👉 “ይህን ድርጊት የፈፀሙና የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘኑ ክለቦች ላይ በሚቀርበው ሪፖርት ልክ እርምጃ እንወስዳለን ብለን እናስባለን”
👉 “የተፈጠው ክስተት በእውነቱ የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘነ ነው ፤ እኛም እንደ አወዳዳሪ አካል ያዘንበት ነው”
👉 “የጥቂት ክለብ ደጋፊዎች የእግርኳስ ድጋፍ ምን ማለት እንደሆነ እየገባቸው ያለ አይመስለኝም”
👉 “በአንዳንድ ተፅዕኖዎች ለተወሰነ ክለቦች አድቫንቴጅ መስጠትን የሚያሳዩ ነገሮች ተከስተዋል”
👉 “ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እስካልሰረፀ ድረስ አሁን የተከናወነውን ነገር በቅጣትና በማስተማር የሚመለስ መስሎ አይታየንም”
የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በከፍተኛ ደረጃ የተጠበቁ ነበሩ። ከጨዋታዎቹ መካከል ከትናንት በስቲያ በተመሳሳይ ሰዓት የተደረጉት ሦስት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን የሊጉ አሸናፊ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማን ደግሞ ሦስተኛው ወራጅ ቡድን በማድረግ ተጠናቀዋል። ሆኖም በጨዋታዎቹ የተመዘገቡት ውጤቶችን ተከትሎ የእግርኳሱ ከባቢ ከአቅም በታች ከመጫወት ጋር በተያያዘ ከሁሉም አቅጣጫዎች የሚስነዘሩ የሴራ ንድፈ ሀሳቦች ሲመላለሱበት ቆይቷል። ቀደም ብለን ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸው ከተነሱ ክለቦች መካከል በፋሲል ከነማ በኩል ያለውን ሀሳብ ያስነበብን ሲሆን አሁን ደግሞ የሊጉን የበላይ አካል ማብራሪያ ጠይቀን ሀሳባቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆኑት የሊጉ አክስዮን ማህበር የውድድር እና ሥነ ስርዓት ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።
የውድድር ዓመቱ ግምገማችሁ ምን ይመስላል ? ከአስተዳደር አኳያ ? ስኬት እና ፈተናዎቹ ?
“በመጀመርያ ሶከሮች ለጥያቄ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ። የዘንድሮ የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ክንውን በተመለከተ ምንም እንኳን አጠቃላይ ሪፖርቶችን በቀጣይ ቀናት ውስጥ የምናቀርብ ቢሆንም ቀሪ ሥራዎች ለምሳሌ ሽልማቶችን መሸለም እና ሌሎች ስራዎች ቢቀሩብንም በወፍ በረር የአጠቃላይ የዓመቱን ሪፖርት ዕይታ ለመግለፅ እሞክራለው። የ2014 የውድድር ዓመት ዓምና ከተደረገው የ2013 የውድድር ዓመት በብዙ መልኩ የተሻለና ነገር ቢኖረውም አልፎ አለፎ የሚታዩ እንደ ክፍተት ያየናቸውም ጉዳዮች ቢኖሩም በአንፃራዊነት የ2014 የውድድር ዓመት አፈፃፀም ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው የሚል ምልከታ ነው ያለን፡፡”
በመጨረሻው ቀን በሦስቱ ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የተከሰቱ አነጋጋሪ ጉዳዮችን በምን መልኩ አያችኋቸው ?
“እንግዲህ ቅድም እንደገለፅኩት የ2014 በሁሉም እግርኳስ ቤተሰብ ውስጥ እንደ ትዝታም ምናልባትም በቀጣይ የማናያቸው ዓይነት ክስተቶች ተከስተዋል። ወራጅና ሻምፒዮኑን በተመሳሳይ ሰዓት ጨዋታዎች የሚወሰኑበት ማድረግ እግርኳሱን ጤናማ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ ውድድራችንን ያሳምርልናል ብለን አስበን ነበር። ሆኖም የተፈጠረው ግን አንዳንድ እግርኳሳዊ ያልሆኑ ነገሮች ተከስተዋል። የቡድኖች መላቀቅ በተመለከተ ያው በማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደምናየው አንዳንድ ክለቦች ያቀረቡት ቅሬታ አለ። (እኛ ጋር ተጠናቆ የመጣ ቅሬታ ሪፖርት እስካሁን ስላልገባ)። ያም ቢሆን ክለቦች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሜዳ አለመግባት ጨምሮ ሜዳም ከገቡ በኋላ በአንዳንድ ተፅዕኖዎች ለተወሰነ ክለቦች አድቫንቴጅ መስጠትን የሚያሳዩ ነገሮች ተከስተዋል። ይህ እንደ አወዳዳሪ አካል ከአቅም በታች መጫወት ማለት በብዙ መንገድ ይታያል። ለምሳሌ ከአቅም በታች መጫወት ምን አልባትም ሙሉ አቅምን ይዞ ሜዳ ላይ ገብቶ ተጫዋቹ በሚፈለገው መልኩ አለመንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል። በሌላኛው ደግሞ ጥሩ አቅም ያላቸው ተጫዎቾችን እያሉ እነርሱን ይዞም አለመግባትም ራሱን የቻለ ተፅእኖ አለው። ሦስቱንም ሜዳ ላይ የተከናወኑ ጨዋታዎች ተዟዙረን ነው መመልከት የቻልነው። እንዳየነው ከሆነ ውጤት ለማስጠበቅ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ሁሉ ሦስቱም ጨዋታዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። እነዚህ ቅሬታዎች እንደ አወዳዳሪ አካል እና እንደ ደጋሽ አፈጻፀማችን በአማረ እና በተሻለ ሁሉንም የእግርኳስ ቤተሰብ ባስደሰተ መልኩ እንዲሆን ነው ጥረታችን ነገር ግን ይሄ ፕሮፌሽናል ካለመሆን የሚመጣ ነው የሚል እምነት ነው ያለን። ፕሮፌሽናል መሆን የሚጀምረው ከግል ከአንድ ተጫዋች ይጀምራል ቀጥሎም ከቡድን ቀጥሎም ቡድን የሚመሩት አካላት የሚጀምር ነው። ይሄ ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እስካልሰረፀ ድረስ አሁን የተከናወነውን ነገር በቅጣትና በማስተማር የሚመለስ መስሎ አይታየንም። ምክንያቱም ይህን በተመሳሳይ ሰዓት ስናደርግ ፕሮፌሽናል ነን የሚል እምነት ነበረን። ነገር ግን ያንን የሚከውኑ ተዋንያኖቹ ፕሮፌሽናል እስካልሆኑ ድረስ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶችን የማናስተናግድበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለእኛ እንደ አወዳዳሪ አካል በቀጣይ ትምህርት የወሰድንበት ነው። በተመሳሳይ ሰዓት ማጫወት ብቻውን እንደዚህ ዓይነት ኢ-ፍትሀዊ የሆኑ ድርጊቶች ይፈታሉ ብለን አናስብም። በቀጣይም ሊታሰብ የሚገቡ ጉዳዩች አሉ። ለምሳሌ ከፕሮግራም አወጣጥ ጀምሮ የመውረድና የመውጣት አካሄዶች በተመለከተ ምናልባትም እንደ መፍትሄ በወፍ በረር ያየነው እና መሆን ያለበት ሦስት ቡድኖች የሚወርዱበትን ሁኔታ ቀንሶ ደቡብ አፍሪካ እንደ የሚያደርጉት የፕሌይ ኦፍ ሁኔታ አለ ፤ ይህ ምንን ይከላከልልናል። ምንም እንኳ ሦስቱ ቢታወቁም ያንን ዕድል ስላለ ከመውረድና ከመውጣት ጋር እንደዚህ ዓይነት ቅድመ አፈፃፀም ላይ የሚያመጡት ክፍተቶች ይቀንሳል የሚል እምነት አለ። ሌሎችንም አማራጮችን የመጠቀም እና አሁን እየተሻሻለ የመጣው ኳሳችን ወደ ኋላ እንዳይመልሱብን ስጋቶች ስላሉ በዚህ ለመለወጥ እናስብበታለን። የተፈጠው ክስተት በእውነቱ የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘነው እኛም እንደ አወዳዳሪ አካል ያዘንበት ነው። ምክንያቱም በተመሳሳይ ሰዓት ስናደርግ እነዚህንና የመሳሰሉትን ነገሮችን ያስወግድልናል ብለን አስበን ነበር። ሆኖም እንዲህ ያለ ነገር መከሰቱ እኔም እንደ አወዳዳሪ አካልም የተሰማኝ ስሜት አለ በዛ ልክ ነው የምናየው።”
መሰል ሀሜቶችን ለማስቀረት ከጨዋታው በፊት በተመሳሳይ ሰዓት ከማድረግ ባለፈ ሌሎች የወሰዳችኋቸው እርምጃዎች አሉ ?
“እኛ ያደረግነው የመጀመሪያው መፍትሔ በተመሳሳይ ስዓት የሚደረጉ ጨዋታዎችን ከማድረግ ባሻገር ኮሚኒኬሽኖችን ግንኙነቶችን በተፈለገው ልክ እንዳይሆን ክለቦች እና ወደ ሜዳና ወደ ቴክኒክ ኤርያ የሚመጡ አሰልጣኞችን ፣ ተጫዋቾችን ምንም ዓይነት የመገናኛ መንገድ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ተሞክሯል። ነገር ግን ተጫዋቹ ፣ በቡድኑ አካባቢ ያሉትን ብንከለክልም። ከላይ ሆነው ክለቡን በትልልቅ ደረጃ የሚመሩ ሰዎች ፕሮፌሽናል ናቸው ብለን ስላሰብን ስታዲየም ሲገቡ የሞባይል ስልኮቻቸውን አልተቀበልንም። ምክንያቱም ትላልቅ አመራሮች፣ ፍጹም ፕሮፌሽናል ናቸው ብለን ስላሰብን። በአጠቃላይ ግን ሌሎች የመፍትሔ ሀሳቦችን ለመተግበር ስንሰራ ቆይተናል።
በጉዳዩ ዙርያ ምርመራስ እያደረጋችሁ ነው ? ከምርመራው በኋላ የሚመጣ ውጤት ካለስ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኝነታችሁ እስከምን ድረስ ነው ?
“እንግዲህ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ የትኞቹ ናቸው የሚለውን መለየት ይፈልጋል። ቅሬታዎች እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን እኛ ሁሌም ውሳኔያችን የሚመሰረተው የሚቀርቡ የዕለቱ ሪፖርቶች ላይ ነው። ከዳኞች ፣ ከኮሚሽነሮች የሚቀርቡ ሪፖርቶች አሉ ፤ እነዛ ሪፖርቶች ከደንቡ አንፃር ምን ይላል የሚለውን እናያለን። ከደንቡ አንፃር የሚሄድና በትክክልም የቀረቡት ሪፖርቶች መፈፀሙን የሚያረጋግጡልን ከሆነ ህጉ የሚፈቅደውን ውሳኔ እናደርጋለን። ነገር ግን የቀርቡት ክሶች ራሳቸው ፎርማል በትክክል ወይም በአግባቡ ቀርበዋሉ የሚለው አንድ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ በመወራቱ ምናልባት ክስ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ክስም ቀረበ አልቀረበ በሚቀርቡልን የዳኞችና የኮሚሽነሮች ሪፖርት ተመስርተን ሕጉ የሚለውን መተግበር ነው። ይህ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። ይህንን ድርጊት ለፈፀሙና የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘኑ ክለቦች አስፈላጊውን በማስጠንቀቂያም ሊሆን ይችላል ፤ አስፈላጊውን እርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ ይኖራል። የማስተማሪያ እና በቀጣይ ይህ ድርጊት እንዳይደገም እንሰራለን። ሜዳ ውስጥ በገቡ ተጫዋቾችም ላይ ውሳኔ ይኖራል። አንዳንድ ነገሮችን ስንሰማ የስታዲየሙ ሴታፕ ራሱ ለዛ የሚጋርድ ነበር። ደጋፊው ሜዳ የሚገባበት ሁኔታ እንደምታውቁት የባህርዳር ስታዲየም የተመልካች እና የመጫወቻ ሜዳው ምንም ዓይነት አጥር አልነበረውም። በሰራዊት ነበር ስናስጠብቅ የነበረው። ሰራዊትስ በምን ያህል ሊቆጣጠረው ይችላል የሚለው ነገር ከግምት መግባት ይኖርበታል። ነገር ግን ይህንን ድርጊት የፈፀሙና የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያሳዘኑ ክለቦች ላይ በሚቀርበው ሪፖርት ልክ እርምጃ እንወስዳለን ብለን እናስባለን።”
እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በሌሎች ጉዳዮች ዕድገት እያሳየ የሚገኘውን ሊግ ወደ ኋላ ይጎትታሉ ብላችሁ አታስቡም ?
“ቅድም እንደገለፅኩት ነው። ዘጠና በመቶ ጥሩ ሆኖ አስር በመቶው ስራህን የሚያጠለሽ ከሆነ እዛ ላይ መስራት ግድ ነው። ምክንያቱ ገና ሁለተኛ ዓመት ላይ ነን ፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ብዙ ልንሞገስ እንችላለን። ግን ያ ሙገሳ ትክክል ነው የሚል ዕምነት የለኝም። ገና ብዙ መሰራት ያለበት ነገር አለ። እግርኳሱ የሚፈልገውን መንገድ ማምጣት እንፈልጋለን። እግርኳሱ የሚፈልገው ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ ነው። (ለእግርኳሱ እግርኳሳዊ አመለካከት ያስፈልጋል።) ከአመራሩ ጀምሮ እግርኳሱን የሚጫወት ተጫዋች፣ አሰልጣኝ አጠቃላይ የቡድን አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በእግርኳሱ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች በሙሉ የእግርኳስን ምንነት አውቀው ትክክለኛ አስተሳሰብ እስኪመጣ ድረስ መስራት ያስፈልጋል። የዚህ ሊግ ስኬት የሚለካው በዚህ መሆን አለበት። ውድድርን በጊዜ ጀምሮ በጊዜ መጨረስ ብቻ መለኪያ መሆን የለበትም። የውድድሩ ተዋንያን የእግርኳስን ምንነት በሚገባ እንዲረዳ አሰራሮችን በትክክል በመተግበር ረገድ ገና ብዙ የቤት ስራዎች አሉብን። በቀጣይ የውድድር ዓመት ሊጉን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ብለን ያሰብናቸው ስራዎች እንሰራለን። ለምሳሌ ከዳኝነት አንፃር ቫርን(የመልሶ ማሳያ) የመተግበር ሀሳብ አለን። በቢሮ ደረጃም እንቅስቃሴ እያደረግን ነው። ይሄ ከተሳካልን በቀጣይ ቫርን ይዘን እንመጣለን። ቫር ብቻውን ውድድሩን ፍፁም ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም። ቫርን የሚተረጉሙ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል። እንደ ሀገር ያሉን ባለሙያዎች ሁለት ናቸው። ውድድሮቻችን ሰፊ በመሆናቸው ለዚህ ብቁ የሆኑ ዳኞችን ማሰልጠን ይጠበቅብናል። በተጨማሪም አሁን በዕረፍት ጊዜ ለአሰልጣኞች፣ ለተጫዋቾች እና የቡድን አመራሮች የቫርን አጠቃቀም ማወቅ ስላለባቸው ሥልጠና ለመስጠት እናስባለን። የክለብ ደጋፊዎች በአሁኑ ባለው ልክ ትክክለኛ ቁመና ላይ ናቸው ብዬ አላስብም። በተለይ የጥቂት ክለብ ደጋፊዎች የእግርኳስ ድጋፍ ምን ማለት እንደሆነ እየገባቸው ያለ አይመስለኝም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል። በተጨማሪም የ240 ጨዋታዎችን ቴክኒካል ግምገማ አሰልጣኞችን ጠርተን የምንገመግም ይሆናል። ይህ ግመጋማ ለብሔራዊ ቡድን፣ ለራሳቸው ለክለቦችም ጭምር ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛል። በአጠቃላይ ሌሎች ተግባራትን በመከውን እግርኳሱን ትንሽ ፈቀቅ ለማድረግ ብዙ ዕቅዶችን ለመፈፀም አስበናል።”