“ያለምንም ጥርጥር የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ በሙሉ አቅማችን ወደ ሜዳ እንገባለን” ሱራፌል ዳኛቸው

በነገው ጨዋታ ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎችን እያደረስን ሲሆን አሁን ደግሞ የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከድረ-ገፃችን ጋር የነበረውን ቆይታ እናስነብባችኋለን።

ያለፉትን አራት ዓመታት ፋሲል ከነማን ያገለገለው እና ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከቡድኑ ጋር ቆይታ ለማድረግ በቅርቡ ፊርማውን ያኖረው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋችን አንደሆነ ይታወቃል። በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ የሆነው ሱራፌል ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን እና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋል።

ስለ ጤንነት ሁኔታው…

“ያጋጠመኝ የጉዳት ሁኔታ ታንዛኒያ ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር ስንጫወት ነበር። አሁን ከጉዳቴ ሙሉ ለሙሉ አገግሜ ጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ። ልምምዴንም በአግባቡ እየሰራሁ ለጨዋታ ዝግጁ መሆኔን መግለፅ እፈልጋለሁ።”

ስለ ቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ…

“ያለን ያዝግጅት ሁኔታ አሪፍ ነው። የቡድኑ መንፈስም በጣም ቆንጆ ነው። አዳዲስ የመጡ ልጆች አሉ ፤ ከእኛ ጋር እንዲዋሀዱ እየሰሩ ነው። ፋሲል ቤት ደስ የሚለው የቡድኑ መንፈሱ በጣም ጥሩ ነው።
ከትንሽ እስከ ትልቁ ያለው መከባበር ደስ የሚል እና ሁሉም በአንድ ስሜት ሚታይበት ቤት ነው። አዲስ ተጫዋች ሲመጣ የአዲስነት ስሜት እንዳይሰማው በቡድኑ ውስጥ የቆየን ልጆች የበኩላችንን እንወጣለን። አጠቃላይ የቡድናችን ስሜት በጣም ጥሩ ነው።”

አጣማሪዎቹ ከቡድኑ ጋር አለመኖራቸው…

“ያው በረከት እና ሙጂብ ትልልቅ ተጫዋቾች ናቸው። በብሔራዊ ቡድንም ተመራጭ ተጫዋቾች ናቸው። ከእኛ ጋር ቢቆዩ ጥሩ ነበር ፤ ግን ይሄ አልሆነም። በምትካቸው አሰልጣኞች ጥሩ ጥሩ ልጆችን አምጥተዋል። ያው እኛ ሀገር ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ባይኖርም እነሱን የሚተኩ ተጫዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለዋል። ልምምድ ላይም ያላቸው ነገር ደስ ይላል። ለመግባባት ከኛ ጋር ያላቸው ነገር ደስ ይላል። በነገው ጨዋታው በጋራ ሆነን ቡድኑን ለማገልገል እንሰራለን።”

ስለነገው ጨዋታ…

“ከዚህ ቀደም በዚህ የውድድር መድረክ ስንካፈል ለአራተኛ ጊዜ ነው። ጥሩ ልምድ አግኝተናል። ያለምንም ጥርጥር የነገውን ጨዋታ ከፈጣሪ ጋር ለማሸነፍ በሙሉ አቅማችን ወደ ሜዳ እንገባለን።”