የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ግርማ ሃብተዮሃንስ በአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ እሁድ ሶማልያን የሚገጥመው ብሄራዊ ቡድናችንን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ ባረፈበት ኢትዮጵያ ሆቴል የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያም ከአሰልጣኝ ግርማ ጋር በጨዋታው እና ወቅታዊ የቡድኑ ሁኔታ ዙርያ አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡
ለቡድኑ 38 ተጫዋቾች ከተጠሩ በኋላ ተጨማሪ ተጫዋቾች ተካትተዋል፡፡ የመጨረሻዎቹን ተጫዋቾች ለመምረጥ ችግር አልፈጠረባችሁም?
“የምርጫው ሁኔታ ከጊዜው አንፃር ፈታኝ ነበር፡፡ ከ23 ክለቦች የተውጣጡ ተጫዋቾች በመያዝና የምርጫ ጨዋታዎች በማድረግ የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች ማስቀረት ስለነበረብን ከጊዜው አንፃር ችግር ነበረብን፡፡ ነገር ግን ካሉት ተጫዋቾች መካከል ጨዋታ በማድረግ የመጨረሻ 30 ተጫዋቾችን መርጠናል፡፡“
ተጫዋቾቹን የመረጣችሁበት መንገድ ምን ይመስላል?
“በመጀመርያ ደረጃ ከእድሜ ጋር የተያያዘውን መመዘኛ ስንመለከት ይህንን ምርጫ አድርገው ዝርዝሩን የላኩልን አካላት በተገቢው መስፈርት የተመረጡ ተጫዋቾች ልከውልናል ወይ የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የያዙትን የልደት ማስረጃ እና መታወቅያ በማየት ለመምረጥ ሞክረናል፡፡ በመቀጠል ችሎታቸውን እና ወቅታዊ አቋማቸውን በማገናዘብ የምንፈልጋቸውን ልጆች ካስቀረን በኋላ ለማጣራት ሞክረናል፡፡
“30 ተጫዋች ይዘን ለመዘጋጀት በምንሞክርበት ወቅት ደግሞ አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም ፓስፖርታቸው በካፍ የተመዘገበ በመሆኑ ከእድሜ በላይ ናቸው ተብለው ተቀንሰዋል፡፡ በጉዳት ምክንያት የተቀነሱም አሉ፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ሰአት 26 ተጫዋች በመያዝ በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡“
በሙገር ለታዳጊዎች በሚሰጡት ትኩረት ይታወቃሉ፡፡ በታዳጊዎች ላይ ያለዎት ልምድ ተጫዋቾችን በመለየት በኩል ጠቅሞታል?
“ልምዴ ጠቅሞኛል፡፡ ችሎታቸውን ለማነፃፀርም ችግር አልፈጠረብኝም፡፡ የመጀመርያው ጨዋታ እየተቃረበ የመጣ በመሆኑ እኛ ከምንሰጣቸው ይልቅ ራሳቸው ባላቸው ልምድ ነው እንዲዘጋጁ ያደረግነው፡፡ በእርግጥ በመጀመርያ ከተመረጡት መካከል ለመለየት ያገዘኝ ልምዴ ነው፡፡ ያሉትን በማነፃፀር በኩል ችግር አልገጠመኝም፡፡“
ቡድኑ ከተሰባሰበ ረጅም ቀናት ቢያስቆጥርም አብዛኛውን ጊዜ የወሰደባችሁ ተጫዋቾችን በመለየት ላይ ነው፡፡ ቡድኑ ወጥ በሆነ ሁኔታ ልምምድ የጀመረውም በሳምንቱ አጋማሽ ነው፡፡ በቀሩት ቀናት ለእሁዱ ጨዋታ ቡድኑን ማዘጋጀት አስቸጋሪ አያደርግባችሁም?
“ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾቹ ያላቸው እምቅ አቅም እና በክለባቸው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ባማከለ መልኩ ለማዋሃድ ጥረት አድርገናል፡፡ በስብስቡ የሚገኙት ተጫዋቾች ተስፋ ሰጪ እና ወደ ፊት መጓዝ የሚችሉ ናቸው፡፡
“ሶማልያን ለማሸነፍ የሚያበቃ ጥንካሬ አለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን ስል ግን እጅግ ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ማለት አይደለም፡፡ የዝግጅት ጨዋታዎች ማድረግ ባለመቻላችን ቡድናችን የተፈተነ አይደለም፡፡ የተጫዋቾቹን ብቃት ከተቃራኒ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማየት አልቻልንም፡፡ እንግዲህ በመጀመርያ ጨዋታቸው ምን ያሳያሉ የሚለውን እሁድ እናየዋለን፡፡
“እንደሚታወቀው የልምምድ እና የነጥብ ጨዋታ ይለያያል፡፡ እርስ በእርስ ከለመዱት ተጫዋቾች ጋር የመጫወት ስነልቦና እና በነጥብ ጨዋታ ላይ የሚኖረው ስነ ልቦና ይለያያል፡፡ እርስ በእርስ ጨዋታ ላይ በነፃነት የሚጫወት ተጫዋች በነጥብ ጨዋታ ላይ ሊደናገጥ ይችላል፡፡ ይሄን እንደችግር መናገር የምንችለው ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ቡድናችን ያለው አቅም ጥሩ ነው የሚል እምነት አለን፡፡“
ስለ ሶማልያ ምን ያህል ግንዛቤው አላችሁ?
“ብዙም መረጃ አላገኘንም፡፡ ዛሬ ጠዋት (ሀሙስ) የሶማልያውን አሰልጣኝ እና የቡድን መሪ ቀርቤ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡ ኬንያ 15 ቀን ቢዘጋጁም ለጨዋታው ያን ያህል እንዳልተዘጋጁበት ተረድቻለሁ፡፡ ”
ከእሁዱ ጨዋታ ምን እንጠብቅ?
“አንደኛ የሚጠበቀው እነዚህ ወጣቶች ወደፊት ሃገርን የሚረከቡበት አቅም አላቸው ዋናውን ብሄራዊ ቡድን ይተካሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ በምርጫ እና ሌሎች ጉዳዮች ችግር ቢታይ እንኳ ከድርጊቶች የምንማርበት ይሆናል፡፡ የሚስተካከሉ ነገሮችንም ከስፖርት አፍቃሪው እና ባለሙያው እንጠብቃለን፡፡ ሌላው ውጤት እንፈልጋለን፡፡ ለማሸነፍ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሟልተናል ባንልም ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው፡፡”