በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ቀይሮ ባስገባቸው ሁለት ተጫዋቾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 መርታት ችሏል።
10፡00 ላይ የኢትዮጵያ መድን እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሲደረግ መድኖች በስድስተኛው ሳምንት በባህርዳር ከተማ 3-2 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ሀቢብ መሀመድ በአስጨናቂ ጸጋዬ ተተክቶ ጀምሯል። ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በስድስተኛው ሳምንት በወልቂጤ ከተማ 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አላዛር ሽመልስ ፣ ናትናኤል ሰለሞን ፣ ሙሴ ከበላ እና ኢብራሂም ከድር በማታይ ሉል ፣ ምንያህል ተሾመ ፣ ሄኖክ አየለ እና ሚኪያስ መኮንን ምትክ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩም በኩል ኤሌክትሪኮች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የሜዳው ምቹ አለመሆን ቢፈትናቸውም ሁለቱም ቡድኖች ብዙ የተሳኩ ቅብብሎችን ማድረግ ችለዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሰለሞን ከረጅም ርቀት በግራ እግሩ ወደ ግብ የሞከረውና የግቡን የቀኙ ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በጨዋታው የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ከተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። 27ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ዮናስ ገረመው ኢብራሂም ከድር ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሙሴ ከበላ ከረጅም ርቀት በጥሩ ሁኔታ ወደግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ሊያስወጣው ችሏል። ኤሌክትሪኮች በኢብራሂም ከድር መድኖች በኪቲካ ጅማ እና ሲሞን ፒተር የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። መድኖችም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች የመጨረሻ ኳሳቸው ብዙም ውጤታማ አይሁን እንጂ በተሻለ መልኩ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ በቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክር ኳሱ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ይሄም መድኖችን ያስቆጨ ትልቁ አጋጣሚ ነበር።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያቸው የሆነውን ሙከራ 65ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ናትናኤል ሰለሞን በግንባሩ በመግጨት ያቀበለውን ኳስ ወደቀኙ የሜዳ ክፍል ካመዘነ ቦታ ላይ ያገኘው ኢብራሂም ከድር ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኗል። ኤሌክትሪኮች በፀጋ ደርቤ እና ናትናኤል ሰለሞን የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ በተለይም ናትናኤል ሰለሞን ከሳጥን ውጪ የሞከረውና የላዩን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
74ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሲሞን ፒተር ወደግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ የመለሰው እና የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በትክክል ያላራቁትን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አሚር ሙደሲር ማስቆጠር ችሏል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከተጋጣሚ የሳጥን ጫፍ ላይ የነበረው ሲሞን ፒተር ከተጋጣሚ የሳጥን ጫፍ ላይ ሆኖ እና 82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አሚር ሙደሲር ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸውን ግሩም ሙከራዎች ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በጥሩ ብቃት አድኗቸዋል። 87ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው ተቀይሮ የገባው ሀቢብ ከማል ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ የመድንን መሪነት አጠናክሯል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌም ታክቲካዊ ቅያሪያቸው ውጤታማ ሆኖላቸዋል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ ፀጋ ደርቤ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ልደቱ ለማ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በግቡ አግዳሚ በኩል በፍጥነት ወደውጪ ሊያስወጣው ችሏል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ቡድናቸው ውስጥ የልምድ ማነስ መኖሩና ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ አለማግኘታቸው እንደፈተናቸው ሲናገሩ መድኖች ቀይረው ያስገቧቸው ተጫዋቾች ውጤታማ እንደነበሩ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በቡላቸው በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ገልጸው ውድድሩ ገና ቢሆንም የደረጃ ሠንጠረዡን መምራት መጀመራቸው የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ያላቸውን ሀሳብ ተናግረዋል።