የ2016 የባንግላዴሽ ሊግ ከመጀመርሩ በፊት የሚደረገው የኢንድፔንደንስ ካፕ በዚህ ሳምንት ተጀምሯል፡፡ ሁለት ምድብ ተከፍሎ 11 የሊጉ ክለቦችን በሚያወዳድረው በዚህ ዋንጫ በምድብ ለ የሚገኘው ሼይክ ረሰል የመጀመርያ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊው ፍቅሩ ተፈራም ግብ ቀንቶታል፡፡
ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ አራምባግ ክሪራ ሳንጋህን በባንጋባንዱ ናሽናል ስታድየም የገጠመው ሼይክ ረሰል 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል ሲጀምር የህንዱ ቼናይን ክለብን ለቆ በቅርቡ ለክለቡ ከፈረመ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው ፍቅሩ ተፈራ የሼይክ ረሰል የመጀመርያ ግቡን ለማግኘት የፈጀበት ደቂቃ 4 ብቻ ነበር፡፡
ኬስተር በ2ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ አራምባንግን ቀዳሚ ቢያደርግም ከሁለት ደቂቃ በኋላ ፍቅሩ ተፈራ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ጨዋታው ሊገባደድ 8 ደቂቃ ሲቀረው ፖል የሸይክ ረሰል የማሸነፍያ ግብን ከመረብ አሳርፏል፡፡