“ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር አልተሳካም” ፋሲል ተካልኝ
“ስህተቶቻችን ብዙ ጊዜ ዋጋ እያስከፈሉን ነው” ገዛኸኝ ከተማ
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – መቻል
ስለ ጨዋታው…
እንደ ጨዋታ ጥሩ ነው። በመጀመሪያውም በሁለተኛውም አጋማሽ ጥሩ ጨዋታ ነው ፤ 90 ደቂቃ ተጭነን ተጫውተናል። ቀድሞ የማይታሰብ ጎል ገባብን ፤ ተጋጣሚያችን በደንብ እየተከላከለ ነበር። በአጋጣሚ የሄደ ኳስ ገባብን። እሱን ለማስተካከል ሞከርን አስተካከልን። ከዛ በኋላ የጎል ዕድሎችን አግኝተናል ፤ ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር አልተሳካም።
በተከታታይ ጨዋታ ቀድመው ግብ ስለማስተናገዳቸው…
የዛሬውን ዓይነት ጎል ቀድሞ መተንበይ አይቻልም። በእርግጠኝነት ተጫዋቹም ሳይታሰብ መትቶት ነው የገባው። ተከላካዮችን ረብሸው ወይም ደግሞ ወደ ሳጥን መጥተው ከጨዋታ ውጪ አድርገውን አይደለም የገባው። ከዳር ዝም ብሎ የተመታ ኳስ ነው መረቡ ላይ ያረፈው። እንደዚህ ዓይነት ነገር ያጋጥማል ፤ እንደ ቡድን ግን በደንብ ሁሉንም ነገር አድርገናል። በርግጥ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ አሁንም ፍጹምነቶች ይቀሩናል። ግን በደንብ ተጫውተናል ብዬ ነው የማስበው።
ቡድኑ ላይ ዕድገት እያዩ ስለመሆናቸው…
ምንም ጥያቄ የለውም ዛሬ ጥሩ ቡድን ሜዳ ላይ አይቻለሁ። የሚያጠቃ እና ሲከላከል በደንብ የሚከላከል ስሜት ያለው ቡድን ሜዳ ላይ አይቻለሁ ፤ ይሄንን ወደ ውጤት መቀየር ነው ያቃተን። በአጠቃላይ በድሬዳዋ ቆይታችን እስካሁን ቡድናችን ላይ ማደግ ታይቷል ወደ ውጤት ነው መቀየር ያልቻልነው። ይሄ ደግሞ እንደሚታየው ሜዳ ላይ ትንሽ መቸኮል አለ። ጨዋታውን ለማሸነፍ ያለን ፍላጎት እና ስነልቦናችንን ማስተካከል ይጠበቅብናል።
አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ) – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ስለጨዋታው…
በእንቅስቃሴ ረገድ ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። የመጣነው ትንሽ ከበድ ካለ ነገር ስለሆነ ያንን ለማረም ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመውጣት ያደረግነው ነገር ጥሩ ነበር። ይሄም ተሳክቶልናል።
ስለተገኘው አንድ ነጥብ…
ጨዋታውን ማሸነፍም ነበረብን። ስህተቶቻችን ብዙ ጊዜ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ይሄንን ለማረም እየሞከርን ነው። ዛሬም የተቆጠረብን ጎል የእኛ ስህተት ነው። ማስቆጠር የምንችላቸውን ደግሞ ሳናስቆጥር ቀርተናል። ይህ ቢሆንም ግን አቻው ጥሩ ነው። በቀጣይ የተሻለ ነገር እናገኛለን ብዬ አስባለው።
ቡድኑን ለመለወጥ እየተከወነ ስላለው ሥራ…
አንደኛ በአጨዋወታችን ላይ የተሻለ ነገር ሰርቶ ለመሄድ ነው። በዚህ ሂደት ወደ ውጤት ለመመለስ ጥሩ ነገሮችን ለመስራት ነው እየሞከርን ያለነው። ነገር ግን ያለን የቡድን ይዘት ላይ አንዳንድ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። በዋናነት ግን ባለን ነገር ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ነው እየጣርን ያለነው።