የ2014 የአንደኛ ሊግ የማጠቃልያ ውድድር ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አዲስ ከተማ፣ ሮቤ ፣ ዱራሜ እና ጂንካ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸውን ተረጋግጧል።
ጠዋት በማለዳ በጀመረው የአዲስ ከተማ እና የመከላከያ ቢ ጨዋታ አዲስ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ተረጋግቶ ከመጫወት ይልቅ የጉልበት አጨዋወትን በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸው ብዙም ያልጠቀማቸው መከላከያዎች በአንፃሩ ከራሳቸው ሜዳ ኳሱን በዕርጋታ ተቆጣጥረው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ አደጋ የሚፈጥሩት አዲስ ከተማዎች ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸው ደቂቃ ስድሰት ነበር። በሂደት ሳጥን ውስጥ የገቡት አዲስ ከተማዎች የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በነበረው ያሬድ አለማየሁ አማካኝነት ግብጠባቂውን በማለፍ ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጎል።
በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት መከላከያዎች በ30ኛው ደቂቃ በግብጠባቂው እና በተከላካዩ መካከል በተፈጠረ አለመናበብ የተገኘውን ነፃ የጎል አጋጣሚ እንዳልካቸው ጥበቡ ሳይጠቀምበት የቀረው ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለ አጋጣሚ ነው። በ34ኛው ደቂቃ ጨናውን ተቋቁመው በተለመደ መንገድ ተረገግተው ኳሱን ይዘው የሄዱት አዲስ ከተማዎች አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ ነፃ አቋቃም ለሚገኘው ያሬድ አለማየሁ ተቀብሎ ቦታ አይቶ በመምታት ወደ ጎል ነት በመቀየር ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።
ወደ ዕረፍት መዳረሻ 45ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ የተላከውን የአዲስ ከተማ ግብጠባቂ ኳሱ ከያዘ በኋላ ተፍቶት መቆጣጠር ባለመቻሉ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል መከላከያዎችን ተነቃቅተው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አድርጓቸዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው የተለየ መልክ ኖሮት በፉክክር ይቀጥላል ቢባልም መጀመርያው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ ተደግሟል። መከላከያዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ቢሄድም ስኬታማ አልነበሩም። አዲስ ከተማዎች ኳሱን ይዘው ወደ ማጥቃት ያቢያመሩም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የመጨረሻው ደቂቃ መጠበቅ አስፈልጓል። መከላከያዎች በሙሉ አቅማቸው ነቅለው ለማጥቃት በሄዱበት አጋጣሚ በ84ኛው ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቢንያም ፀጋዬ የጨዋታው ማሳረጊያ ቡድኑ ከጫና ያወጣ ወሳኝ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዲስ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ አዲስ ከተማ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ አድጓል።
በማስከተል አራት ሰዓት የቀጠለው የቦዲቲ ከተማ እና የሮቤ ከተማ ጨዋታ በሮቤ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል። እምብዛም ሳቢ ያልነበረው እና ጥንቃቄን መሰረት ባደረገው በዚህ ጨዋታ በርከት ያሉ የጎል ዕድሎች አልተፈጠሩበትም ።
በሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ የኳስ ቅብብሎች ወደ ፊት በመሄድ በ59ኛው ደቂቃ የሮቤው አጥቂ ሀሰን ሁሴን ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል። ቦዲቲ ውጤቱን ለመቀየር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ግሩም ግዛው በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ቡድኑ ላይ ተፅኖ ሲፈጥር ሮቤዎች ውጤቱ አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት መከላከል ስኬታማ አድርጓቸው ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። ለሮቤ ከተማ ድል ልምዱን፣ አቅሙን በመጠቀም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ እና ከደደቢት ጋር በ2005 የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን የነበረው እንዲሁም የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ አንድ ጊዜ የተሸለመው ሲሳይ ባንጫ ትልቅ አስተዋፆኦ ነበረው። በውጤቱም ሮቤ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል።
10:00 በቀጠለው የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ዱራሜ ከተማን ከንፋስ ስልክ ላፍቶ አገናኝቶ በዱራሜ አሸናፊነት ተጠናቋል። በዱራቤ የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ በ24ኛው ደቂቃ የመጀመርያው ጎል ሊስተናገድ ችሏል። ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን አጥቂውኳሱን ለመቆጣጠር በሚያስብብት ወቅት የንፋስ ስልኩ አማካይ ኢዮብ ገ/አናንያ ተደርቦ በራሱ ላይ የመጀመርያውን ጎል ለቦዲቲዎች አስቆጥሯል።
ከዕረፍት መልስ ጅማሬ ከጎሉ ፊት ለፊት ከርቀት የየተሰጠውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት አለኝታ ማርቆስ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስገኝቷል። የጨዋታው መጨረሻ ደቂቃ የተነቃቁት ንፋስ ስልኮች በ83 ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ወንድማገኝ አለማየሁ ኳሱ አየር ላይ እያለ በቮላ መቶ ለቡድኑ የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ ምላሽ የሰጡት ቦዲቲዎች ሁለተኛውን ጎል ባገኙበት መንገድ ከቅጣት ምት አለኝታ ማርቆስ በ86ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ከጫና ማሳረፍ ችሏል። ንፋስ ስልኮች ወደ ጨዋታው የማትመልስ ጎል 88ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቱ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በረከት ከማ ሁለተኛ ጎል ለቡድኑ አስቆጥሮ ጨዋታው በዱራሜ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ከክልል ሻምፒዮን በመጣበት ዓመት ዱራሜ ከተማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል።
በኢትዮጵያ ታችኛው ሊግ ባልተለመደ ሁኔታ ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት በተካሄደው ድሬዳዋ ፖሊስ እና ጂንካ ከተማ ጨዋታ ጂንካዎች ባስቆጠሩት አንድ ጎል ማሸነፍ ችለዋል።
በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ጎል ለማስቆጠር ቢጥሩም ከሙከራ ውጭ ወደ ጎልነት የሚቀየሩ አጋጣሚዎችን እምብዛም አልተመለከትንም። ከዕረፍት መልስ በተሻለ ጥሩ ፉክክር ሲያስመለክተን ጂንካዎች በ48ኛው ደቂቃ ጎል አግኝተዋል። ለቀኝ መስመር ያጋደለ ከርቀት የተገኘውን ኳስ ለቡድን አጋሮቹ ለማሻመት የሚመስለው ኳስ በቀጥታ በዮሴፍ ድሪባ አስቆጥሮታል። ጂንካዎች ውጤቱን አስጠብቀው ጠንክረው በመከላከል በሚገኙ አጋጣሚዎች አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል።
ድሬደዋ ፖሊሶች ጎል ፍለጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይ መሐመድ አሊ ያነከነው የሚያስቆጭ ነበር። በዚህ ሂደት ጨዋታው ቀጥሎ በመጨረሻም በጂንካ አሸናፊነት ተጠናቋል። ፍፁም ቅጣት ምት ተከለከልን በማለትተ በጨዋታው መሐል የዕለቱን ዳኛ ሲቃወሙ የቆዮት የድሬዳዋ ፖሊስ ተጫዋቾችን ከጨዋታም መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ደጋፊዎች በዕለቱ ዳኛ ላይ ያልተገባ ተግባር ሲፈፅሙ አስተውለናል። ውጤቱን ተከትሎ ጂንካ ከተማ ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊግ መመለስ ችሏል። ቡድኑ በ2009 ከከፍተኛ ሊግ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል።
የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ረቡዕ ግንቦት 17 ቀን ሲቀጥል
02:00 | አዲስ ከተማ ከ ዱራሜ ከተማ
04:00 | ሮቤ ከተማ ከ ጂንካ ከተማ
ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚገቡ ቀሪ ሁለት ቡድኖች የሚለዩበት ጨዋታዎች
10:00 | መከላከያቢ ንፋስ ስልክ
12:00 | ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ቦዲቲ ከተማ