ሦስተኛው የትኩረታችን ክፍል ደግሞ አሰልጣኞች ላይ ያተኮረ ነው።
👉 የደረጀ መንግሥቱ አስተዋፅዖ
ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ወሳኝ ድል ማሳካት ችለዋል። በጨዋታው የቀድሞው የቡድኑ አምበል ቡድኑን በሜዳ ጠርዝ ሆኖ ሲመራ ተመልክተነዋል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድኑን ክረምት ላይ ከተረከቡ ወዲህ ባለፉት ዓመታት የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ አምበል በመሆን ሲያገለግል የነበረው እና በቅርቡ ጫማውን የሰቀለውን ደረጀ መንግሥቱን በቡድኑ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ውስጥ እንዲካተት ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ታድያ በተለይም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የጉልበት ጉዳት ካስተናገዱ ወዲህ በሜዳው ጠርዝ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቆመው ቡድናቸውን መምራት አለመቻላቸውን ተከትሎ በተለይ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ለአፍሪካ ዋንጫ ወደ ካሜሩን ማምራቱን ተከትሎ በጊዜያዊነት ሲመራ የነበረው አብርሃም መላኩ በሜዳው ጠርዝ ቡድኑን በተደጋጋሚ ሲመራ አስተውለናል። በድሬዳዋው ጨዋታ የአብርሃም መላኩ በዕረፍት ምክንያት አለመኖሩን ተከትሎ በጨዋታው ከመጋረጃ ጀርባ እንጂ በፊት ለፊት በጨዋታዎች ወቅት ብዙ ተሳትፎ ሲያደርግ የማናስተውለው ደረጀ መንግሥቱ በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ቡድኑን ከሜዳው ጠርዝ ሆኖ ሲመራ አስተውለናል።
በጨዋታው ከፍ ባለ ስሜት እና ንቃት የቀድሞ የቡድን አጋሮቹን ሲያበረታታ የነበረው ደረጀ በውሃ ዕረፍት ወቅትም እንዲሁ ለቡድን አባላት መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ አስተውለናል። ታድያ ለባህር ዳር ከተማ ትልቅ ተስፋ በፈነጠቀው በዚህ ጨዋታ ለተመዘገበው ውጤት ማማር የደረጀ መንግሦቱ ሚና የላቀ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።
ገና ወደ ሥልጠናው ለመግባት እየተንደረደረ የሚገኘው የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና ሐረር ቢራ አማካይ ለቀጣይ የሥልጠና ህይወቱ ስንቅ የሚሆነውን አይረሴ ቀትር በደጋፊዎቹ ፊት አሳልፏል።
👉 አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ያልነበሩት አሰልጣኝ
በጨዋታ ሳምንቱ በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ ታጅቦ ከተጠናቀቀው የድሬዳዋ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከዚህ ቀደም እንዲህ እንደ አሁኑ በተቀናጀ መልኩ የድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ሳይለመዱ በፊት በነበረው የእግር ኳሳችን ልምምድ ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በተለይ የተሸናፊ ቡድን አሰልጣኞች የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በመሸሽ በፍጥነት ከአካባቢው የመሰወር ፣ አንዳንዴም የመደበቅ ነገሮች የነበሩ ቢሆንም ከሱፐር ስፖርት መምጣት በኋላ በዚህ ረገድ አስገራሚ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ አስተያየታቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርዋል። ምንም እንኳን በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረችው እና በዳኛው ሳትፀድቅ የቀረችው ግብ በብዙ መልኩ የምታስቆጭ የነበረች ቢሆንም አሰልጣኙ ሀሳባቸውን ለመከታተል ይጠባበቅ የነበረውን የእግር ኳስ ቤተሰብ ክብር ሰጥተው ሀሳባቸውን ቢያጋሩ የተሻለ ይሆን ነበር።
👉 “ሀያ አምስቱም ተጫዋቾቼ ከዋክብቶቼ ናቸው”
አዲስ አበባ ከተማ ሰበታ ከተማን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በቀጣዩ ጨዋታ በአምስት ቢጫ ስለማይሰለፈው የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ ስለሆነው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ሲጠየቁ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
“እኔ በእዚህ አይነት ነገር ከዚህ በፊትም ብያለሁ፡፡ እኔ ኮከቦች የሉኝም ሀያ አምስቱም ተጫዋቾቼ ከዋክብቴ ናቸው፡፡ በቀጣይ ጨዋታ ደግሞ ሌላ ሰው በዕርግጠኝነት ታያላችው። እንደዚህ አይነት ዕምነት አሰልጣኞች ካለንማ ቡድናችን ይበላሻል፡፡ ይህ ዓይነት ነገር ብዙ የሚያስጨንቀኝ ነገር የለም፡፡ ሁሌም የሰራ ፣ በአካል ብቃት ዝግጁ የሆነ ይጫወታል ስለዚህ ብዙ አያሳስበኝም፡፡”
ይህም እንደ አዲስ አበባ ከተማ ባለ በንፅፅር ተቀራራቢ የጥራት ደረጃ ባላቸው ተጫዋቾች ለተገነባ ቡድን አጠቃላይ የቡድኑን ስሜት በማነሳሳትም ሆነ ሁሉም ግለሰቦች ዋጋ እንዳላቸው እንዲያስቡ በማድረግ ለማነሳሳት ይረዳል ተብሎ ይታመናል።
ገና ከቅጥራቸው አንስቶ በሥነ ልቦና ረገድ ቡድኑን በማነሳሳት ውጤት ለማምጣት እንደሚጥሩ ሲናገሩ የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ተጫዋቾቻቸው ላይ ከላይ የተመለከትነው ዓይነት ሀሳቦችን በማስረፅ ቡድኑን ለማቃናት እያደረጉ የሚገኙት ጥረት በተወሰነ መልኩ ውጤት እያስገኘላቸው ይገኛል።