ለፍፃሜው ሰከንዶች እስኪቀሩ ድረስ ያለግብ የዘለቀው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ባስቆጠረው ጎል ፈረሰኞቹን ባለድል አድርጓል።
አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከባህር ዳሩ ሽንፈት አጥቂ ቦታ ላይ አላዛር ሽመልስ እና አቤል ሐብታሙን በኢብራሂም ከድር እና ሄኖክ አየለ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ኢትዮጵያ መድንን 7-1 የረቱበተን አሰላለፍ ሳይቀይሩ መቅረብን መርጠዋል።
ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍ ባለ ጫና በማጥቃት የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ጭምር መፍጠር ችሎ ነበር። ሆኖም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት የገቡት ኤሌክትሪኮች ከኳስ ውጪ ክፍተቶችን በመድፈን ከኳስ ጋር ደግሞ የተሻለ የቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የጨዋታ ሚዛኑን ወደ ራሳቸው ወስደዋል። ሆኖም ቡድኑ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰራቸው የቅብብል ስህተቶች ከሙከራዎች አርቀውት ቆይተዋል።
በቀላሉ ክፍተቶችን ማግኘት የከበዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች 22ኛ ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ያሻገረው ኳስ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ከባከነ በኋላ ዳዊት ተፈራ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከቸርነት ጉግሳ በተቀበለው ኳስ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ያልተጠቀመበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ራሱ ዳዊት ከሳጥን ውጪ ባደረገው ሙከራ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረዋል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በፍጥነት ኳስ አስጥሎ ወደ ማጥቃት ከተሻገገረባቸው ቅፅበቶች ውስጥ አንዱ ወደ ሙከራነት ሲቀየር ታይቷል። 32ኛ ደቂቃ ላይ ከተነጠቀ ኳስ ሳጥን ውስጥ ደርሰው ኢብራሂም ከድር ያመቻቸውን ሄኖክ አየለ አክርሮ መትቶ ደስታ ደሙ ተደርቦበታል። በዚህም ሁለቱ ቡድኖች ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ተጋምሷል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ ከመሀል ከስንታየሁ ዋለጬ የተላከን ግሩም ኳስ ከተከላካይ ጀርባ በመግባት የተቆጣጠረው ፀጋ ደርቤ አመቻችቶለት ኢብራሂም ከድር ቢያስቆጥርም ፀጋ በእጅ ነክቷል በሚል ተሽሯል። ከዚህ ክስተት በኋላ ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ከኤሌክትሪክ የኳስ ቁጥጥር ይልቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር ጥቃት እየጎላ ሄዷል። በተለይም ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ 58ኛው ደቂቃ ላይ ከዚሁ አቅጣጫ ከሳጥን ውጪ ቀጥሎ ደግሞ ከሳጥን ውስጥ አከታትሎ ወደ ግብ የላካቸው የከረሩ ኳሶች ግብ ለመሆን ተቃርበው ቀዳሚው ለጥቂት ሲወጣ ተከታዩ በዘሪሁን ታደለ ጥረት የዳነ ነበር።
ከሁለቱ ሙከራዎች በኋላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ጫና ከፍ ብሎ ሲታይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተወሰደበትን ብልጫ ወደ ኋላ ቀርቶ በመቋቋም እና መሀል ላይ ኳስ በመንጠቅ በመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት አድርጓል። ከጊዮርጊስ የማጥቃት ሂደቶች ውስጥ 77ኛ ደቂቃ ላይ ተከላካዮች በአግባቡ ካላጠሩት ኳስ አጎሮ በዘሪሁን አናት ላይ ያሳለፈው ኳስ በጎሉ አግዳሚ ሲመለስበት 80ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ከቀኝ ወደ ሳጥን ውስጥ ያመቻቸለትን ተቀይሮ የገባው ሱለይማን ሀሚድ ነፃ ሆኖ አስቆጠረ ሲባል ደካማ ሙከራ አድርጓል። ተጫዋቹ 88ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገው አደገኛ ሙከራ በአንፃሩ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣ ነበር።
በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎችም ወደ ሁለቱም ሳጥኖች የሚደርሱ ፈጣን ጥቃቶች በጨዋታው ታይተው ያለግብ ተጠናቀቀ ሲባል ጭማሪ ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም ተቀይሮ የገባው የኤሌክትሪኩ አጥቂ አቤል ሐብታሙ በቀኝ ጌቱ ኃይለማሪያም ከረመዳን ነጥቆ በሰጠው ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ በቻርለስ ሉኩዋጎ ሲድንበት በሌላኛው ጫፍ የመጨረሻው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ረመዳን የሱፍ ያሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን የ1-0 ድል አስጨብጧል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለሁለተኛ ጊዜ በመጨረሻ ደቂቃ ነጥብ ማጣታቸው እንዳስገረማቸው እና ልምድ ማጣት ዋናው ምክንያት እንደሆነ አስረድተው የተከላካይ መስመራቸው ጥሩ እንደነበር ሆኖም የአየር ላይ ኳስ መከላከል ላይ ድክማት እንደታየባቸው ገልፀዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸውን አድንቀው ቡድናቸው ግድየለሽነት እንደታየበት ተናግረው 90 ደቂቃውን እስከመጨረሻው ጥረት በማድረግ መውጣታቸው ለውጤት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።