በ10ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን በሚከተለው መልኩ በምርጥ ቡድናችን አካተናል።
የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-4-2
ግብ ጠባቂ
ፋሲል ገብረሚካኤል – ባህር ዳር ከተማ
የግብ ዘቡ ፋሲል ቡድኑ ሀዲያን 2ለ0 ሲረታ ከብዙዎች አድናቆት እንዲያስቸረው ያደረገ ብቃት አሳይቷል። ምናልባት የጨዋታው ልዩነት ልትሆን የነበረችውን የ6ኛ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ ተጫዋቹ አምስት ለግብነት የቀረቡ ሌሎች ሙከራዎችን በሚገርም ቅልጥፍና ሲያመክን አምሽቶ ቡድኑ ካለምንም ግብ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችሏል።
ተከላካዮች
ዓለምብርሃን ይግዛው – ፋሲል ከነማ
ከግብ ጠባቂው ሳማኬ ጋር እኩል 720 ደቂቃዎችን የተጫወተው ዓለምብርሃን ከሳምንት ሳምንት በወጥ ብቃት ላይ የሚገኝ ተጫዋች ነው። በ10ኛ ሳምንትም በቀኝ መስመሩ ላይ በማጥቃትም ሆነ በመከላከሉ ረገድ በጥሩ ብርታት ሲጫወት ነበር። ከፊቱ ከሚሰለፈው ሽመክት ጋርም በጥሩ ቅንጅት የቡድኑን የቀኝ መስመር አደገኛ አድርገውት ታይተዋል።
ታምራት አየለ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ለገጣፎ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች አልቀመስ ብሎ ሲውል በኋላ መስመር ከመዝገቡ ጋር የተጣመረው ታምራት ድንቅ የመከላከል ስራ ሲሰራ ነበር። በጨዋታው ቡና በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዞ ወደ ሜዳ ቢገባም በዐየርም ሆነ በመሬት የሚላኩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በተሻለ ሲያመክን የነበረው ታምራት አንዱን የመሐል ተከላካይነት ቦታ እንዲይዝ አድርጎታል።
አዩብ በቀታ – አርባምንጭ ከተማ
በሦስት የመሐል ተከላካይ ውቅር ወደ ሜዳ የገባው አርባምንጭ ከተማ የተጋጣሚን ጥቃት በማክሸፉ ረገድ የተዋጣለት ምሽት ነበረው። በተለይ ደግሞ አዩብ ጊዜያቸውን የጠበቁ ውሳኔዎች በመወሰን የአዳማን አጥቂዎች ለመቆጣጠር ያደረገው ብቃት ሲደነቅ ተጋጣሚም በሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች እንዲቀይር ያስገደደ ውሳኔ አስከትሏል።
ፍፁም ግርማ – ወልቂጤ ከተማ
በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሰባተኛ ጨዋታውን ያደረገው የግራ መስመር ተከላካዩ ፍፁም የድሬዳዋን የመስመር አጨዋወት በማጥፋቱ ረገድ የተሳካለት ጊዜ አሳልፏል። ከእርሱ ፊት ለሚገኙ ተጫዋቾችም የማጥቃት ነፃነት በመስጠት ቡድኑን ሲጠቅም ተመልክተናል።
አማካዮች
ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ
በፋሲል የ4ለ2 ድል የነጠረ ብቃት ያሳየው ሽመክት በሚታወቅበት መታተር ሲጫወት ታይቷል። ከተቆጠሩት አራት ግቦች የፍፁም ቅጣት ምቱ እርሱ በተሰለፈበት መስመር በሚደረግ ጥቃት የተገኘ ሲሆን የሁለተኛው ጎል ደግሞ መነሻ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በ25ኛው ደቂቃ ከሌላኛው ኮከብ ፍቃዱ ጋር በጥሩ አንድ ሁለት ግብ አስቆጥሯል።
አስራት መገርሳ – ወልቂጤ ከተማ
ከወልቂጤ ቡድን በምርጥ ቡድናችን የተካተተው ሌላኛው ተጫዋች አስራት ነው። እንደ ቡድኑ ቅፅል ስም በጥሩ የሰራተኝነት መንፈስ ሲጫወት የተመለከትነው አስራት በተለይ ቡድኑ የመምራት ቦታ ላይ እያለ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ጨዋታውን በመቆጣጠር መልካም የሚባል አበርክቶ ሲሰጥ ስለነበር የአማካይ መስመሩ ላይ ተሰልፏል።
ቻርለስ ሪባኑ – ባህር ዳር ከተማ
ቻርለስ ሪባኑ በፈታኙ የሀዲያ ፍልሚያ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን በመቆጣጠር እና የፊት መስመር አጥቂዎቹን ፍጥነት ያገናዘቡ የተከላካይ ጀርባ እንዲሁም ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች በመላክ ቡድኑን በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ሲያግዝ ስለነበር በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል።
ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከቀድሞ ክለቡ ወላይታ ድቻ ጋር የተጫወተው ቸርነት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታው የራስ መተማመኑን አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ያደረገ ግብ ገና በ5ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ተጫዋቹ ወረቀት ላይ የግራ አጥቂ ቢሆንም በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ የነበሩትን ድቻዎች ለማስከፈት በሚዋልል አጨዋወት ወደ መሐል እየገባ ለራሱ እና ለአጋሮቹ ክፍተት እንዲፈጠር ሲያደርግ ነበር። ግቡንም በተመሳሳይ መንገድ በስሙ አስመዝግቧል።
አጥቂዎች
ፍቃዱ ዓለሙ – ፋሲል ከነማ
በጨዋታ ሳምንቱ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ጎል ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው የሆነው ፍቃዱ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ ሆኗል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ለሲዳማ ተከላካዮች ፈተና የነበረው ፍቃዱ ሁለት ጎል ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስ ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል።
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ
የወልቂጤ አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ እንዳሉት እንደ ወይን እየጣፈጠ የመጣው ጌታነህ ባሳለፍነውም የጨዋታ ሳምንት የቡድኑን ሁለት ግቦች ከመረብ አሳርፏል። በተለይ የመጀመሪያው ጎል የተጋጣሚን ተጫዋች ስህተት አነፍንፎ ተከላካዮችን በማታለል በግራ እግሩ ከመረብ ያገናኘበት መንገድ ተጫዋቹ የተሟላ አጥቂ እንደሆነ በሚገባ ያስመሰከረ ነበር።
አሠልጣኝ
ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ
በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያገኘበትን ውጤት አስመዝግቦ ሽቅብ መጓዙን ቀጥሏል። ጠንካራ በነበረው የሀዲያ ጨዋታ ቡድኑ በተወሰነ ቢፈተንም በጊዜ ውጤት በእጁ ያስገባበት እንዲሁም በአጠቃላይ ጨዋታውን የተቆጣጠረበት መንገድ አሠልጣኙን በምርጥ ቡድናችን እንድናስገባ አድርጎናል።
ተጠባባቂ
መሐመድ ሙንታሪ
በርናንድ ኦቺንግ
እያሱ ለገሰ
ጋብሬል አህመድ
ታፈሰ ሰለሞን
ፍፁም ዓለሙ
ፍፁም ጥላሁን
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ