በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ የፋሲል ከነማ ሥራ-አስኪያጅ አቶ አቢዮት ከሶከር ኢትዮጰያ ጋር ቆይታ አድርገዋል

👉”በድሬዳዋ ከተማ መሸነፋችን እኛም ያልፈለግነው ነው እንጂ ታስቦበት የተደረገ ነገር እንዳልሆነ በንፁህ ልብ እና በሀቅ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለሚደግፍ የስፖርት ቤተሰብ መግለፅ እንፈልጋለን”

👉”…ይሄንን የሚያደርጉ ሰዎች አርፈው እንዲቀመጡና ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ለማሳሰብ እወዳለው”

👉”…እንደዚህ አይነት ነገር ቢኖረን ወዲያው ቅዱስ ጊዮርጊስን እንኳን ደስ አላችሁ ላንል እንችላለን”

👉”…ስታዲየም ውስጥም ሆነ በኋላ በማኅበራዊ ገፆች ያንፀባረቁት ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ ይሄ ግን ደጋፊ ማኅበሩንም ስፖርት ክለቡንም አይወክልም”

👉”የእኛ ሊግ በአስር ደቂቃዎች ሦስት ጎል አይገባበትም የምትልበት ሊግ አይደለም”

የዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ከፍተኛ ፉክክር ተደርጎበት ሻምፒዮናው እና ወራጆቹ ክለቦች ባለቀ ሰዓት መለየታቸው ይታወቃል። ሊጉ ትናንት ቢገባደድም የብዙዎችን ቀልብ የያዙት መርሐ-ግብሮች ከትናንት በስትያ ተደርገዋል። በተመሳሳይ ሰዓት ከተደረጉት ሦስት ጨዋታዎች መካከል በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ (ፔዳ) ስታዲየም የተከናወነው የድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በብርትካናማዎቹ 3-2 አሸናፊነት ከተገባደደ በኋላ “ከጨዋታ ውጤት ማጭበርበር ” ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱ ይገኛሉ።

የጨዋታ ተፋላሚዎቹ ድሬዳዋ እና ፋሲል ቢሆኑም “በጨዋታው የተፈጠረው ነገር አግባብ ያለው አይደለም” ያለው አዲስ አበባ ከተማም ከሊጉ መውረዱ ከተረጋገጠ በኋላ ለአክሲዮን ማኅበሩ ጨዋታው እንዲመረመር ክስ አቅርቧል። የሀገር ውስጥ እግርኳስ ላይ ትኩረቷን አድርጋ የምትሰራው ሶከር ኢትዮጵያም ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ እንዲሁም የሊጉን የበላይ አካል አክሲዮን ማኀበር እና የሀገሪቱን እግርኳስ የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አናግራ በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብ ለመቀበል ሞልራለች። እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ከድሬዳዋ ከተማ በቀር ሌሎቹ አካላት ፍቃደኛ ሆነው በራሳቸው በኩል ያለውን ጉዳይ አብራርተዋል። በዚህም መሰረት የሰጡትን ሀሳብ በየተራ የምናቀርብ ሲሆን በቅድሚያም በፋሲል ከነማ በኩል የክለቡን ሥራ-አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ አግኝተን ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከትለው አቅርበነዋል።

የትናንት በስቲያው ሽንፈት መነጋገሪያ ሆኗል። ‘በአዲስ አበባ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ተፈጥሯል’ ለተባለው ነገር ግብረ መልስ ነው የሚል ሰፊ ሀሜት አስነስቷል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እናንተ ምልከታችሁ ምንድነው ?

“የእኛ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ውጤት ከአዲስ አበባ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ውጤት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ግን የአዲስ አበባ እና ጊዮርጊስ ጨዋታ በራሱ ግን ችግር አለበት። ጨዋታው ላይ ብቻ ሳይሆን ከጨዋታው በፊት በነበሩት ብዙ ነገሮች ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን እኛ ጋር የተመዘገበው ውጤት የአዲስ አበባን ውጤት በመስማት የተፈጠረ ነገር አይደለም። ቡድናችን ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የገባው። ተጫዋቾቻችንም እስከ መጨረሻው ለማሸነፍ ተጫውተዋል። በማኅበራዊ ሚዲያዎች ግን ሆን ተብሎ የስፖርት ክለቡን ጥላሸት ለመቀባት ፣ የስፖርት ክለቡ ስኬት ያላስደሰታቸው ሰዎች ወይም ሜዳ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ እና ማሸነፍ ማስቆም ያልቻሉ ሰዎች የሚያራግቡት ወሬ ስለሆነ ወሬው ትክክል አይደለም ፤ ስፖርት ክለቡን የሚመጥንም አይደለም። ፋሲል ከነማ ከዚህ በፊት የሚታወቀው እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ውስጥም ሆነ አሁን የሊግ ካምፓኒው ከተመሰረተ በኋላ ያሉ ኢ-ፍትሀዊ አሰራሮችን በመታገል ነው። ይሄንን ፊት ለፊት ነው የምንታገለው። ስለዚህ ይሄ ነገር ትክክል አይደለም።

“ከሷል የሚባለው ክለብ ልክ ነው ከሷል። የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ለክሱ የሚመልሰውን ምላሽ ሰምተን በህጋዊ መንገድ መልስ እንሰጣለን ብለን ነው የምንጠብቀው ፤ እንጂ ማንም ሰው በተናገረ ቁጥር ወጥተህ የምታስተባብል ከሆነ የትልቅ ክለብ ምልክት አይደለም። ነገር ግን በተደራጀ መንገድ እኛ መግለጫ እንሰጣለን ፤ እየተዘጋጀንበትም ነው። ህጋዊ የሚሆነውም ክሱን ላቀረበው ቡድን አወዳዳሪው አካል አንድ ቡድን ከአቅም በታች ተጫውቷል ወይስ አልተጫወተም ብሎ የሚለካበት መለኪያዎች ስላሉት የሚመለከተው አካል መልስ ይሰጣል። ከዛ በኋላ እኛ መልስ እንሰጣለን ብለን ነው የምናስበው። በአጠቃላይ የእኛ ጨዋታ ውጤት ከአዲስ አበባ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።”

የአዲስ አበባ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ችግሮች ነበሩበት ብለኸኛል። ምን ዓይነት ችግሮች ነው የነበሩበት…?

“እነዛን ችግሮች እኛ አላነሳናቸውም ፤ ችግሮች አሉ። ያላነሳነው ከእኛ ውጤት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር ቢኖርም እኛ እና ድሬዳዋ ስንጫወት ተፅዕኖ ስላልፈጠሩ ነው። ነገር ግን ለአዲስ አበባ መውረድ ወይም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን መሆን አስተዋፅኦ አድርገዋል። ነገር ግን ከዚህኛው ጨዋታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ለአዲስ አበባ መውረድ ግን ቀድሞ የነበሩ ነገሮች በራሱ ላይ ችግር ፈጥረዋል።”

በማኅበራዊ ሚዲያ እና በስታዲየሙ ውስጥ የታየው የደጋፊው ሁኔታ ለሀሜቱ አንዱ መነሻ ሆኗል ። ይህ ጉዳይ የክለቡ አቋም ተደርጎ ይወሰዳል ?

“ደጋፊዎቹ እንደ አንድ የስፖርት ቤተሰብ የራሳቸው ስሜት ይኖራቸዋል። ደጋፊዎቻችን ፋሲል ሻምፒዮን እንዲሆን ይፈልጋሉ ፤ ሻምፒዮን ባይሆንም እስከ መጨረሻው ድረስ ትግል አድርጎ ሁለተኛ ቢወጣም ይቀበላሉ። ነገር ግን እዛኛው ሜዳ ላይ የተደረገው ነገር ትክክል አይደለም የሚል እሳቤ ስለነበራቸው እና ቀድመው የሰሟቸው ነገሮች ስላሉ እንዲሁም እዛኛው ሜዳ የእኛም ደጋፊዎች ገብተው እየተከታተሉ በስልክ ይደዋወሉ ስለነበር እነሱን ስሜት ውስጥ የከተታቸው ነገር ሊኖር ይችላል። በዚህ ምክንያት ስታዲየም ውስጥም ሆነ በኋላ በማኅበራዊ ገፆች ያንፀባረቁት ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ ይሄ ግን ደጋፊ ማኅበሩንም ስፖርት ክለቡንም አይወክልም። በዚህ ውስጥ ግን የግል ስሜታቸውን ማንፀባረቅ ይችላሉ ፤ መብታቸውም ነው። ምናልባት በዚህ መንገድ የተንፀባረቀ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለው እንጂ ደጋፊ ማኅበሩንም ሆነ ስፖርት ክለቡን የሚወክል ነገር በሜዳ ላይም በማኅበራዊ ሚዲያም አልተራገበም። ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ነገር ቢኖረን ወዲያው ቅዱስ ጊዮርጊስን እንኳን ደስ አላችሁ ላንል እንችላለን። ስለዚህ ደጋፊዎች ከግል ስሜታቸው ተነስተው በመሰላቸው እና በተረዱበት መንገድ የገለፁት ስሜት ነው።”

ሁለት ዓመት በተከታታይ ረጅም የድል ጉዞ ያደረገው ፋሲል ከነማ በመጨረሻ በተመሳሳይ ተጋጣሚ ወቅታዊ አቋሙን በማይገልፅ መልኩ መሸነፉ እና በተመሳሳይ ነገሮች ስሙ መነሳቱ በተለይም ደግሞ ክለቡ በይፋ ማስተባበያ አለመስጠቱ ይበልጥ ጣቶች እንዲቀሰሩበት አያደርግም ?

“ማስተባበል የሚባለው ስትጠየቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ነገር ስለተራገበ እየወጣህ መልስ መስጠት አለብህ ብዬ አላስብም። በተደራጀ መንገድ ነው ምላሽ የምትሰጠው። በእግር ኳስ ብዙ ጨዋታዎችን ብታሸንፍ የሆነ ቦታ ላይ መሸነፍህ አይቀርም። የሆነ ቦታ ላይ ትሸነፋለህ። ስለዚህ ፋሲልም በዚህ ዓመት የተሸነፈው በድሬዳዋ ብቻ አይደለም። በዚህ ዓመት ላለመውረድ በሚጫወተው አዲስ አበባ ከተማ ተሸንፈናል። ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማም አሸንፎናል። በወልቂጤ ስንሸነፍ የተባለ ነገር የለም። ስለዚህ ያሁኑ እንደ ልዩ ተደርጎ መቅረቡ ትክክል አይደለም። ዘንድሮ በሊጋችን ያየናቸው ውጤቶች አሉ። ቡና በወልቂጤ 3-1 እየተመራ 4-3 ያሸነፈበት እንዲሁም የሀዲያ እና አርባምንጭ ጨዋታ 4-1 ሆኖ ባለቀ ሰዓት ጎሎች ገብተው አቻ አልቋል። የእኛ ሊግ በአስር ደቂቃ ሦስት ጎል አይገባበትም የምትልበት ሊግ አይደለም። ስለዚህ እኛ ጋር የተከሰተው የጨዋታ ማጭበርበር ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መታረም ያለበት ጨዋታው ምንም ሳይገመገም እና ከዳኛው ሪፖርት ተጠይቆ አጠቃላይ ‘ጨዋታው ተጭበርብሯል ወይስ አልተጭበረበረም ?’ የሚያስብል መለኪያዎች አሉ ፤ ይሄ በሌለበት አወዳዳሪው አካል በተለይ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የሰጡትን መግለጫ እያየው ነበር። እንደውም ለእርሱ ነበር ምላሽ መጠየቅ የነበረብን። ይሄ ትክክል ያልሆነ የግለሰብ ስሜት እና ለክለቡ ካለውን የግል የተሳሳተ ምልከታ ተነስቶ የሰጠው መግለጫ ስለሆነ ይሄንን እኛ መታረም ባለበት መንገድ እንዲታረም መግለጫ እንሰጣለን። ነገር ግን በድሬዳዋ ከተማ መሸነፋችን እኛም ያልፈለግነው ነው እንጂ ታስቦበት የተደረገ ነገር እንዳልሆነ በንፁህ ልብ እና በሀቅ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለሚደግፍ የስፖርት ቤተሰብ መግለፅ እንፈልጋለን።”

በመጨረሻ…

“ፋሲል ከነማ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በደል እየደረሰበት እየታገለ በአጠቃላይ በሊጉ ፍትሀዊ አሰራር እንዲኖር ሲታገል የነበረ ክለብ ነው። አሁንም ቢሆን ከዚህ የተለየ አቋም የለንም። እኛ ተበድለን እዚህ የደረስን ክለብ ነንና ያንን ጉዳይ እኛም መፈፀም አንፈልግም ፤ የዚህም አይነት እኩይ ተግባር ተባባሪ መሆን አንፈልግም። ትናንትም አልነበርንም፣ ዛሬም ማድረግ አንፈልግም ወደፊትም ማድረግ አንፈልግም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሰው እየተነሳ በማኅበራዊ እና ዋናው ሚዲያ የክለቡን ስም በሚያጠለሽ መንገድ አስተያየት መስጠትና ክለቡ የወከለውን ማኅበረሰብ እና የመጣበትን አካባቢ መተቸት ከሞራልም ሆነ ከህግ አኳያ ትክክል ስላልሆነ ይሄንን የሚያደርጉ ሰዎች አርፈው እንዲቀመጡና ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ለማሳሰብ እወዳለሁ።”