👉”እግር ኳስ የሥነ-ልቦና ጉዳይ ስለሆነ የዛሬው ማሸነፋችን ሌላ ማሸነፍ ይዞ ይመጣል የሚል ዕምነት አለኝ” ተመስገን ዳና
👉”ኢትዮጵያ ቡና ይሄን ያህል በጨዋታው ተጽዕኖ ፈጥሮ ነው የሚል ነገር የለኝም” ገዛኸኝ ከተማ
አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው…
“በጣም ጥሩ እንቅሴቃሴ ነው ያደረግነው። በተለይ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ስንሰራ የነበረው ስህተት ላይ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህ ጨዋታ ደስ የሚል ነገር ከተጫዋቾቼ አግኝቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ከጎል ርቀው የነበሩት ብሩክ እና መሐመድኑር ግብ ስለማቆጠራቸው…
“በዋናነት ዛሬ ፎርሜሽን ቀይረን ነው የገባነው፡፡ ፎርሜሽኑ የእነርሱን እንቅስቃሴ ህይወት እንዲዘራበት የሚያደርግ እንዲሆን አስበናል። በ3-5-2 ነበር የገባነው። መሐመድም ሆነ ብሩክ በተጋጣሚ ተከላካዮች መሀል እንዲቆሙ አድርገን ነው ያጫወትናቸው ፤ ስለዚህ ትክክለኛ ቦታቸው ይሔ ነው፡፡ ብሩክ በዕርግጥ እንደ ዘጠኝ ቁጥር ነው ሲጫወት የነበረው። ነገር ግን በቅርበት የሚያግዘው ሰው ስለሌለ ሲባክን ነበር ፤ መሐመድኑር ዛሬ ከእርሱ ጎን መኖሩ በርካታ ነገርን እንድንመለከት አድርጎናል። ስለዚህ ጥሩ ነገር ነው ያየውት፡፡
3ለ2 ውጤቱ ሲሆን ስለነበረው ጫና…
“ቡድናችን የማሸነፍ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረው ስለመከላከል አይደለም ዛሬ ስናስብ የነበረው ፤ ጨዋታውን ለመግደል ተጨማሪ ጎል ማግባት አለብን ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጎሎች አግብተን ማፈግፈግ ራሳችን ላይ አደጋ ይፈጥራል በሚል ተነጋገርን ነበር። ግን ክፍተቶች ነበሩ። ያገኘናቸውን ዕድሎች ብንጠቀም ምን አልባት ስለገባብን ጎል አናወራም ነበር። በርካታ ዕድሎችን ፈጥረናል ፤ እነዛን ዕድሎች መጠቀም አለመቻላችን እነርሱን የልብ ልብ ሰጥቷቸው እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡
በድሬዳዋ ስለተገኘው የመጀመሪያ ድል እና ስለቀጣይ ጨዋታዎች…
“እንግዲህ ጥሩ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ማሸነፍ ሌላ ማሸነፍን ይዞ ይመጣል፡፡ መሸነፍ ደግሞ ሌላ መሸነፍን ይዞ ያመጣል ፤ ስለዚህ እግር ኳስ የሥነ-ልቦና ጉዳይ ስለሆነ የዛሬው ማሸነፋችን ሌላ ማሸነፍ ይዞ ይመጣል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡”
አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ) – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ስለ ጨዋታው…
“ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ተጫዋቾች ላይ ጉዳት አለ ፤ እንደጠበቅነው ባይሆንም ጥሩ ነው።
የአሰልጣኝ ሽግሽጉ ስላለው ተጽዕኖ…
“አንድ ቡድን ከአንድ ከአሰልጣኝ ወደሌላ አሰልጣኝ በሚሄድ ሰዓት ሽግግር ያስፈልገዋል ፤ ግን ያን እንደምክንያት ልናቀርበው አንችልም። ባለበት ነው ማስቀጠል የነበረብን ባለበትም አስቀጥለነዋል። እንደ ምክንያት ላየው አልችልም።
ቡና በተለየ አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ መግባቱ ስለፈጠረባቸው ነገር…
“ይሄ በእኛ ላይ ያመጣው ነገር የለም። የራሳችንን ጨዋታ ጠብቀን መጫወት አለመቻላችን ነው አንዱ ትልቁ ችግር ብዬ የማስበው። ሁለተኛው ነገር ደግሞ ተጫዋቾች አልተረጋጉም ነበር። እስክንረጋጋ የወሰደው ጊዜ በስህተትም ታግዞ ግብ ተቆጥሮብናል። እነዛ ነገሮች እንጂ ቡና ያን ያህል የተለወጠ ነገር ኖሮት አይደለም
ጨዋታውን ያጡት በተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ ወይስ በእነርሱ ድክመት ስለመሆኑ
“የተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ የምለው ነገር የለኝም። የእኛ ተጫዋቾች በፊት በነበሩበት ላይ አይደሉም ፤ ይሄ ነው የጨዋታው ችግር። ኢትዮጵያ ቡና ይሄን ያህል በጨዋታው ተጽዕኖ ፈጥሮ ነው የሚል ነገር የለኝም።”