በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ቡናማዎቹን 3-1 በመርታት ወደ መሪዎች የተጠጉበትን ድል አስመዝግበዋል።
10፡00 ላይ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታቸው የተራዘመባቸው ኢትዮጵያ ቡና እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ቡናማዎቹ በስድስተኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 3-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሕዝቅኤል ሞራኬ ፣ ዘነበ ከድር ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና አንተነህ ተፈራ በበረከት አማረ ፣ ሄኖክ ድልቢ ፣ አሥራት ቱንጆ እና ጫላ ተሺታ ተተክተው ጀምረዋል። የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው በስድስተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 3-2 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ በሄደው ታፔ አልዛዬር ሲተካ ኦሴ ማውሊ ደግሞ በተስፋዬ ታምራት ተተክቶ ጀምሯል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ቡናማዎቹ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ግን ባህርዳር ከነማዎች የተሻሉ ነበሩ። 3ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ኢሳይያስ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ባሻማውና ኦሴ ማውሊ በደረቱ አብርዶ ተገልበጦ ባደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በተደጋጋሚ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት የጣና ሞገዶቹ የመጨረሻ ኳሳቸው ብዙም ውጤታማ አይሁን እንጂ በዱሬሳ ሹቢሳ እና ኦሴ ማውሊ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር።
23ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ መሪ መሆን ችለዋል። ሄኖክ ኢሳይያስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የቡናው ተከላካይ ኩዌኩ ዱሃ መቆጣጠር ባለመቻሉ ያገኘው ዱሬሳ ሹቢሳ ለመግፋት ሲሞክር ጥፋት ቢሠራበትም በድጋሚ ኳሱን ያገኘው ኦሴ ማውሊ ለፉዐድ ፈረጃ ሲያመቻችለት ፉዐድ ፈረጃ ከሳጥን ውጪ በድንቅ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
ግቡ ከመቆጠሩ ከሰከንዶች በፊት ወሳኙ አማካያቸውን አማኑኤል ዮሐንስ ያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጎዶሎ በሆኑበት ቅፅበት ግብ ቢያስተናግዱም ወዲያው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ኳሱን ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን በቀላሉ ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መገኘት አልቻሉም። በተቃራኒው ከኳስ ውጪ የአማካይ መስመሩን የተቆጣጠሩት ባህር ዳሮች በ35ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ ነበር። በዚህም ከመልስ ውርወራ የተነሳውን ኳስ የግቡ ባለቤት ፉዐድ ፈረጃ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ሊያስወጣው ችሏል።
44ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ድልቢ ከግራ መስመር ያሻማውና ያሬድ ባየህ ለማውጣት ሲሞክር በእግሩ ሳያገኘው ቀርቶ የግቡን የቀኙ ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በቡናማዎቹ በኩል የተሻለ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ነበር። እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ ደርሰው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያ ደቂቃዎች ባህርዳር ከተማዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ዱሬሳ ሹቢሳ ወደፊት ያሻማውን ኳስ የቡናው ተከላካይ ወልደአማኑኤል ጌቱ በእግሩ ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ፋሲል አስማማው ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር አብሮት ተቀይሮ ለገባው ፍጹም ጥላሁን አቀብሎት ፍጹም በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል። አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ያደረጉት ታክቲካዊ ቅያሪም በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ወጤታማ አድርጓቸዋል።
ወደተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ በአለልኝ አዘነ ፣ ፋሲል አስማማው እና ፍጹም ጥላሁን ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። በጨዋታው የመጨረሻ 20 ደቂቃዎችም በራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በዝተው ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ወሳኙን አማካይ አማኑኤል ዮሐንስ ያጡት ቡናማዎቹ የተከላካይ መስመር ላይ ከሚሠሩት ስህተት በተጨማሪ መሃል ላይ በተሳኩ ቅብብሎች የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የተሻለ ወደፊት ተጠግተው የተጫወቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያቸው የሆነውን የግብ ዕድል 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ያሬድ ባየህ ጫላ ተሺታ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሮቤል ተክለሚካኤል አስቆጥሮ የአሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ቡድን ወደጨዋታው መልሷል።
ቡናማዎቹ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ባልተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት እየተጠጉ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ባህርዳር ከተማዎች በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ካገኘው ፋሲል አስማማው ላይ ሮቤል ተክለሚካኤል ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ያሬድ ባየህ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በባህርዳር ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይም የአማኑኤል ዮሐንስ በጊዜ በጉዳት መውጣት ተጨምሮበት ጥሩ እንዳልነበሩ እና በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻሉ እንደነበሩ ሲናገሩ ጨዋታቸውን ለማስተካከል በሚጥሩበት ሰዓት የሚቆጠሩባቸው ግቦች ለመቸገራቸው ምክንያት እንደነበሩ አስረድተዋል። የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር ገልጸው እንደ ቡድን የተሻሉ እና አጥቅተው መጫወትን መርጠው ገብተው የፈለጉትን ማግኘታቸውን ሲናገሩ በማሸነፍ ውስጥ እያስተካከሉት የሚሄዱት ነገር እንደተመለከቱ ሀሳባቸውን ገልጸዋል። ውጤቱንም ለባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች በስጦታ አበርክተዋል።