ከቀናት በኋላ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የቻን ማጣሪያ ፍልሚያዎች የሚጠብቀው የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ረፋድ ላይ የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል።
በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፈው የቻን ውድድር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ በቀጣይ ዓመት እንደሚደረግ ይታወቃል። ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን ለመለየት ደግሞ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ የሚደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ሐምሌ 15 እና 21 ታንዛኒያ ላይ የሚያደርግ ይሆናል።
ለዚህ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከቀናት በፊት ልምምዷን የጀመረችው ደቡብ ሱዳን ከትናንት በስትያ ቀድማ ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት ሀገር ታንዛኒያ የገባች ሲሆን ዛሬ ረፋድ ደግሞ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጋለች። ዳሬሰላም ላይ በጃካያ ኪክዌቴ የወጣቶች ማዕከል በተደረገው ጨዋታ ላይ ደቡብ ሱዳን በ54ኛው ደቂቃ በአጥቂው ዮሐና ፖሊኖ አማካኝነት ግብ አስቆጥራ መሪ የነበረች ቢሆንም የኋላ ኋላ ግብ አስተናግዳ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቃለች።