የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ91 ቀናት ዕረፍት በኋላ ባሳለፍነው አርብ ጅማሮውን አድርጓል። እኛም ትላንት ፍፃሜውን ባገኘው የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹን ጉዳዮች በተከታዩ መልኩ አቅርበናቸዋል።
– የሊጉ የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ጌታነህ ከበደ ሆኗል። ቡድኑ ወልቂጤ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ሲረታ በ50ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ የሊጉ የመክፈቻ ግብ ሆና ስትቆጠር ከዚህ ባለፈም ግቧ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ከቆመ ኳስ የተቆጠረችም ግብ ሆና ተመዝግባለች።
– ቸርነት ጉግሳ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያው ከፍፁም ቅጣት ምት ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ሆኗል። ቡድኑ መድንን በሰፊ ጎል በተረታበት ጨዋታ በ58ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የፍፁም ቅጣት ምን ወደ ጎልነት ቀይሯል።
– ቶጎዋዊው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ መድንን 7-1 ባሸነፈበት ጨዋታ በ21ኛው ፣ በ43ኛው እና በ47ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች ሆኗል።
– ጋናዊው የፈረሰኞቹ የመሀል ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ መድን ላይ በግንባሩ ያስቆጠራት ግብ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ በጭንቅላት የተቆጠረች ግብ ሆናለች።
– ቢኒያም በላይ በአዲሱ የውድድር ዘመን በአንድ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረም ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለም ቀዳሚ ተጫዋች መሆን ሲችል በ47ኛው ደቂቃ ለእስማኤል ኦሮ-አጎሮ ሲያመቻች በ68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ መድን መረብ ላይ ግብ አስቆጥሯል።
– የለገጣፎ ለገዳዲው ግዙፍ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በሊጉ የመጀመሪያው በአንድ ጨዋታ ሁለት ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።
-የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አማካይ አብነት ደምሴ ለስንታየሁ ዋለጬ ግብ ኳሷን አመቻችቶ በመስጠት በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያዋን ግብ የሆነች ኳስ አመቻችቶ የሰጠው ተጫዋች ሆኗል።
-የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የመስመር ተከላካይ ታፈሰ ሰርካ ቡድኑ በባህር ዳር ከተማ በተረታበት ጨዋታ በ15ኛው ደቂቃ በፈፀመው ጥፋት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያውን የማስጠንቀቂያ ካርድ ሰለባ ሆኗል።
– የድሬዳዋ ከተማው ኤልያስ አህመድ ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በ89ኛው ደቂቃ ከዳኛ ጋር በፈጠረው አተካራ የመጀመሪያው በሊጉ በቀጥታ ቀይ ካርድ የተሰናበተ ተጫዋች አድርጎታል።
– በተመሳሳይ ጨዋታ የሲዳማ ቡናው የመሀል ተከላካይ ጊትጋት ጉት በ62ኛው እና 89ኛው ደቂቃ በተመለከታቸው ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ከሜዳ የተሰናበተው ቀዳሚ ተጫዋች ነው።
– የድቻው ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያው ማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ግብ ጠባቂ ነው።
– የኢትዮጵያ መድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ደግሞ ቡድኑ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ያሰጠ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።
– አሸናፊ አልያስ ፣ አህመድ ሁሴን እና መላኩ ኤልያስ የመጀመሪያዎቹ በውድድር ዘመኑ ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ሲሆኑ በአንፃሩ እንዳልካቸው መስፍን ፣ ተመስገን ደረሰ እና አካሉ አቴሞ የመጀመሪያዎቹ ተቀያሪ ተጫዋቾች ነበሩ።
– ጌታነህ ከበደ በአርባምንጩ ጨዋታ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለመውጣት መገደዱ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ በጉዳት ሳቢያ ተቀይሮ የወጣው ተጫዋች ያደርገዋል።
– የባህር ዳር ከተማው የመሀል ተከላካይ ተስፋዬ ታምራት በሊጉ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ የሊጉ የመጀመሪያው ግብ ያስቆጠረ ቀዳሚው ተጫዋች መሆን ችሏል።