በሦስት ከተሞች የሚደረገው የዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ዛሬ ባስተናገዳቸው ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰፊ ልዩነት ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ ሰባት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል።
የ04:00 ጨዋታዎች
በባህር ዳር ከተማ ዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ላይ የሚደረገው የምድብ ‘ሀ’ አቃቂ ቃሊቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ ሲጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ፣ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች የክብር እንግዶች በተገኙበት የመክፈቻ መርሐ-ግብር ተደርጓል።
በጨዋታው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል የበላይነቱን ሲወስዱ በ8ኛው ደቂቃም መሪ ሆነዋል። ሀይከር ድዋሮ መነሻው ከቀኝ መስመር የሆነን ኳስ ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂውን በማለፍ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ንግድ ባንኮች ኳስን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ትዕዛዙ ፍቃዱ አብዱለጢፍ ሙራድ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ልዑልሰገድ አስፋው አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል።
ከዕረፍት መልስ በፈጣን ሽግግሮች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የፈጠሩት አቃቂዎቾ 50ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ አግኝተዋል። ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ከድር አድማሱ አስቆጥሯል። አቃቂዎች የተሻለ የጨዋታ መንፈስ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ይባሱንም ተጨማሪ ግቦች አስተናግደዋል። ልዑል ሰገድ አስፋው በ 70ኛው እና 86ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ሐትሪክ መሥራት ሲችል 77ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ ሙራድ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በምድብ ለ እንጅባራ ከተማ እና ጅንካ ከተማ ተገናኝተው አንተነህ ተሾመ በ51ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ጅንካዎች ቀዳሚ ቢሆኑም አበበ ታደሰ 69ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም ተመስገን ሀንቆ 79ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝተው እንጅባራ ከተማን ለድል አብቅተዋል።
ምድብ ‘ሐ’ ደግሞ ሆሳዕና ላይ ሮቤ ከተማ እና ገላን ከተማን ባገናኘው ጨዋታ ሲጀምር በሲሳይ ባንጫ ግብ ጠባቂነት የሚመራው ሮቤ ከተማ ሁለት ግብ አስተናግዶ የተረታ ሲሆን በ7ኛ ደቂቃ ያሬድ ወንድምአገኝ እንዲሁም 62ኛው ላይ በሱፍቃድ ነጋሽ ለገላን ከተማ አስቆጥረዋል።
የ08:00 ጨዋታዎች
ከምሳ በኋላ ባህር ዳር ላይ ጠንካራ እና ለተመልካች አዝናኝ ፉክክር በታየበት የአዲስ ከተማ እና ሰንዳፋ በኬ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩበት በሁለተኛው አጋማሽ ግን አዲስ ከተማዎች ይበልጥ ተሻሽለው ቀርበዋል። በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት አዲስ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥራቸው ታግዘው አቤል ፀጋዬ 70ኛው ደቂቃ ላይ እና ያሬድ ዓለማየሁ 82ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል።
በምድብ ‘ለ’ የ 08:00 ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረው የአመረላ ደልታታ ብቸኛ ግብ ጉለሌ ክፍለከተማን ሲረታ ሆሳዕና ላይ በተደረገው ጨዋታ ሀምበርቾ ዱራሜ 54 ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ እንዲሁም 80ኛ ደቂቃ ላይ አላዛር ዝናቡ ባስቆጠሯቸው ግቦች ዳሞት ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
የ10:00 ጨዋታዎች
ባህር ዳር ላይ የተደረገው የምድብ ሀ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ እንቅስቃሴውን የማይገልጽ ውጤት የተመዘገበበት ነበር። ተጋጣሚዎቹ ጋሞ ጨንቻ እና ቤንች ማጂ ቡና ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረጉ በኩል ግን ቤንች ማጂዎች የተሻሉ ነበሩ። ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያውን የተሻለ የግብ ሙከራ ያስመለከተን 34ኛው ደቂቃ ሲሆን የጋሞ ጨንቻው ለገሠ ዳዊት ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን የቀኙ ቋሚ ታክኮ ወጥቷል።
ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ሆኖ ሲቀርብ በርካታ የግብ ሙከራዎችን አስተናግዷል። በተለይም 70ኛው ደቂቃ ላይ የቤንች ማጂው ዳንኤል አገኘሁ ከግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ሲመታ ኳሱ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰውና 77ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር ወደግብ ሞክሮት በዕለቱ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ንጉሤ ሙሉጌታ ወደማዕዘን ያስወጣው ኳስ በቤንች ማጂዎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ጅማ ላይ የተከናወነው የቂርቆስ እና ደብረብርሀን ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን በምድብ ሐ ግን ስልጤ ወራቤ የካን 3-1 መርታት ችሏል። የካዎች 27ኛው ደቂቃ ላይ በጌታ አየለ ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም ስልጤ ወራቤዎች ከሦስት ደቂቃ በኋላ በጥዑመልሳን ገብረሚካኤል እንዱሁም ጨዋታው ለዕረፍት ሲቃረብ ጃፋር መደሲር ባስቆጠሯቸው ጎሎች እየመሩ ጨዋታውን አጋምሰዋል። ስልጤዎች ከዕረፍት በኋላ በዳንኤል ታደሰ ያስቆጠሩት ጎል ደግሞ አሸናፊነታቸውን ያረጋገጠ ሆኗል።
ውድድሩ በመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብሩ ነገም በሦስቱ ከተማዎች በሚደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች እንደሚቀጥል ይጠበቃል።