መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩት ሳቢ ሁለት ጎሎች አቻ ተለያይተዋል።
መቻል በሲዳማ ቡና ሁለት ለምንም ከተረታበት ስብስቡ ሳሙኤል ሳሊሶን በከነዓን ማርክነህ ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ለኢትዮጵያ ቡና ካስረከበው ሦስት ነጥብ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጧል። በዚህም የግብ ዘቡ ዘሪሁን ታደለን በፍቅሩ ወዴሳ፣ ተከላካዩ አንዳርጋቸው ይሳቅን በማታይ ሉል እንዲሁም የመስመር አጥቂው ፀጋ ደርቤን በኢብራሔም ከድር ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት መቻሎች በ6ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ሙከራ ሰንዝረዋል። የመዓዘን ምት ሲሻማ በሩቁ ቋሚ የነበረው ከነዓን ማርክነህ አግኝቶት ወደ ግብ ቢመታውም ኳስ የግቡን የግራ መረብ ታኮ ወጥቶበታል። እስከ 27ኛው ደቂቃ ድረስ የግብ ዘቡ ዳግም ተፈራን መፈተን ያልቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጀርባ ሆነው ያሳለፉ ሲሆን አልፎ አልፎ ብቻ ረጃጅም ኳሶችን በመላክ የተጋጣሚ ሳጥን ጋር እየደረሱ የግብ ምንጭ ለመፈለግ ሲጥሩ ተስተውሏል። በመሐል መቻሎች በ23ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ በሞከረባቸው የቅጣት ምት ጥቃት ግን ግብ ሊያስተናግዱ ነበር።
በ27ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጀመሪያ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራው የመጀመሪያ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም የቀኝ መስመር አጥቂው ናትናኤል ሰለሞን በረጅሙ የተመታን ኳስ ሔኖክ አየለ ከቶማስ ስምረቱ ጋር ታግሎ በግንባሩ ሲገጨው ከሳጥኑ ጫፍ ተቀብሎ በድንቅ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት አክርሮ ለመምታት የሞከረውን ኳስ አጨናግፈውት በፈጣን ሽግግር ወደ መቻል ሳጥን ወስደውት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ተመልሰዋል።
በቀላሉ የኤሌክትሪክን የኋላ መስመር መስበር ያልቻሉት መቻሎች ከሳጥን ውጪ አክርረው መምታታቸውን ተያይዘውታል። በተለይ ሁለቱ አማካዮች ተስፋዬ እና ምንተስኖት በተደጋጋሚ ከራር ኳሶችን ሲመቱ ታይቷል። የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመሩት 4 ደቂቃዎች መባቻ ላይ ደግሞ በቁጥር በዝተው ሳጥን ውሰጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም በወረደ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ከነዓን እና ምንይሉ ዕድሉን አምክነውታል።
የመሐል ተከላካይ በመቀነስ የአማካይ ተከላካዩን ምንተስኖት ወደ ኋላ ስበው ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርቦ የሚጫወት ተጫዋች በሁለተኛው አጋማሽ ያስገቡት መቻሎች ገና በ46ኛው ደቂቃ ፈጣን አጀማመር በማድረግ አቻ ለመሆን ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። በዚህም ፍፁም ዓለሙ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ መሬት ለመሬት ሲያሻማው ምንይሉ በአንድ ንክኪ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታል። መቻሎች ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለው በ58ኛው ደቂቃ የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህም ፍፁም ዓለሙ ሳጥኑ ጫፍ ከምንይሉ የተቀበለውን ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ መዳረሺያውን የፍቅሩ ወዴሳ መረብ አድርጎታል።
እጅግ ተነቃቅተው ወደ ሜዳ የገቡት የአሠልጣኝ ፋሲል ተጫዋቾች ከነዓን ማርክነህ በደቂቃዎች ልዩነት ከቆመ ኳስ እና ከክፍት ጨዋታ በተፈጠሩ ተከታታይ ዕድሎች ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። የመቻል ጫና የበረታባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግቡን እንዳስተናገዱ ሦስት የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። 65ኛው ደቂቃ ላይም የግቡ ባለቤት ናትናኤል በቀኝ መስመር ተከላካዮችን በመቀነስ ጥሩ ዕድል ፈጥሮ ቡድኑን ዳግም መሪ ለማድረግ ቢጥርም ግብ ጠባቂው ዳግም ውጥኑን አምክኖበታል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም መቻሎች በተደጋጋሚ የኤልፓን የግብ ክልል ቢጎበኙም ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር አልቻሉም። ኤሌክትሪኮችም እጃቸው የገባውን አንድ ነጥብ ላለማጣት ክፍተቶችን መዝጋት እና ኳሶችን ማጨናገፍ ላይ ተጠምደው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች አሳልፈዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት አንድ እኩል ፍፃሜውን አግኝቷል።