በትናትናው ዕለት ክለቡ ያሰናበታቸው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ዳግም ወደ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲመለስ ያስቻሉት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በቡድኑ ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላመጡም በማለት ክለቡ እንዳሰናበታቸው ይታወሳል።
አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ‘ቀሪ የውል ዘመን እያለኝ ያለ አግባብ ክለቡ ውል አፍርሶ ያቋረጠ በመሆኑ የዘጠኝ ወር ደመወዜ እንዲከፈለኝ እና መልቀቂያ እንዲሰጠኝ’ በማለት ለፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ በደብዳቤ አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን አቶ ብርሀኑ በጋሻው የህግ አማካሪ እና ጠበቃ መረጃውን አድርሰውናል።
ጉዳዩን አስመልክተን ለክለቡ ሥራ አስክያጅ አቶ አሸናፊ ባቀረብነው ጥያቄ “ክለቡ የሚያቀው ለጊዜው መነሳቱን እና በምትኩ በጊዜያዊነት አሰልጣኝ መሾሙን ነው። እርሱ ቅሬታውን ለፌዴሬሽን አቅርቦ ይሆናል። እኛ ጋር እስካሁን የደረሰን ነገር የለም የሚመለከተው አካል ፌዴሬሽኑ የሚጠይቀንን ጥያቄ ተከትሎ ክለቡ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።” የሚል ማብራሪያ ሰጥተውናል።