አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀደም ብሎ ስምምነት ፈፅሞ የነበሩትን ሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም ተሳታፊ መሆን የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ እየከወነ የሚገኝ ሲሆን ከሳምንታት በፊት የቅድመ ስምምነት ፈፅመው የነበሩትን ሁለት ተጫዋቾች በይፋ በአንድ ዓመት ውል አስፈርሟል፡፡
አጥቂው ልደቱ ለማ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የስሑል ሽረ እና ባህርዳር ከተማ የፊት መስመር ተጫዋች አብዛኛዎቹን የእግርኳስ ዘመኑን በከፍተኛ ሊጉ ለገጣፎ ለገዳዲ በመጫወት በሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ሲገባ የምንመለከተው ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም ለገጣፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ሲችል በክለቡ ጥሩ ግልጋሎት መስጠት የቻለ ሲሆን በውሰትሞ በሀድያ ሆሳዕና በዓመቱ መጨረሻ አሳልፎ ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ኤሌክትሪክን ተቀላቅሏል፡፡
ሌላኛው ፈራሚ ደግሞ ናትናኤል ሰለሞን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ፍሬ የሆነው እና በአርባምንጭ ከተማ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ደግሞ በዲላ ከተማ ያሳለፈው የመስመር ተጫዋቹ መዳረሻው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሆነ ተጫዋች ሆኗል፡፡