የሶማልያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰርቷል።
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ መሐመድ አብደላ ስብስባቸው በጥሩ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።
“ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ ልምምድ እየሰራን ቆይተናል። ላለፉት 2 ወራት ደግሞ አንድ ላይ በካምፕ በመሰባሰብ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታችን በፊትም 2 ሳምንታትን በናይሮቢ አሳልፈናል። በዚያ ከሚገኙ ሁለት የወጣት ክለቦች ጋር ባደረግነው የወዳጅነት ጨዋታም አበረታች ውጤት አስመዝግበናል። ስለዚህ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ብዬ መናገር እችላለሁ።”
ቡድኑ ከጨዋታው ቀደም ብሎ ረቡዕ ዕለት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን አዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው ኤስጂኤስ ሆቴል በመክተም ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል። በአዲስ አበባ ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ ማሳለፋቸው ቡድናቸውን ለማዘጋጀት እንደጠቀማቸው ነው አሠልጣኝ መሐመድ የተናገሩት።
“ለአራት ቀናት አዲስ አበባ ላይ መቆየታችን ጠቅሞናል ብዬ አስባለሁ። ከአየር ንብረቱ ጋር ለመላመድ ከመቻላችን በተጨማሪ ጥሩ የልምምድ ጊዜም ነበረን። እንግዳ ተቀባዩ የኢትዮጵያ ህዝብም ጥሩ አቀባበል አድርጎልናል፤ በዚህም ፌዴሬሽኑንና ህዝቡን ማመስገን እፈልጋለሁ።”
‘ፋሮያሬ’ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት አሠልጣኝ መሐመድ በአፍሪካ እግርኳስ ውስጥ ያላቸው ልምድ እና በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ያላቸው የስራ ሃላፊነት ለኢትዮጵያ እና በአጠቃላይም ለአፍሪካ እግርኳስ ቅርብ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡
“እኔ የካፍ የአሠልጣኞች ኢንስትራክተር እና A የማሠልጠኛ ፈቃድ ያለኝ በመሆኑ በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ሰፊ ልምድ አካብቻለሁ። የኢትዮጵያ እግርኳስም የዚሁ አንድ አካል በመሆኑ ነገ ስለምንገጥመው ቡድን አጨዋወት ግንዛቤው አለኝ።” ሲሉ ስለተጋጣሚያቸው በቂ መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል።
አሠልጣኙ በረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በተሻለ መረጋጋት ላይ በምትገኘው ሃገራቸው ያለው የእግርኳስ መዋቅር ገና በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኝ መሆኑ የወጣት ተጫዋቾች ቁጥርን ከፍ እንዳደረገውና ይህም የተጫዋች ምርጫቸው ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደነበረው አልሸሸጉም።
“በሶማሊያ በሶስት የደረጃ እርከን ላይ የሚገኙ የእግርኳስ ውድድሮች አሉን። በነዚህ ውድድሮች የሚሳተፉት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ወጣት እና ዕድሜያቸውም ከ20 ያልዘለለ ነው። ይህ ከሶስቱም ሊጎች ጥሩ ተጫዋቾችን እንድንመርጥ ዕድል ፈጥሮልናል። በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ እና የተሻለ ልምድ ያላቸው ሁለት ተጫዋቾችን ይዘናል። ግብ ጠባቂያችንና የቡድኑ አምበል የሆነው ሙሳ ወጣቶቹን ተጫዋቾቻችንን ይመራልናል ብለን ተስፋ አድርገናል። በቡድን ምርጫችን ደስተኛ ነን፡፡ አሉ የምንላቸውን ተጫዋቾች ይዘናል፤ የተጫዋች ጉዳት ስጋትም የለብንም።”
አሠልጣኙ በመጨረሻም በነገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንን ለመፈተን ወደሜዳ እንደሚገቡና ለዚህም በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሶማሊያ ተወላጆች ድጋፍ እንደሚያሻቸው ተናግረዋል።
“በነገው ጨዋታ ጥሩ የሚባል ውጤት ለማስመዝገብ ወደሜዳ እንገባለን። ያለንን አቅምም ሙሉ በሙሉ በማውጣት ኢትዮጵያውያኑን ለመፈተን ተዘጋጅተናል። ግብ እንዳይቆጠርብን በጥብቅ መከላከል እና ያገኘነውን አጋጣሚም በአግባቡ ተጠቅመን ግብ ማስቆጠር እቅዳችን ነው። በአዲስ አበባ የሚኖረው ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የሶማሊያ ተወላጅ ወደሜዳ በመምጣት እንዲደግፈን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ማስተላለፍ እወዳለሁ።”