣሚ አሜ መሀመድ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በጊት መጨናገፉን ተከትሎ የተመለሰውን ኳስ አብዲሳ ጀማል አግኝቶ አስቆጠረው ሲባል ያመከናት ኳስ የአጋማሹ ተጠቃሽ አደገኛ አጋጣሚ ነበረች።
በርከት ያሉ ጥፋቶች በበዙበት አጋማሽ በከተማቸው የመጨረሻ ጨዋታቸውን በድል ለመደምደም ፍላጎት የነበራቸው አዳማዎች በአውንታዊ ለውጦች ታግዘው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ የተንጠለጠለው የጨዋታ ዕቅዳቸው ውጤታማ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች በ34 ነጥብ ለጊዜውም ቢሆን ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ማለት የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ26 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።