የአራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዲያ ሀሳዕና
የምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ከድል መልስ የሚገናኙት አዞዎቹ እና ነብሮቹን ያፋልማል። አምና በ18ኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማ 4-1 የመራበት እና ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ ደግሞ የዚህ መርሀ ግብር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ይታወሳል። በዘንድሮው አጀማመራቸው ሆሳዕናዎች ሁለት ተከታታይ ድሎችን በማሳካት ከመክፈቻ ሳምንት ጨዋታ ሽንፈታቸው ያገገሙ ሲሆን አርባምንጮች ደግሞ በተቃራኒው ከሁለት ሽንፈቶች በኋላ ሦስት ነጥብ አሳክተው ለነገው ጨዋታ ይደርሳሉ።
አዞዎቹ ከድል ጋር በታረቁበት የመቻሉ ጨዋታ አምስት ለውጦችን አድርገው የቀረቡት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የቡድናቸውን ሁነኛ ተመራጮች ሊያመላክታቸው የሚችል ሁለተኛ ድልን ማሳካት ይሻሉ። በሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገዱት አርባምንጮች የቀደመ የመከላከል ብርታታቸውን መመለስ ሲገባቸው በማጥቃቱም ረገድ አሁንም አጥጋቢ ደረጃ ላይ አሉ ለማለት አያስደፍርም። በእርግጥ የግለሰቦች ነጥሮ የወጣ ብቃት በድጋሚ ልዩነት ሊፈጥርላቸው ይችላል። በተለይም ከፊት ተመስገን ደረሰ በአጨራረሱ በኩል እያሳየ ያለው ብቃት እና ወጣቱ ቡጣቃ ሸመና ኳሶችን በፍጥነት ወደ አደጋ ዞን ያደርስ የነበረበት አኳኋን ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ጨዋታ ይዞት ሊሄድ የሚገባ ጠንካራ ጎን ነው።
በመቻል በጠባብ ውጤት በተሸነፉበትም ሆነ በቀጣዩቹ ሁለት ድሎች ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወደ ፊት ገፍቶ ጫና መፍጠር የሚያስችል ቡድን እንዳላቸው አሳይተዋል። ስቲቨን ናያርኮ እና ሪችሞንድ አዶንጎን ለመጀመሪያ ጊዜ በተጠቀሙበት የድሬዳዋው ጨዋታ ደግሞ ይበልጥ ፊት መስመር ላይ በቁጥር በርክቶ የመገኘት አዝማሚያን አሳይተዋል። ቡድኑ መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ላይ ይበልጥ መመርኮዙ የተገማችነት ጥያቄ ቢያስነሳበትም በተለይም ባዬ ገዛኸኝ ከመጨረሻ አጥቂነት ሚና ይልቅ ወደ መስመር እየወጣ በሚፈጥራቸው ክፍተቶች የአርባምንጭ ከተማን የመከላከል መዋቅር የሚጋፈጥበት አኳኋን በነገው ጨዋታ ከሚጠበቁ የሜዳ ውስጥ ፍልሚያዎች መካከል ትኩረት የሚስበው ሊሆን ይችላል።
የቡድን ዜናን በተመለከተ ሀዲያ ሆሳዕና በነገው ጨዋታ የአማካዮቹ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና የሳምሶን ጥላሁን መድረስ አጠራጣሪ ሆኖበታል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ ጉዳት ላይ ከነበሩ አራት ተጫዋቾች አህመድ ሁሴን እና በላይ ገዛኸኝ ሲመለሱ አንድነት አዳነ ያላገገመ ሲሆን የኤሪክ ካፓይቶ ለጨዋታው መድረስ እርግጥ አልሆነም።
ቡድኖቹ በሊጉ ከተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ አንድ ጊዜ ድል አድርጓል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ ስድስት አዞዎቹ ደግሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ጨዋታው በመሀል ዳኝነት በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ሲመራ ፣ ሙሉነህ በዳዳ እና ታምሩ አደም ረዳቶች ፣ ተካልኝ ለማ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለጨዋታው ተመድበዋል፡፡
ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
10:00 ላይ ሦስተኛ ጨዋታውን የሚያደርገው ባህር ዳር እና ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ያሳካው ድሬዳዋ ከተማ ይገናኛሉ።
ድሬዳዋ ከተማ አጀማመሩ እንዳሰበው አልሆነለትም። ወደ ከዚህ ቀደሙ የወራጅ ቀጠና አዙሪት ውስጥ ዘንድሮም ላለመግባት በቶሎ የአሸናፊነት ሥነልቦና የሚያስፈልገው በመሆኑም በነገው ጨዋታ የመጀመሪያ ድሉን ማሳካት በእጅጉ ያስፈልገዋል። በሆሳዕናው ጨዋታ የታየባቸው ግለሰባዊ ስህተቶች እና የቆመ ኳስ የመከላከል ድክመት አሁንም አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ቡድናቸው የሚፈልጉት የተግባቦት እና የእርጋታ ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ማስያ ሆኖ አልፏል። ቡድኑ በአመዛኙ ከመስመሮች የሚነሳው ጥቃቱን ተገማችነት መቀነስ እና የፈጠራ ምንጮቹን ማበራከት ሲጠበቅበት ጥሩ አጀማመር ላደረገው አዲሱ አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ በቂ ዕድሎችን መፍጠር ከቀሪው ተጫዋቾቹም ከችኩልነት የራቀ አጨራረስን አብዝቶ ይፈልጋል።
ባህር ዳር ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ፊት መስመር ላይ ችኩልነት ይታይበታል። ጨዋታዎቹን በሜዳው እንደማድረጉ በደጋፊዎቹ ፊት ድል ለማስመዝገብ ያለው ከፍ ያለ ፍላጎት በግብ ፊት ያለውን ስኬት እንዳያወርደው ማድረግ ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ይጠበቃል። ከቡድኑ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜ ላልነበራቸው አሰልጣኙ ከፋሲል ጋር የነበረው ጨዋታ በይደር መቆየቱ የፈጠረው የ13 ቀን ክፍተትም የተሻለ ለመዘጋጀት እንደሚረዳቸው ይታመናል። በዋነኝነት ዱሬሳ ሹቢሳን ያነጣጠሩ የቡድኑ የጥቃት ምንጮችን ማስቀጠልም ከጣና ሞገዶቹ የሚጠበቅ ሌላኛው የቤት ሥራ ይሆናል።
ያሬድ ባየህ እና ፈቱዲን ጀማል ከጉዳት የተመለሱለት ባህር ዳር ከተማ ኦሴይ ማዉሊ እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በጉዳት ሲያጣ የአለልኝ አዘነ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም አማካዩ ኤልያስ አህመድ በቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል።
የስድስት ጨዋታዎች ግንኙነት ያላቸው ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በድምሩ አስር ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ሦስት ድሎችን ያስመዘገቡት ባህር ዳሮች ስድስት እንዲሁም አንድ ጊዜ ያሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አራት ግቦችን አስመዝግበዋል።
ይህን ጨዋታ ባህሩ ተካ የመሀል ዳኛ ሆኖ የመምራት ኃላፊነት ሲሰጠው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና አሸብር ታፈሰ በረዳትነት ፣ ዳንኤል ግርማይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ግልጋሎት የሚሰጡ ይሆናል፡፡