የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ዛምቢያ ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል፡፡ ስለ ቡድኑ ተያያዥ ጉዳዮችም ዛሬ በ5፡30 በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፣ አምበል ፣ የቡድን መሪው እና ቡድኑን የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት በተገኙበት ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ቡድኑ የተጨዋቾች አመራረጥ ስለ ዝግጅታቸው እና ስለ ዋናው አሰልጣኝ ኮንትራት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አሰልጣኝ ግርማ ሀ/ዩሃንስ
ስለ ተጨዋቾች መረጣ
‹‹እኛ ከነበረን እይታ በተጨማሪ ከከፍተኛ ሊግ ፣ ብሄራዊ ሊግ ፣ ፕሪምየር ሊግ እና ከተስፋ ቡድን ልዩ ልዩ ተጨዋቾችን ጠርተናል፡፡ እነዚህ የጠራናቸው ተጨዋቾች በኛ ብቻ ሳይሆን በፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የተመለመሉ ናቸው፡፡ ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተጨዋቾችን እንዲልኩልን እና እናም የማጣራት ስራውን እንድንሰራ ነበር አስበን ወደ ተጨዋች መረጣው የገባነው፡፡
‹‹ በአጠቃላይ 67 ተጨዋቾችን አሰባስበን በአምስት ቀን የማጣሪያ ጊዜያት ውስጥ ከ23 ክለቦች ከመረጣናቸው ተጨዋቾች ውስጥ ለኛ የሚኖኑንን ተጨዋቾች በመምረጥ 30 ተጨዋቾችን አጣርተን ወደ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ የስም ዝርዝራቸውን አስገብተናል፡፡ የተስፋ ቡድኖች ውድድር ተቋርጦ ስለነበር ብዙ ተጨዋቾችን ከውድድሩ ለማየት እድሉን አላገኘንም፡፡
‹‹ምርጫው መቶ በመቶ ትክክለኛ ነው ብለን አናስብም፡፡ የመረጥናቸው ተጨዋቾችም በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው እንደማይቀርቡ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ባለችን አጭር ጊዜ ስራዎችን ለመስራት ሞክረናል፡፡››
ስለ ዝግጅታቸው
‹‹ከመረጥናቸው 30 ተጨዋቾች ጋር መደበኛ ልምምዳችንን በምንሰራበት ወቅት የእድሜ ችግሮች የነበሩባቸው አምስት ተጨዋቾች ስለነበሩ እነሱን በመቀነስ 25 ተጨዋቾችን ይዘን ልምምዳችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ ብዙዎቹ ተጨዋቾች በውድድር ላይ የነበሩ ስለነበሩ በቀጥታ እኛ የቅንጅት ስራ ውስጥ ነው የገባነው፡፡ በዝግጅታችን በጊዜ እጥረት አንፃር የወዳጅነት ጨዋታ አለማግኘታችን እንደ ችግር ሊነሳ ቢችልም ሁሉም ተጨዋቾች ከጨዋታ ስለመጡ ያን ያህል የሚጎዳን አይመስለንም፡፡››
ስለ ምርጫ ፉክክር
‹‹ቡድኑ ውስጥ በተጨዋቾች መካከል ፉክክሮች ነበሩ፡፡ ከ67 ተጨዋቾች የመጨረሻው ምርጫ ላይ ለመግባት ተጨዋቾቹ የብሄራዊ ቡድንን ፍቅር ስለሚያቁት ጉጉት ነበራቸው፡፡ ይህንን ጉጉት እኛ እንደ መልካም አጋጣሚ ነው የተመለከትነው፡፡ ፉክክሮች ሲኖሩ እኛም ጥሩ ተጨዋች የመምረጥ እድላችን ያድጋል፡፡››
ስለ ተጋጣሚያቸው
‹‹ለቡድኖች ከፍተኛ ግምት አንሰጥም፡፡ ዝቅተኛ ግምትም እንደዛው፡፡ የነገው ተጋጣሚያችን ሶማልያንም ሆነ ሌሎች ቡድኖችን አግዝፈውም ሆነ አቅልለው እንዳያዩ ለተጫዋቾቹ ነግረናቸዋል፡፡››
ኢንጅነር ቾል ቤል
ስለ አስተዳደራዊ ጉዳዮች
‹‹በቡድኑ ውስጥ የእድሜ ማጭበርበሮች እንዳይኖሩ ቀደም ብለን ሁሉንም ተጨዋቾች ስንጠራ የልደት ሰርተፊኬታቸውን እንዲያመጡ አድርገናል፡፡ ይህንን ማጣራት በምናደርግበት ወቅት አምስት የሚሆኑ ተጨዋቾች ከ20 አመት በላይ ስለነበሩ እነሱን ቀንሰናል፡፡ ይህንን ማጣራት ካደረግን በኃላ ከአሰልጣኞች ጋር በመሆን ፓስፖርት ላልነበራቸው ተጨዋቾች ፓስፖርት አውጥተናል፡፡››
የአሰልጣኞች ቅጥር
‹‹ከዚህ በፊት የተለመደው የሶስት ወር ኮንትራት ነበር አሰልጣኞች የሚፈርሙት ነገር ግን ከዚህ በኃላ ከአሰልጣኖች ጋር ተነጋግረን ለስድስት ወር ለማስፈለም ችለናል፡፡ ከጨዋታም በኃላ ይህ ቡድን የዋናው ቡድን ተተኪ ስለሆነ ስልጠናዎችን በቀጣይነት ለማሰጠት እንጥራለን፡፡ በአስተዳደራዊ ስራዎች በኩል ለቡድኑ የሚሆኑ የትጥቅ ማሟላት ስራዎችንም በሚገባ ሰርተናል፡፡››