በአሠልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ የሚመራው ሲዳማ ቡና የአጥቂ እና ተከላላዩን ውል ማራዘሙ ታውቋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዘው የቀጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች የቀጣዩ ዓመት ስብስባቸውን እያጠናከሩ የሚገኝ ሲሆን የነባር ተጫዋቾቻቸውንም ውል ጎን ለጎን እያደሱ ይገኛሉ። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት አጥቂው ሳላዲን ሰዒድ እና የመሐል ተከላካዩ ያኩቡ መሐመድ ውላቸውን አድሰዋል።
በሙገር ሲሚንቶ የክለብ ህይወቱን የጀመረው ሳላዲን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኋላም ከኢትዮጵያ ውጭ ዋዲ ዴግላ፣ ሊርስ (ውሰት)፣ አል አህሊ እና ኤምሲ አልጀር የተጫወተ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ግማሽ ላይ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ መልካም የሚባል ግልጋሎት ሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም። ጋናዊው ያኩቡ መሐመድ በበኩሉ ለሀገሩ ክለብ አዱዋና ስታርስ ከተጫወተ በኋላ ለታንዛኒያው አዛም ግልጋሎት ሰጥቶ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ የእግር ኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ሁለቱም ተጫዋቾች ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ከክለቡ ጋር ለመቆየት እንደተስማሙም ለማወቅ ተችሏል።