የሊጉ 10ኛ ሳምንት ነገ ሲጀምር የሚከናወኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ !
መቻል ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ውድድሩ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ካመራ ወዲህ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የተሳናቸው መቻል እና ኤሌክትሪክ ነገ 10:00 ላይ በፌደራል ዳኛ ብርሀኑ መኩሪያ መሪነት ይፋለማሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል ላይ ለሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ይህ ጨዋታ የተሻለ የማገገም ዕድል ይዞላቸው እንደሚመጣ ይገመታል።
በሲዳማ ቡና የ2-0 ሽንፈት ያስተናገደው መቻል አሁንም ብዙ የክህሎት ክምችት ካለው የወገብ በላይ የቡድኑ ክፍል የሚፈልገውን ያገኘ አይመስልም። በሲዳማው ሽንፈት ከዚህ ድክመት ባለፈ በኋላ መስመሩ ስህተቶችን መፈፀሙ ደግሞ ሌላው የነገ ስጋቱ ሆኗል። በዚህም ሁለት ግቦችን ለማስተናገድ ሦስት ጨዋታዎችን የፈጀው መቻል በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦች ተቆጥረውበታል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት ግን ቡድኑ ድል ለማድረግ ካለው ጉጉት የተነሳ የሚያባክናቸው ኳሶች የተከላካይ መስመሩን ይበልጥ ለጫና እንደሚዳርገው የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው መቻል በንፅፅር ቀለል ካለው የነገው ተጋጣሚው ሙሉ ነጥብ ለማሳካት ማሻሻል የሚገባው ዋነኛው ድክመቱም ይኸው ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የሚመነጨው ዕድሎችን ተረጋግቶ ወደ ግብነት የመቀየት ችግሩ እንደሆነ መናገር ይቻላል።
ከነገ ተጋጣሚያቸው በተሻለ የአጨራረስ ብቃት በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ያስቆጠሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ዋናው ራስ ምትሀት ደግሞ በተመሳሳይ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው የኋላ መስመራቸው ነው። የተለያዩ የመሀል ተከላካይ ጥምረቶችን በማሰባጠር የሞከረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ነገም በዚሁ ቦታ ላይ ለውጦችን ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል። ከግለሰባዊ ስህተቶች ባለፈ የተረጋጋ የመከላከል አደረጃጀትን ሲያጣ የሚታየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቡናው ጨዋታ ለመስመር ጥቃቶች ተጋልጦ መታየቱ ነገም ተመሳሳይ ችግር እንዳያገኘው ያሰጋዋል። ከዚህ ባለፈ የተሻለ የሚባለውን የቡድኑን የአማካይ ክፍል አፈፃፀም መጨመር እና በሁለቱም ሽግግሮች ላይ ተፈላጊውን ተፅዕኖ እንዲፈጥር ማድረግ ከኤሌክትሪክ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ይጠበቃል።
የመቻሎቹ ተሾመ በላቸው እና ቾል ላም በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። ኢትዮ ኤሌትሪክ ደግሞ ማታይ ሉል እና ምንያህል ተሾመ ሲመለሱለት ተስፋዬ በቀለ ፣ አላዛር ሽመልስ እና አንዳርጋቸው ይላቅ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾቹ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 26 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 10 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 5 አሸንፎ በ11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 28 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 39 ግቦች አሉት።
ኢትዮጵያ መድን ከ ሀዋሳ ከተማ
ምሽት 01:00 ላይ በፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው ፊሽካ የሚጀምረው ጨዋታ ከሽንፈት የተመለሱት መድን እና ሀዋሳን ያገናኛል። በተመሳሳይ የዓመቱን ሦስተኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ለአራተኛ ጊዜ ያለነጥብ ከሜዳ ላለመውጣት ይፋለማሉ።
የሊግ መሪነታቸውን ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመለሱት መድኖች በዚህ ጨዋታ ቢያንስ እስከ ረቡዕ ድረስ ወደ ቦታቸው መመለስ ይችላሉ። ይህንን ለማድረግ ግን ውድድሩ ሲጀመር በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በመሀል በባህር ዳር ከተሸነፉ በኋላ በፍጥነት ወደ ድል የተመለሱበትን መላ በድጋሚ መተግበር ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ አሁንም ከሀብታሙ ፣ ዮናስ እና ዑሙር የአማካይ ጥምረት የሚፈልገውን የጨዋታ ቁጥጥር እያገኘ መሆኑ የድል ምልሰቱን ለማሳካት ዋነኛ ግብዓቱ እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም በድሬዳዋው ጨዋታ ፊት መስመር ላይ የታየበት የአጨራረስ ድክመት እና ከዛም በላይ ደግሞ ሁለት ጨዋታዎችን መረቡን ሳያስደፍር ቆይቶ ከድሬ ጋር በስህተቶች የታጀበ ጊዜ ለማሳለፍ የተገደደበትን የኋላ መስመር ችግር መፍታት በእጅጉ ያስፈልገዋል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ክፍተቱ ከራስ መተማመን መውረድ የመነጨ መሆኑን መጠቆማቸውም ምንአልባት ነገ ከኋላ ለውጦች ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማል።
ሀዋሳ ከተማ አሁንም ወጥ አቋም ያለማሳየት ድክመቱ እንደቀጠለ ነው። በሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ ላይ ያሳካቸው ሁለት ድሎች ከተጋጣሚዎቹ ክብደት ብቻም ሳይሆን ግብ ሳያስተናግድ 180 ደቂቃዎችን መዝለቅ በመቻሉ ቡድኑ ወደ አንድ መስመር እየገባ እንደሆነ የሚያስገምት ነበር። ሆኖም ሀዋሳ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ተቆጥሮበት አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ አሁንም እጅግ ደካማ የሆነው የመከላከል አደረጃጀቱ የድክመቱ ምንጭ ስለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ ይችላል። ከዚህ ባለፈ ፈጣን ጥቃቶችን በመሰንዘር ተጋጣሚ ሳይደራጅ ሳጥን ውስጥ የሚገባበትን ጥንካሬውን በወጥነት ማሳየት ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ለነገ የሚጠበቅ በጎ ጎን ነው። ይህንን ወደ ውጤት በመቀየሩ ረገድ ግን እስካሁን በአምስት ጎሎች ከፍተኛ አስቆጣሪው ከሆነው ሙጂብ ቃሲም ውጪ ወደ ሜዳ መግባቱ ክፍተቱን በአግባቡ የመሸፈን የቤት ሥራ ይሰጠዋል።
ኢትዮጵያ መድን ሳሙኤል ዮሐንስ እና ቻላቸው መንበሩን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ መጠቀም የማይችል ሲሆን ብርሀኑ አሻሞ በቅጣት አዲሱ አቱላ እና ሙጂብ ቃሲም ደግሞ በጉዳት በነገው የሀዋሳ ከተማ ቡድን ዝርዝር ውስጥ አይካተቱም።
ሀዋሳ እና መድን በሊጉ 24 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 12 ፤ መድን 4 ጊዜ ሲረቱ ፤ ቀሪዎቹን 8 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ 32 ሲያገባ መድን በበኩሉ 23 አስቆጥሯል።