የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ምርጥ አቋማቸውን ያሳዩ ተጫዋቾችን መርጠናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ዳግም ተፈራ – ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ከተማ በሰበታ ከተማ ሰፊ ብልጫ ቢወሰድበትም አንድ ነጥብ አሳክቶ እንዲወጣ የግብ ጠባቂው ዳግም ብቃት እጅግ አስፈላጊው ነበር። በጊዜ አጠባበቅም ሆነ ዕድሎችን በማምከን ንቁ ሆኖ የዋለው ዳግም በተለይም በመጨረሻ ጌቱ ኃይለማሪያም እና ዱሬሳ ሹቢሳ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ያዳነበት መንገድ አስገራሚ ነበር።
ተከላካዮች
ጌቱ ኃይለማሪያም – ሰበታ ከተማ
የሰበታው አምበል ጌቱ ቡድኑን በመምራት እና በቦታው የሚጠበቅነትን በማድረግ ሰበታ ወሳኝ ሦስት ነጥቦችን እንዲያሳካ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ነበር። የቡድኑን የቀኝ መስመር ከኋላ በመነሳት በመምራት ጥቃት በማስጀመር እና ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ሳጥኑ በማድረስ ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ጌቱ ራሱም ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
ፈቱዲን ጀማል – ባህር ዳር ከተማ
የባህር ዳሩ የመሀል ተከላካይ በዚህ ሳምንት በራሱ ሳጥን ውስጥ ካለው ከዋና ኃላፊነቱ በላይ የቡድኑን ውጤት ለመቀየር የወደው ተነሳሽነት ትኩረትን የሚስብ ነበር። ተጫዋቹ የድቻን መልሶ ማጥቃቶች ከማቋረጥ ባለፈ በተደጋጋሚ ወደ ፊት ተስቦ በመሄድ ማጥቃቱን ሲያግዝ ከቡድኑ አጥቂዎች በላይ የማጥቃት ተሳትፎ ኖሮት ታይቷል። በዚህም በግቡ ብረት የተመለሰበትን ሙከራ ጨምሮ በሦስት አጋጣሚዎች አደጋ መጣል ችሎ ነበር።
ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ጋናዊው ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳማ ከተማ ከፍ ያለ ጫና ባስተናገደበት ጨዋታ ከምኞት ደበበ ጋር በተረጋጋው ጥምረቱ በስክነት ጨዋታውን ከውኖ ጨርሷል። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የበላይ በመሆን የአዳማን ቅብብሎች ያቋርጥ የነበረው ፍሪምፖንግ ከመከላከሉ ባለፈ ከጥልቅ ቦታ ላይ በላከው ኳስ አንድ ያለቀለት የግብ ዕድልም መፍጠር ችሎ ነበር።
ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በግራ እና በቀኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ላይ በወጥነት እየተሰለፈ የሚገኘው ሄኖክ ዳግም ለጊዮርጊስ ነጥብ ማግኘት ምክንያት ሆኗል። ብቸኛዋ የከነዓን ማርክነህ ጎል የተቆጠረችበን ኳስ እንደተለመደው ከቆመ ኳስ ያደረሰው ሄኖክ በመከላከሉም ረገድ የተሰለፈበትን ኮሪደር ከጥቃት ለመጠበቅ በትጋት ተጫውቷል።
አማካዮች
ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ
ናይጄሪያዊው ተከላካይ አማካይ ቡድኑ ከውጤት ቢርቅም በግሉ የሚያደርገው መልካም እንቅስቃሴ በዚህ ሳምንትም ተደግሟል። ማጥቃትን የሚያስጀምሩ ረጅም ኳሶቹ በስፋት ባይስተዋሉም የወልቂጤ ከተማ የኳስ ፍሰት እንዳይሰምር በተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን ያቋርጥ የነበረበት መንገድ አዲስ አበባ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጫና ውስጥ እንዳይገባ እና ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች እንዳያስተናግድ ወሳኝ ነበር።
አዲሱ አቱላ – መከላከያ
የቀድሞው የሲዳማ ቡና የመስመር አጥቂ በመከላከያ ቤት መደላደል የጀመረ ይመስላል። በአማካይ ስፍራ ላይ መሰለፍ በጀመረበት ቡድን ውስጥ ከጉዳት መልስ ልዩነት ፈጣሪ እየሆነ መጥቷል። በ21ኛው ሳምንት ካሳየው ምርጥ በቃት በኋላ በዚህ ሳምንት ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲረታ ከኳስ ውጪ የሚፈለግበትን ታታሪነት በትጋት ከመተግበሩ ባሻገር ጦሩን አሸናፊ ያደረገች ወሳኝ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ቢኒያም በላይ – መከላከያ
በዚህ ሳምንት ከታዩ ግለሰባዊ ብቃቶች የቢኒያም በላይ በረጅም ርቀት ግንባር ቀደሙ ነበር። መከላከያ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ባስመዘገበበት ጨዋታ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ዋና ቀማሪ የነበረው ቢኒያም በመከላከሉም ረገድ ትልቅ እገዛ እያደረገ የነበረ ሲሆን ሁለቱንም የቡድኑን ጎሎች አመቻችቶ ማቀበል ሲችል በተለይ ለእስራኤል እሸቱ ጎል ያቀበለበት መንገድ ልዩ ነበር።
አጥቂዎች
በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ
በሊጉ በርካታ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በመቃበል እየመራ የሚገኘው የአፄዎቹ የመስመር ተጫዋች በዚህ ሳምንት ፋሲል ሲዳማን ያሸነፋበት ወሳኝ ግብ መነሻ መሆን ችሏል። ተጫዋቹ ከዚህ ውጪ በነበረበት መስመር የፋሲልን የማጥቃት ሂደት ከመምራት ባለፈ በቡድኑ የመከላከል ሽግግር ወቅት የነበረው ተሳትፎ መልካም ሆኖ ታይቷል።
እዮብ ዓለማየሁ – ጅማ አባ ጅፋር
አምስተኛ የሊግ ጎሉን በማስቆጠር የጅማ ከፍተኛ ግብ አግቢነትን መምራት የጀመረው እዮብ ያስመዘገባት ጎል ጅማ ጨዋታውን ያሸነፈባት መሆኗ ይበልጥ ዋጋ ያሰጠዋል። ከአጥቂነት ወደ መስመር ተመላላሽነት ተቀይሮ ዳግም ወደ ቀደመ ኃላፊነቱ የተመለሰው እዮብ ሁለት አደገኛ የግብ ዕድሎችን መፍጠርም ችሎ ነበር።
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
ያሳለፍነው ዓመት ኮከብ ግብ አግቢ ከቆይታ በኋላ ነግሶ የዋለበትን የጨዋታ ዕለት አሳልፏል። በሁሉም የኢትዮጵያ ቡና የግብ አጋጣሚዎች ላይ በማጥቃት ላይ በመሳተፍ እና ኳስ በማመቻቸት ውስጥ ተሳታፊ የነበረው አቡበከር ከጉዳቱ ጋር እየታገለ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን አስቆጥሮ ቡናን ባለድል አድርጓል።
አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር
ባሳለፍነው ሳምንት ከመከላከያው ዮርዳኖስ አባይ ጋር ለሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ብርቱ ፉክክር ያደረጉት የሱፍ ዓሊ በዚህ ሳምንት ያለተቀናቃኝ ተመርጠዋል። ጅማ አርባምንጭን 2-1 በመርታት ለሁለተኛ ተከታታይ ድል እንዲበቃ ያደረጉት አሰልጣኙ ቡድኑ በራስ ወደ መተማመኑ ተመልሶ ጥሩ ተንቀሳቅሶ ከመውጣት ባለፈ ውጤት የማስመዝገቢያ ፎርሙላውን እንዲያገኝ አስችለውታል።
ተጠባባቂዎች
ቻርለስ ሉኩዋጎ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አንተነህ ጉግሳ – ወላይታ ድቻ
አሌክስ ተሰማ – መከላከያ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – አዲስ አበባ ከተማ
በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ
አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከተማ
ፍቃዱ መኮንን – አርባምንጭ ከተማ
ፍቃዱ ዓለሙ – ፋሲል ከነማ