በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች መካከል የሚጠቀሰው ሀምበሪቾ ዱራሜ የዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል፡፡
በተጠናቀቀው የ2014 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ እየተመራ በሁለተኛው ዙር ባሳየው ጠንካራ አቋም በምድብ ሐ ደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ላይ ተቀምጦ የፈፀመው ሀምበሪቾ ዱራሜ ለዘንድሮው የ2015 የውድድር ዘመን የአሰልጣኙን ውል ካደሰ በኋላ ከተለያዩ ክለቦች ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ በማድረግ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡
ደስታ ጊቻሞ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን ፣ ደቡብ ፓሊስ እና አዳማ ከተማ ተከላካይ ያለፈውን ዓመት በስልጤ ወራቤ ከቆየ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻው ሀምበሪቾ ሆኗል፡፡ ዳግም በቀለ ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል። የቀድሞው የወላይታ ድቻ ተጫዋች ያለፈውን የውድድር ጊዜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሳልፎ በድጋሜ ሀምበሪቾን ተቀላቅሏል፡፡
ክለቡ ከሁለቱ በተጨማሪ መስቀሉ ሌቴቦ ተከላካይ ከወራቤ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ አማካይ ከዱራሜ ከተማ ፣ በረከት ወንድሙ አማካይ ከልጤ ወራቤ ፣ ምንተስኖት ታምሬ አማካይ ከደቡብ ፓሊሰ ፣ ቃልአብ ጋሻው አማካይ ከገላን ከተማ ፣ አልዓዛር ዝናቡ አጥቂ ከየካ ክፍለከተማ እና እንግዳዘር ታከለ አማካይ ከሺንሺቾ ከተማ ማስፈረሙ ታውቋል።
ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ ክለቡ የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡