አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂውን ውል ማደሱ ታውቋል።
የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ቆይታ ለአንድ ዓመት ካራዘመ በኋላ ወደ ዝውውሩ በመግባት እስካሁን ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ የቀላቀለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከቡድኑ ጋር ጥሩ ቆይታ የነበራቸውን የስምንት ነባር ተጫዋቾቹንም ውል ማራዘሙ ይታወቃል። አሁን ደግሞ የመስመር አጥቂውን ፀጋ ደርቤን ውል አድሷል።
ከሀላባ ከተማ የታዳጊዎች ውድድር ተመልምሎ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአራት ዓመታት ቆይታውን በማጠናቀቅ የኢትዮ ኤሌትሪክን ተስፋ ቡድን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ፀጋ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በዋናው ቡድን ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ከኤሌክትሪኮች ጋር ለተጨማሪ አንድ ዓመት የሚያቆየውን ስምምነት ፈፅሟል። በኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ፀጋ ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን በቀጣይ የውድድር ዓመት የሊጉ ድምቀት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።