የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ነገ መደረግ ሲጀመሩ ዛንዚባር ላይ የሚደረገውን ጨዋታም አራት ኢትዮጵያዊያን በዳኝነት እንደሚመሩት ታውቋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የክለቦች ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የዘንድሮው የውድድር ዓመት የሁለተኛው ዙር ማጣሪያ መርሐ-ግብሮችም ከነገ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት መከናወኑን ይጀምራል፡፡ ነገ ከሚደረጉ የመጀመሪያ መርሐ-ግብሮች መካከልም 10፡15 ዛንዚባር ከተማ ላይ በአማኒ ስታዲየም የዛንዚባሩ ኪፓንጋ ኤፍ ሲ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እንዲመሩት ስለመመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ጨዋታውን የመምራቱ ሀላፊነት ሲሰጠው ክንዴ ሙሴ እና ትግል ግዛው በረዳትነት እንዲሁም ለሚ ንጉሴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡ አራቱም ዳኞች ረፋድ ላይ ወደ ስፍራው እንዳመሩም ታውቋል።