ሁለተኛው የዓበይት ጉዳይ ፅሁፋችን በ22ኛው ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የተካተቱበት ነው።
👉 ኢትዮጵያ ቡና እና አቡበከር ናስር
አቡበከር ናስር እና የኢትዮጵያ ቡና ጋብቻ በስምምነት ሊጠናቀቅ የስምንት ጨዋታዎች ዕድሜ ብቻ ቀርተዋል። ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ እየተሰናዳ የሚገኘው ተጫዋቹ ለኢትዮጵያ ቡና ካበረከተው እና እያበረከተ ከሚገኘው አስተዋፅዖ አንፃር ‘ህይወት ከአቡበከር ናስር ውጪ በኢትዮጵያ ቡና ምን ሊመስል ይችላል ?’ የሚለው ጉዳይ ከወዲሁ ይጠበቃል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡና 44 ግቦች አስቆጥሮ 2ኛ ደረጃን በመያዝ በአፍሪካ ካንፌደሬሽን ዋንጫ ላይ ለመካፈል ሲበቃ አቡበከር በግሉ 29 (66%) የሚሆነውን ግብ በማስቆጠር አይተኬ ሚና ተጫውቷል። ተጫዋቹ ዘንድሮም ተፅዕኖው የቀነሰ ቢመስልም አሁንም ግን የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ሆኖ ቀጥሏል። በሊጉ ቡድኑ እስካሁን 18 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 9 (50%) ግቦች የተገኙት ከአስር ቁጥር ለባሹ ነው። ከአቡበከር ቀጥሎ የቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ ከሆነው ዊልያን ሰለሞን በስድስት ግቦች ልቆ የመገኘቱ ጉዳይ በራሱ አሁንም ለቡድኑ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ የሚገልፅ ቁጥር ነው።
ነገር ግን የአቡበከር ናስርን ተፅዕኖ ከግቦች አንፃር ብቻ መመልከት ተገቢ እንዳልሆነ የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የድሬዳዋ ከተማው ድል ዓይነተኛ ማሳያ ነበር። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በጉዳት ሳቢያ ከስብስብ ውጪ ሆኖ ቢቆይም ዳግም በተመለሰበት ጨዋታ ቡድኑ ያሸነፈባቸውን ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ ባለፈ ግን በመሰረታዊነት በጨዋታው የታዘብነው ጉዳይ ቡድኑ አቡበከር ናስር ሲኖር እና ሳይኖር ያለው አጠቃላይ ይዞታ ፍፁም የተለያየ የመሆኑ ጉዳይ ነው። እሱ ሜዳ ላይ ሲኖር በተለየ የራስ መተማመን የሚጫወት ተፎካካሪ ቡድን ሲመስል በተቃራኒው ያለእሱ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ደግሞ በተቃራኒው ለብዙ ጉዳዮች መፍትሔ ለማበጀት የተቸገረ “ስስ” ቡድን ሲሆን ተመልክተናል።
በጥቅሉ አቡበከር በሜዳ ላይ በቆየባቸው 1406 የጨዋታ ደቂቃዎች ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት ያን ያህል የሚያኩራራ ባይሆንም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያለ አቡበከር ናስር ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ማለትም ከጅማ አባ ጅፋር እና ሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ውጪ በሦስቱ (ከመከላከያ ፣ አዳማ እና ሀዋሳ) ሽንፈት የማስተናገዱ ጉዳይ ቡና ያለወሳኙ አጥቂው እንዴት እንደሚቸገር ማሳያ ነው።
አሁንም ከጉዳቱ መሉ ለሙሉ ያለገገመው ተጫዋቹ ከህመም ጋር እየተጫወተ እንደሚገኝ በድሬዳዋው ጨዋታ ላይም መታዘብ ችለናል። ከዚህ ባለፈም ትልቁ ስጋት የሚሆነው ተጫዋቹ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ከቡድኑ የመለየቱ ነገር ሲሆን ‘ይሄ ቡድን ያለእሱ እንዴት ይሆናል ?’ የሚለው ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ይሆናል።
👉 ሄኖክ አየለ ግብ ማምረቱን ቀጥሏል
ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ለማግኘት የተቸገረው ድሬዳዋ ከተማ አሁን ላይ በሄኖክ አየለ ምላሽ እያገኘ ያለ ይመስላል።
11ኛ ጨዋታውን ለቡድኑ ያደረገው ሄኖክ በስድስቱ ጨዋታዎች ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በውድድር ዘመኑ በቋሚነት በአምስት ጨዋታዎች ብቻ ሲጀምር አራቱ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የተጫወተባቸው ጨዋታዎች በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ነበሩ።
በአዲሱ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ ወዲህ የፊት መስመሩን የመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ሄኖክ አየለ አሰልጣኙ የጣሉበትን ዕምነት መልሶ እየከፈለ ይገኛል። ድሬዳዋ ከተማ ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች አራት ግብ ማስቆጠር የቻለው ሄኖክ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ አጥቶ ለቆየው ድሬ በ495 ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታው በአምስት ግቦች የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችሏል።
በተደጋጋሚ ጉዳት የእግርኳስ ህይወቱ በሚጠበቀው ደረጃ መጎምራት ተቸግሮ የቆየው ተጫዋቹ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ቀስ በቀስ ራሱን በሊጉ እያደላደለ ይገኛል። ባለፉት ሳምንታት እያሳየ በሚገኘው ታስፋም አሁንም ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት የሄኖክን ግልጋሎት አጥብቆ ይፈልጋል።
👉 ቢኒያም በላይ መድመቁን ቀጥሏል
በዘንድሮ የመከላከያ ጉዞ ውስጥ የማይተካ ሚናን እየተወጣ የሚገኘው ቢኒያም በላይ አሁንም ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።
በጨዋታ ሳምንቱ መከላከያ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበበትን ውጤት ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ሲቀዳጅ አማካዩ እስራኤል እሸቱ እና አዲሱ አቱላ ያስቆጠሯቸውን ግቦች አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
በጨዋታው በግቦቹ ላይ ከነበረው ተሳትፎ ባለፈ ለቡድኑ በመከላከሉ ወቅት ይሰጥ የነበረው አበርክቶ በራሱ አድናቆት የሚቸረው ነው። እንደ ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ውስንነቶች በነበረበት መከላከያ ውስጥ ብቸኛ የተስፋ ጭላንጭል የነበረው ቢኒያም አሁን ላይ ግን ጦሩ በጨዋታ ዕቅድ እና በአተገባበር ማጥቃቱ ላይ እየተሻሻለ መምጣቱ አቅሙን ይበልጥ የሚያሳይበት ዕድልን ፈጥሮለታል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ሲረቱ ግብ በማስቆጠር በውድድር ዘመኑ ከመረብ ያገናኛቸው ግቦችን መጠን ሦስት ያደረሰው ቢኒያም በላይ አሁን ደግሞ ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶችን ማስማዝገቡ ከጥረት ባለፈ ውጤታማ የማጥቃት ተሳትፎ ላይ እንዲገኝ ያደረገው መሆኑ በቀጣይ ጨዋታዎች መከላከያ ይበልጥ አስተማማኝ ወደ ሆነ ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያግዘው እንደሆነ ይታመናል።
👉 ወደ ሜዳ የተመለሱት ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች
የጨዋታ ሳምንቱ ከሜዳ ርቀው የሰነበቱት ሙሴ ገብረኪዳን እና ሴኮባ ካማራ ወደ ሜዳ የተመለሱበት ነበር።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ የነበረው ሙሴ ገብረኪዳን ዳግም በፕሪሚየር ሊጉ የመሰለፍ ዕድልን አግኝቶ ተመልክተናል። በፕሪሚየር ሊጉ ቤተኛ የነበረው እና በ2009 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደ ወዲህ በደሴ ከተማ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ቆይታ የነበረው ግብ ጠባቂው በክረምቱ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚመልሰውን ዝውውር መፈፀሙ ይታወሳል። በዝውውሩ ወደ መከላከያ ከመጣ ወዲህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስከ 21ኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ የክሌመንት ቦዬ ተጠባባቂ በመሆን ያሳለፈው ሙሴ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያውን ዘጠና ደቂቃ ዳግም በፕሪሚየር ሊጉ በቋሚዎች መካከል ማሳለፍ ችሏል።
በተመሳሳይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ አዳማ ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ የቡድኑ ተቀዳሚ ግብ ጠባቂ የነበረው ሴኮባ ካማራም እንዲሁ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ረዘም ካሉ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ተመልሶ ተመልክተናል። በመጀመሪያዎቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታትን የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ የነበረው ግብ ጠባቂው አዳማዎች በ3ኛው የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ 1-0 ከተሸነፉ በኋላ ከ19 የጨዋታ ሳምንታት በኋላ የውድድር ዘመኑን አራተኛውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል። ተጫዋቹ ለዕረፍት ወደ ሀገሩ ካመራ በኋላ የጠፋበትን ፖስፖርት እንደአዲስ ለማውጣት ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀበት መሆኑ ከቡድኑ ጋር አራርቆት መቆየቱ ከክለቡ በኩል ለተጨዋቹ ከአሰላለፍ ጠፍቶ መቆየት የተሰጠ ምክንያት ነው።
👉 ለቡድኑ ተስፋ ለመፈንጠቅ እየጣረ የሚገኘው ጌቱ ኃይለማርያም
ሰበታ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የሰበታ ከተማው አምበል ጌቱ ኃይለማርያም በጨዋታው ቡድኑ መሉ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ የተቻለውን ሲጥር ተመልክተናል። ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ሰበታዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በተደጋጋሚ ዕድሎችን ከመስመር በተለይም ጌቱ ኃይለማርያም ከተሰለፈበት የቀኝ መስመር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ጌቱ ኃይለማርያም በቀኝ እግሩ በቀጥታ ከሚያደርሳቸው ተሻጋሪ ኳሶች ባለፈ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ኳሱን ከተፈጥሮአዊ እግሩ ወደ ግራ በመሳብ በግራ እግሩ ባሻገራቸው ኳሶች ለቡድን አጋሮቹ ተደጋጋሚ ዕድልን ፈጥሯል። የቡድኑ አጋሮቹ ወደ ጎልነት መቀየር ሳይችሉ ቀሩ እንጂ አጋጣሚዎቹ ይህ ቀረሽ የማይባሉ ነበሩ።
ተጫዋቹ ከተሻጋሪ ኳሶቹ ባለፈ በአንድ አጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ጥሩ ሙከራን አድርጎ በሀዋሳው ግብ ጠባቂ የመከነበት ሲሆን በጥቅሉ በዘጠና ደቂቃ ግን ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ የተቻለውን ጥረት ሲያደርግ አስተውለናል።
👉 የግብ ደመነፍስ ያለው ፈቱዲን ጀማል
ባህር ዳር ከተማ በደጋፊው ፊት ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ምንም እንኳን አቻ ቢለያይም የፈቱዲን ጀማል ጥረት ግን እጅግ አስደናቂ ነበር።
በጨዋታው በመሀል ተከላካይነት የጀመረው ፈቱዲን ጀማል በመከላከሉ ወቅት የወላይታ ድቻዎችን ረጃጅም ኳሶች በማክሸፍ እንዲሁም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወላይታ ድቻዎች የመልሶ ማጥቃትን ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ እጅግ ወሳኝ የሆኑ የኳስ ማቋረጦችን በማድረግ ጥሩ የመከላከል አቋም አሳይቷል።
ከዚህ ባለፈ በጨዋታው በማጥቃቱ ረገድ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ቡድኑ ሀሳብ ሲያጥረው ፈቱዲን ኃላፊነት ወስዶ ወደ ፊት በመጠጋት ተጨማሪ አማራጭ ለመሆን ጥረት ያደረገ ሲሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ሳይጠበቅ ከረጅም ርቀቶች ወደ ግብ ያደረጋቸው ሙከራዎች አደገኞች ነበሩ። በተለይም ከመሀል ሜዳ አቅራቢያ በቀጥታ የፅዮን መርዕድን መውጣት ተከትሎ ያደረጋት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ድቻ አጋማሽ በጥልቀት ገፍቶ ገብቶ ያደረጋት እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ በማጥቃቱም የነበረውን ተሳትፎ ያሳያሉ።
ከወትሮው በተሻለ ከፍተኛ መነሳሳት ጨዋታውን ያደረገው ፈቱዲን ጀማል ቡድኑን ብሎ ሜዳ የታደመው የክለቡ ደጋፊ ተደስቶ እንዲወጣ ለማድረግ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው።
👉 ከቀይ ካርዱ አብዝቶ የተማረው ሀይደር ሸረፋ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በጠባብ ውጤት ሲረታ በሁለተኛው አጋማሽ ባልተገባ ድርጊት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዶ የነበረው ሀይደር ሸረፋ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሷል።
ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የተመለሰው ሀይደር በጨዋታው በተጋጣሚ በተወሰደባቸው ብልጫ መነሻነት የዳኝነት ውሳኔዎችን አስከትሎ በከፍተኛ ስሜት ውሳኔዎችን ሲቃወሙ የነበሩትን የቡድን አጋሮቹን በማረጋጋት ረገድ ከወትሮው የተለየ ጥረትን ሲያደርግ ተመልክተናል።
ከአንድ የጨዋታ ሳምንት በፊት በራሱ ላይ የደረሰው በሌሎች እንዳይደገም ሀይደር በጨዋታው የቡድን አጋሮቹን ካልተገባ ካርድ ለመታደግ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው። ከተጫዋቹ የዚህ ሳምንት ድርጊት በመነሳት ሌሎች የቡድን አምበሎችም ከቡድን አጋሮቻቸው ሰከን ብለው ነገሮችን በአስተውሎት መመልከት እና መራመድ ይጠበቅባቸዋል።
👉 ደጉ ደበበ ተመልሷል
ባለፉት የጨዋታ ሳምንታት ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርዶ የነበረው ደጉ ደበበ ዳግም ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ተመልሷል።
በ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን 1-0 ከረታበት ጨዋታ ወዲህ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው ተጫዋቹ ከጉዳት ከተመለሰ በኋላም እንዲሁ ቦታውን መልሶ ማግኘት ሳይችል ቆይቶ ነበር። በሌላ በኩል የወጣቱ ተከላካይ መልካሙ ቦጋለ እና አንተነህ ጉግሳን ጥምረት ለመንካት ያልደፈሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በባለፈው የጨዋታ በፋሲል ከነማ ሲሸነፉ ግን ሜዳ ላይ የተመለከቱት ነገር ደስተኛ እንዳላደረጋቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል። ቡድኑ የተከላካይ መስመር በተወሰነ መልኩ ልምድ እና መረጋጋት ይጎድለው እንደነበር ከፋሲሉ ሽንፈት በኋላ የተናገሩት አሰልጣኙ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወጣቱን መልካሙን አስወጥተው ደጉ ደበበን ተክተዋል።
በውሳኔውም የውድድር ዘመኑን 13ኛ ጨዋታውን ያደረገው ደጉ ደበበ ባለመኖሩ ቡድኑ አጥቶት የነበረውን የኋላ ክፍልን መረጋጋት በባህር ዳሩ ጨዋታ አግኝቶ ተመልክተናል። ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ ስለ ልምድ አጨዋወት ደጋግመው ሲያነሱ የሚደመጡት አሰልጣኝ ፀጋዬ ከዚህ በኋላ ባሉት ጨዋታዎች ደጉን ዳግም ወደ ተጠባባቂ ወንበር ያወርዱታል ተብሎ አይጠበቅም። ምናልባት መልካሙን መጠቀም ካስፈለገም ከደጉ ጉዳት በፊት ይጠቀሙበት የነበረውን የኋላ ሦስት ተከላካዮች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ይገመታል።
👉 ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው አዲሱ አቱላ
ከ2009 አንስቶ በሲዳማ ቡና የተለያዩ የዕድሜ እርከን ቡድኖች እና በዋናው ቡድን ቆይታ ማድረግ የቻለው ወጣቱ የመስመር አጥቂ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን ለቆ መከላከያን ከተቀላቀለ ወዲህ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ተቸግሮ ቢቆይም አሁን ላይ ግን የተሻለ ድርሻ ኖሮት እየታየ ነው።
አዲሱ ምንም እንኳን ተፈጥሮአዊ የመጫወቻ ቦታው የመስመር አጥቂነት ቢሆንም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ስር እንዳለፉት ሌሎች ተጫዋቾች ሁሉ በተለያዩ የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። አሁን ላይ በአማካይ ስፍራ ላይ እየተሰለፈ የሚገኘው ተጫዋቹ በ15 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል አብዛኞቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ግን ከተጠባባቂነት እየተነሳ ያደረጋቸው ናቸው።
በመጀመሪያ አስራ አንድ ጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም ከሰሞኑ ግን የተሻለ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከባህር ዳር ጋር ነጥብ ሲጋራ ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት ቡድኑን አቻ ያደረገች ወሳኝ ግብን ሲያስቆጥር በመቀጠል በነበሩት እና በቋሚነት በጀመረባቸው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታም እንዲሁ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ከግቦች ባለፈ ከፍ ባለ ፍላጎት እና የታታሪነት ደረጃ እየተጫወተ የሚገኘው አዲሱ አቱላ በመከላከያ አዲሱ ማጥቃትን መሰረት ባደረገው የ4-3-3 አደራደር ውስጥ አይነኬው ስምንት ቁጥር እየሆነ ይገኛል።
👉 በሀዘን የተሰበረው ውሀብ አዳምስ
ወልቂጤ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን መሪ ያደረገችውን ግብ በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠረው ወሀብ አዳምስ ከግቧ መቆጠር በኋላ ያሳየው ስሜት ልብ የሚነካ ነበር።
እጅግ አስገራሚ የሆነችን ኳስ ወደ ራሱ መረብ ገጭቶ ያስቆጠረው ተጫዋቹ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ በከፍተኛ የድንጋጤ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሜዳ ላይ ወድቆ የተመለከትነው ሲሆን ስሜቱ በእንባ የታጀበ ጭምር ነበር። ኋላ ላይም አሰልጣኙ እንደተናገሩት በቀሪ የጨዋታ ደቂቃዎች ተጫዋቹም በሜዳ ላይ መረጋጋት ተስኖት ተመልክተናል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የቡድን አጋሮቹ የተጫዋቹን ስሜት በሚክስ እና ወደ አቻነት በሚመልሳቸው መልኩ አውንታዊ ምላሽ ያሳያሉ ተብሎ ቢጠበቅም በመጨረሻ ደቂቃ ከተቆጠረችው የጫላ ተሺታ ወሳኝግብ ውጪ የተፈለገውን ከፍ ባለ ጫና ደጋግሞ የማጥቃት ምላሽን ሳያስመለክቱ ቀርተዋል። የጋናዊው ተከላካይ የሀዘን ስሜት ለቡድኑ ካለው መውደድ የመነጨ እንደሆነ የአሰልጣኝ ተመስገን አስተያየት ላይ የሰማን ቢሆንም ራስ ላይ ማስቆጠር በየትኛውም ተጫዋች ላይ ሊፈጠር የሚችል ከመሆኑ አንፃር ውሀብ አዳምስ በቀጣይ ጊዜያት የተሻለ ልበ ሙሉነት ላይ በመገኘት መሰል የስሜት ዝቅታዎች ከሚፈጥሩት ተጨማሪ ስህተት ለመዳን ስሜቱን መቆጣጠር ይኖርበታል።